የኦዴግ አገር ቤት መግባትና «አንዲ ይፈታ» ዘመቻ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 25.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዘመቻው ዳግም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ኦዴግ አገር ቤት መግባቱ አነጋግሯል።

የኦዴግ አገር ቤት መግባትና «አንዲ ይፈታ» ዘመቻ

​​​​​​​«ፓለቲካ የሰለቻቸው፣ የውጭ ሕይወት ያንገሸገሻቸው፣ የጡረተኛ ስብስብ ናቸው» ሲል ይገልጣቸዋል። ሌላኛው ደግሞ፦«ሙሉ የኢትዮጵያ ፓለቲከኛ ቢጨመቅ አንድ ሌንጮን አይሆንም» ይላል። ከሰሞኑ ኢትዮጵያ የገቡት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አመራር አባላትን በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡ አስተያየቶች የተቀነጨቡ ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:09

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሣምንቱ መነጋገሪያ

ኦዴግ አዲስ አበባ መግባቱ

ሐሙስ ዕለት በትዊተር የቀረበ መልእክት ነው። እንዲህ ይነበባል፦ «ክቡር ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ከኦዴግ መሪዎች ጋር ዛሬ ተገናኝተዋል። የኦዴግ አባላት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውይይት በሠላማዊ መንገድ ለመሳተፍም ተስማምተዋል። ሁለቱም ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር እና የዲሞክራሲ ሒደታችንን በማስፋት ላይ አተኩረው ለመሥራት ተስማምተዋል።» 

ይኽ መልእክት የቀረበው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፍጹም አረጋ በሚል የትዊተር ገጽ ነው። ከጽሑፉ ጋር ተያይዞ በቀረቡት ሁለት ፎቶግራፎች ላይ ጠቅላይ ሚንሥትሩ እና የኦዴግ አመራር ሲነጋገሩ ይታያል። እንደ አቶ ፍጹም አረጋ ሌላ የትዊተር መልእክት ከኾነ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር አባላት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን በመንግሥት ግብዣ ነው።

«የሚያነቃቃ ፎቶ» ሲል ይንደረደራል፤ ለአቶ ፍጹም መልእክት ከተሰጡ መልሶች መካከል አንዱ። የቴዎድሮስ መከተ ወዳጆ መልእክት ነው። «መሠረቱ ፍቅር እና ይቅር ባይነት ከኾነ ሁሉም ነገር ይኾናል» ሲልም ይጠቃለላል። ዋይ ኤም ጂ በሚል የእንግሊዝኛ ምኅጻረ ቃል የተላለፈ መልእክት የኦዴግ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን በጥርጣሬ ይመለከታል። «ከመሀከላቸው አንደኛው በሽግግር መንግሥቱ ጊዜ ሚንሥትር ነበሩ። መቼም ወደ 60ዎቹ ዘመን እንደማይመልሱን ተስፋ አደርጋለሁ» ይላል በእንግሊዝኛ ቋንቋ የቀረበው ጽሑፍ። የሣሙኤል ቲ የትዊተር ምልእክትም ተመሳሳይ ጥርጣሬ አዝሏል። እንዲህ ይነበባል፦ «የድሮ ዘመን አስተሳሰብ ተዛማች ነው የሚል ፍራቻ አለኝ። አንጋፋዎቹ የማኅበረሰብ መሪዎች ብቻ ነው መኾን የሚችሉት።»

ከአቶ ፍጹም አረጋ የትዊተር መልእክት፦ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር» የሚለውን ሐረግ በመምዘዝ ሥላቃዊ ጽሑፍ ያቀረበው ዮሴፍ ታደሰ ነው። «የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ከሌንጮ ጋር። ይኼ እጅግ አስደማሚ ነው። ሐረግ መሰካካት እንዲህ ቀላል ነው» ብሏል ዮሴፍ።

እዚህ ርእሰ-ጉዳይ ላይ ተንተርሰው በፌስቡክ ከተላለፉ መልእክቶች ውስጥ «ሙሉ የኢትዮጵያ ፓለቲከኛ ቢጨመቅ አንድ ሌንጮን አይሆንም» ይላል። መልእክቱ ዊን ዊን በሚል የፌስቡክ ስም ነው የቀረበው።

«ፓለቲካ የሰለቻቸው፣ የውጭ ሕይወት ያንገሸገሻቸው የጡረተኛ ስብስብ ናቸው» ሲል የሚገልጣቸው ቦሴ ጤን የተሰኘ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው። «የፓለቲካ ለውጥ ለማምጣት ለመታገል ሳይሆን ጡረታቸውን ሀገር ውስጥ የማሳለፍ ጉጉት ነው» ሲልም ይገልጣቸዋል የኦዴግ አመራርን። ቦሴ «ተቀባይነትም አያገኙም» ሲል ይቀጥላል።

«ምክንያቱም ቆምንለት ላሉት ኦሮም ህዝብ ሞት መከራና ስቃይ አደረሱበት እንጂ አልጠቀሙትም። ታሪካቸውም የሚያሳየው ይሄን ነው። ነገ ሩቅ አይደለም አድርባይነታቸውን እናየዋለን» ሲልም ጥርጣሬውን አጉልቷል።

ዬሮ ጋሪ ደግሞ እዛው ፌስቡክ ላይ ቀጣዩን መልእክት አስተላልፏል። «መጀመሪያውም ይህ ድርጅት የተቋቋመው እነዚህን ስብስብ ይዞ ወደ ሀገር ለመመለስ ታስቦ ነው እንጂ አንድም ነገር ለኦሮሞ ህዝብ ለማምጣት አይደለም። ስለሆነም መጣ አልመጣ ማንንም አይጎዳ፣አይጠቅምም» ብሏል።

አቤ ጊምቢ ደግሞ፦ «ሰውዬው ሌንጮ ለታ በታሪካችን ውስጥ መጥፎ ትዝታ ጥሎብን አልፏል። ስለዚህ ይህ ሰውዬ ወንጀለኛ ነው እናም ድርጅቱ የሚያመጣው ለውጥ የለም» የሚል መልእክት አስፍሯል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ በጡረታ ያሰናበቷቸውን የኢህአዴግ አባላት በማስታወስ ይመስላል ሔዋን ነጋ ቀጣዩን ትችት አቅርባለች። «ሽማግሌዎቹ ጡረታ እየወጡ ሽማግሌ አንፈልግም» ስትል።

Großbritannien - Protest gegen Haft von Andargachew Tsige

የአቶ አንዳርጋጋቸውን መታሠር በተመለከተ ተቃውሞ በለንደን ከተማ፤ ከግራ ወደ ቀኝ፦ የሚ ኃይለማርያም፣ ይላቅ አንዳርጋቸው፣ ኅላዊት ኃይለማርያም እና መንበረ አንዳርጋቸው፤ እንዲሁም የምክር ቤት አባል ክሊቭ ሌዊስ፣ ዳሜ ሐሪየት ቫልተር እና ሣራ ፓስኮ

«መደራደር ካለበት ከታገለው፣ ከታሰረው፣ ከደማውና ከሞተው እንጂ ከውጭ ከመጣው ጋር ቢደራደሩ ትርጉም የለውም» አስተያየት ሰጪው ዮናስ ሳሙኤል ነው በፌስቡክ።

ዳግም ዘመቻ፦ «አንዳርጋቸው ይፈታ»

በብሪታንያ የሌበር ፓርቲ መሪ ጄሬሚ ኮርቢን «አንዲ ጽጌ እኔ በማስተዳድርበት ግዛት ነዋሪ የብሪታንያ ዜጋ ነው። ሦስቱ ልጆቹ መመለሱን ይሻሉ» ብለዋል።። ዛሬ የብሪታንያ መንግሥት አንዳች ነገር እንዲያደርግ በድጋሚ እጠይቃለሁ» ያሉት ጄሬሚ አቶ አንዳርጋቸው እንዲፈቱ የሚወተውተው የማኅበራዊ መገናኛ ዘመቻ አካል መኾናቸውን 2 ሚሊዮን ግድም ተከታይ ባለውበይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ገልጠዋል።  

ሬፕራይቭ የተሰኘው በዓለም ዙሪያ የሞት ፍርደኞች እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ትኩረት የሚያደርገው ዓለም አቀፍ ተቋም የብሪታንያው ባለሥልጣን የቪዲዮ መልእክትን በትዊተር ገጹ አሰራጭቷል። የሌበር ፓርቲ መሪው ጄሬሚ ኮርቢን ስለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በአፋጣኝ መፈታት የጠየቁበት የቪዲዮ መልእክት እንዲህ ይላል።

«የሚ ኃይለማርያምን አናግሬያታለሁ። የትዳር አጋሯ አንዲ የብሪታንያ ዜጋ ነው። ሦስት ልጆችም አሏቸው። እነዚህ ልጆች ያለ አባታቸው እያደጉ ነው። ምክንያቱም አንዲ በ2006 ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ ታፍኖ ሕገ ወጥ በኾነ መንገድ ወደኢትዮጵያ ተወስዷል። በሞት ፍርደኛነት ሰቆቃ እያየ ነው። በሚያሳፍር መልኩ ወግ አጥባቂው መንግሥት የእሱን መታፈን ማውገዝ ተስኖታል፤ እንዲመለስ ሳይደራደር ቀርቷል። ዛሬ ለቴሬዛ ሜይ እና ቦሪስ ጆንሰን የአንዲን ሰብአዊ መብቶች ለማስከበር እና በአፋጣኝ ወደቤቱ ወደ ብሪታንያ እንዲመለስ ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ የምታሰሙ በሺህዎች የምትቆጠሩትን ተቀላቅያለሁ።  አንዲ ከትዳር አጋሩ እና ከሦስት ልጆቹ ጋር ውሎ ሳያድር ሊገናኝ ይገባል።»

«የዛሬ ሁለት ዓመት ወለል ብሎ የታየኝን ህልም ፌስቡክ አስታወሰኝ! ህልም እውን እስኪሆን ስንት ዘበን ይፈጃል?» ሲል ጽሑፉን የሚያንደረድረው ደግሞ ክፍሉ ሁሴን ነው። የዛሬ ሁለት ዓመት እዛው ፌስቡክ ላይ ያሰፈረው መልእክቱ፦ «በህልሜ አንዳርጋቸው ጽጌ ተፈቶ አየሁ!» ይላል። «ከምሬ ነው!» ሲልም ይቀጥላል ክፍሉ በጽሑፉ።  «ፍንትው ባለ ሁኔታ አግኝቼውም አዋራሁት! ከሳ ብሏል (ባይከሳ ነው የሚገርመው) የወትሮ ንቃቱንም አጥቷል!» እያለ ይወርዳል የክፍሉ መልእክት።  

በኢትዮጵያ መንግሥት የሚቆጣጠረዉ ቴሌቪዥን የዛሬ አራት ዓመት በሰጠው መግለጫ መሠረት አቶ አንዳርጋቸው የተያዙት ሰኔ 16 2006 ዓም የመን ሰንዓ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ነበር።

በዚህ ሁሉ ዓመት ግን በውል የትኛው እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙም ዐይታወቅም። በደንብ የሚታወቀው ነገር ቢኖር በቅርቡ ከእስር እንደሚለቀቁ በእርግጠኝነት የሚንሽራሸረው መልእክት ነው።  «አንዳርጋቸው ይፈታ» ዘመቻ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል። አሁን ደግሞ በእንግሊዝኛ «free Andy» ማለትም በቁልምጫ «አንዲን ፍቱ» የሚል ዘመቻ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።  

ብሪያን ማክጉዊርክ ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሰፈረው መልእክት እንዲህ ይላል። «ብሪታንያዊው አባት አንዲ ተጠልፎ ኢትዮጵያ ተወስዷል። የሞት ፍርድም ተበይኖበታል። ወደ ቤቱ እንድንመልሰው እርዱን። አንዲ ጽጌን ፍቱት።»  

Großbritannien - Protest gegen Haft von Andargachew Tsige

አቶ አንዳርጋቸው እንዲፈቱ ዘመቻ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2016

ኢትዮጵያን ዲጄ የተሰኘ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ ከተናገሩት የተወሰደ በሚል የሚከተለው መልእክት ሰፍሯል። «አቶ አንዳርጋቸውን በማሰራችን የተጠቀምነው ነገር የለም። የተረፈን ጥላቻና ከእንግሊዝ መንግሥት 11 ቢሊዮን ዶላር ማጣት ብቻ ነው።»

ነገሠ ተፈረደኝ ፌስቡክ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ «የፍትህና የነጻነት ጩኸት» በሚል ርእስ ስር ነው የቀረበው።  «አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈታ በውጭም በሃገር ውስጥም ስትጮሁ የነበራችሁ የፍትህ የነጻነት ቤተሰቦች ጩኸታችሁ ተሰምቶ ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ በሚቀጥለው ሳምንት የነጻነት ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በእስር ቤት የሚገኙ ባለሃብቶችን እንደሚፈቱ ተናገሩ» ይላል።

በፍቃዱ አባይ ደግሞ ረቡዕ እለት ፌስቡክ ላይ ባሰፈረው መልእክት፦ «ጉዳዩን ስንጠቀልለው ትናንት ምሽት በብሄራዊ ቤተመንግስት ለትግራይ ክልል ተወላጅ አርቲስቶች፣ ባለ ሀብቶች፣ታዋቂ ሰዎች ፖለቲከኞችና ሌሎች ተጋባዦች ከምሽት 12፡00 ጀምሮ ጠ/ሚ/ሩ ግብዣና ነጻ ውይይት አድርገው ነበር» ብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic