የኦፌኮና የአብን መግለጫ፤ የዶክተር ቴድሮስ ወቀሳ  | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 15.04.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኦፌኮና የአብን መግለጫ፤ የዶክተር ቴድሮስ ወቀሳ 

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ፤ ኦፌኮ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን መግለጫ፣ የቅርስ ፈረሳ በአዲስ አበባ እንዲሁም የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረቡት ወቀሳ በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙ መነጋገሪያ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው። 

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኦፌኮና የአብን መግለጫ፤ የቅርስ ፈረሳ በአዲስ አበባ እና የዶክተር ቴድሮስ ወቀሳ 
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ፤ ኦፌኮ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን መግለጫ፣ የቅርስ ፈረሳ በአዲስ አበባ እንዲሁም የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረቡት ወቀሳ በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙ መነጋገሪያ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው። 
 በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱየኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ሚያዚያ 3 ቀን፣ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ ከአማራ ክልል ተነሱ ያላቸው ታጣቂዎች የኦሮሚያ ክልልን ወሰን ጥሰው በተለያዩ ቦታዎች  የመሬት ወረራ ላይ ተሰማርተዋል ብሏል።


 የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ሚያዚያ 4 ቀን፣ 2014 ባወጣው መግለጫ ደግሞ  የኦፌኮን መግለጫ በመረጃ ላይ ያልተመሰረተ እና በአማራ እና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ግጭት የሚፈጥር ነው ሲል ነቅፎታል።

Logo | National Movement of Amhara


የፓርቲዎቹን መግለጫ ተከትሎ ዓለም ተገኑ የተባሉ አስተያየት ሰጪ«ኦፌኮዎች ለኦሮሞ ህዝብ የምታስቡ ከሆነ በነካ እጃችሁ ኦነግ ሸኔንም አውግዙ» ብለዋል።በሱ ፈቃድ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «እባካችሁ በመግለጫ ከመወጋገዝ ወጥታችሁ ቁጭ ብላችሁ ተወያዩ» የሚል አስተያየት አስፍረዋል። ሳሙኤል አሰፋ ደግሞ «ነገ ንፁህንን የአማራ ገበሬ ይገድሉና ታጣቂዎች ገደልን ለማለት የተፈጠረ ሰበብ  ነው» ሲሉ፤ ጌች በቀለ «አይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ ሆነ ነገሩ»ብለዋል። ጂግሳ ኒሞና የተባሉ አእሰተያየት ሰጪ ደግሞ «የተከሰሰው የአማራ ክልል መንግስት ሆኖ እያለ የአብን ቀድሞ መግለጫ መስጠት ምን ይሉታል። ኦፌኮ ያወጣው መግለጫ ትክክለኛ እና  ወቅታዊ ነው።ይልቅ ሁለቱ ህዝቦች ጦርነት ውስጥ እንዳይገቡ ከተፈለገ የያዙትን መሬት ለቆ መውጣትና ትንኮሳ ማቆም ነው» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
እምሻው ሽመልስ ደግሞ « ኦነግ ሸኔ አቅመ ደካሞችንና ያልታጠቁ የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮችን በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በጅምላ ሲጨፈጭፍ ትንፍሽ ብሎ የማያውቀው ኦፌኮ ዛሬ መግለጫ መስጠቱ የሚያስተዛዝብ ነው» ብለዋል።»
አግዘህ ሲሳይ ደግሞ «ፖለቲከኞች ለስልጣን ብላችሁ በምታደርጉት ሽኩቻ ስንት ምስኪን መገደል አለበት። ምናለ ሰከን ብትሉ» ሲሉ፤ ካሳሁን ባይሳ ደግሞ «ኦፌኮ የሚለው እውነት ከሆነ ኦነግ ሸኔን ያወገዘ ሁሉ ይህንን ወረራም ማውገዝ አለበት። የፅንፈኛ መልካም የለውም»ብለዋል።
ባምላክ ነኝ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«አማራን ተጠያቂ የሚያደርገው የኦፌኮ መግለጫ ኦነግ  ሸኔ  በኦሮሚያ ክልል ለሚፈፅመው የንፁሃን ጥቃት ሽፋን ነው» ሲሉ፤ «እስከ መቼ ነው በፖለቲካ ልኂቃን ሽኩቻ ህዝቡ ሲገደል ሲፈናቀል እና ሰላም ሲያጣ የሚኖረው። አምላክ ምህረት ያውርድልን»ያሉት ደግሞ ወሰኔ ወርቁ ናቸው። 
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኜው አንበሳ ፋርማሲ እና ኒዮን አዲስ የተባሉ የቅርስ ቤቶች ሊፈርሱ ነው መባሉን ተከትሎ  የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተሰጠው ማብራሪያ በዚህ  ሳምንት መነጋገሪያ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
ኮርፖሬሽኑ አንበሳ ፋርማሲ እና ኒዮን አዲስ የቅርስ ቤቶች ይዘታቸው እና ቅርጻቸው ሳይቀየር ቤቶቹ ባሉበት ሳይነኩ በአካባቢው ከሚገነባው አዲስ ግንባታ ጋር እንዲለማ ለአልሚው ባለሀብት እንዲተላለፉ ተደረጉ እንጅ እንዲፈርሱ ተወሰነ የተባለው መረጃ መሰረተ ቢስ ነው ብሏል። 
ይህንን የኮርፖሬሽኑን መግለጫ ተከትሎ ዘነበ ሞገስ  የተባሉ አስተያየት ሰጪ «1ኛ. ቅርሶቹ ለግለሰቡ የተላለፉት በምን መልኩ ነው? በሽያጭ ወይስ በአደራ መልክ? 2ኛ.የሀገረ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ ንብረት ወደ ባለሀብት ማስተላለፍ ይቻላል ወይ?በየትኛው ህግ ነው?  በማለት በኮርፖሬሽኑ መግለጫ ላይ ጥያቄ አንስተዋል።


ቲዎድሮስ ታፈሰ ደግሞ «ቅርስ ለምን ለሶስተኛ ወገን ይተላለፋል ?  ቅርስ ለመጠበቅ ማነው ሀላፊነት ያለበት ? ግለሰብ ወይንስ መንግስት?»ሲሉ ጠይቀዋል።ጥላሁን ሲሳይ  ደግሞ «የሀገርን ቅርስ ለግለሰብ ማዘዋወር ተገቢ አይደለም »ብለዋል። ኪያ አሸናፊ  «አሁን ይሄ ሁላ ጩኸት ለቅርሱ ታስቦ ነው? ደሀ ቅርስ ያስለቅሳል እንዴ?የተሻለ ነገር ተሰርቶበት ሀገር ወገን የሚጠቀም ከሆነ እሰየው ይሁን።ትልቅ ህንጻ ተገንብቶ ከፍተኛ ጥቅም በሚያስገኝ ቦታ ላይ አንድ ደሳሳ ቤት ለምን ይፈርሳል ብሎ ከልክ በላይ መጮህ ተገቢ አይመስለኝም» ብለዋል።
አብዱ ብስራት «ከመጀመሪያዉስ ካልጠፋ ቦታ በቅርስ የተመዘገበ ቦታን ለግለሰብ መስጠት ለምን አስፈለገ? አሁን ሰዉ ትኩረት ስለሰጠዉ ማቀዝቀዣ የሚመስል መግለጫ  የምታወጡት?ለመሆኑ ቡፌ ደ ላጋር ሳይፈርስ ነዉ ግንባታዉ የሚሰራው ተብሎ መፍረሱን ሰዉ short memory ስለሆነ ረስቶታአል ብላችሁ ነዉ?» ሲሉ፤ያፌት ያፌት በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «ቅርስን ለሶስተኛ ወገን ጠብቅልኝ ብሎ አሳልፎ መስጠት ከየትኛው ሀገር የተገኘ ጠቃሚ ልምድ  ነው? እስኪ ይጠቀስ:: ገንዘቤን ጠብቅልኝ ብሎ ሌላ ሰው ኪስ ውስጥ የማስቀመጥ ያህል ነው::»ብለዋል።
ፍቅሩ ተሾመ «ከዚህ በፊት የመጀመሪያውን ታሪካዊ ሲኒማ ሰይጣን ቤትን ሊያፈርሱ ሲል ህዝብ በመከራ አስቆመ።ነገር ግን ጭራሽ ታሪካዊነቱን እንደመጠበቅ ውስጡን ለሱቅ ነት እየሸነሸኑት ነው። ታሪክ የሌለው ትውልድ  ማፍራት ለማን ይጠቅማል።» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

ዓለም ለዩክሬን የሰጠውን ትኩረት ያህል በሌሎች አካባቢዎች ለሚደረጉ ግጭቶችና ጦርነቶች ትኩረት  አልሰጠም ሲሉ መናገራቸው ነበር።ዋና ዳይሬክተሩ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  ዓለም ለዩክሬን ጦርነት ከሰጠዉ ትኩረት በጣም ትንሹን  እንኳን ለኢትዮጵያ፣ ለየመን፣ ለአፍጋኒስታን፣ ለሶሪያና ለመሳሰሉት ጦርነትና ቀዉሶች አልሰጠም።ዶ/ር ቴድሮስ አያይዘውም ዓለም ጥቁሮችን  እንደነጮች ሁሉ  እኩል እየተመለከተ እንዳይደለ ተናግረዋል።
ይህንን ተከትሎ አፎሚያ የተባሉ አስተያት ሰጪ «ዶክተር እንኮራበዎታለን ድምፅ ለሌለን ድምፅ ስለሆኑ እናመሰኛለን» ብለዋል።
ባዩ ፈለቀ አርጋው «ዶክተር  ቴድሮስ እስቲ እርሰዎም ስለ አፋሩ ስለ አማራው እና  ሰለ ሌሎችም እኩል ትኩረት መስጠት  ይጀምሩ። ያኔ ለውቀሳም ይመቸዎታል»የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። አስተራዮ «የእነርሱ የታወቀ ነው። የሚያሳዝነው ግን እርሰዎም ከእነርሱ ጋር ተባብረው የበቀሉበትን ሀገር  መበደልዎ ነው» ብለዋል።
ሳም ቮድ በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት  ደግሞ «ዶክተር ቴድሮስ እውነት አላቸው። ሶርያ፣ የመን ኢራቅ፣ ሊቢያ  አፍጋኒስታን እንዲሁም በአፍሪቃም በርካታ ሀገራት ሲቸገሩ  ባለየ እና ባልሰማ ያለፈው የምዕራቡ ዓለም  ዩክሬን ላይ እንዲህ መጮሁ ከዘረኝነት ሌላ ምን ሊባል ይችላል» ሲሉ፤ ባየች ዓለማየሁ ደግሞ «ምነው እሳቸውስ  በአፋር እና በአማራ ክልል የወደሙትን የጤና ተቋማት ባላዬ አልፈው ስለ አንድ  ክልል ብቻ አይደለም ሲጮሁ የነበሩት።ታዲያ ምን ይገርማል» ብለዋል።
ስምረት ተፈሪ  ደግሞ «የዓለም የጤና ድርጅት ሀላፊ ሆነው ሳለ የተቀመጡበትን የሀላፊነት ቦታ በማይመጥን ሁኔታ ለአንድ ክልል መቆመዎንስ ምን እንበለው ዶክተር?» በማለት ጠይቀዋል።
«የፈለገ  አስተያየት ቢሰጥ የፈለገ ሰው ቢንጫጫ እውነት መናገርህን ቀጥል የኛ ጀግና»ያሉት ደግሞ ብሩክቲ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው።
ፌበን ሙላት ደግሞ «ሰውየው የራሳቸው ድክመት እና ጥንካሬ ሊኖራቸው ይችላል ።የተናገሩት ግን መሬት ጠብ የማይል መራራ ሀቅ ነው።ለዩክሬን የተሰጠው ትኩረት ዓለም ፍትህ  የጎደላት መሆኑን ያሳያል» የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።


ፀሀይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

Audios and videos on the topic