የኦባማ ጉብኝት በአፍሪቃ | ዓለም | DW | 01.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኦባማ ጉብኝት በአፍሪቃ

አፍሪቃዉያን ፖለቲከኞች በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት ለምሥራቅ-ምዕራብ ሐያላን ማደራቸዉ ለአፍሪቃ ሕዝብ በጦርነት፥ በረሐብ፥ በሽታ ከማለቅ፥ መሰደድ ሌላ ያተረፉትለት የለም።የዛሬዎቹ የአፍሪቃ መሪዎች ቤጂንግ-ዋሽግተኖች ከሚመሩት

ከብሪክስ፥ እና ከቡድን ሰባት ተቀናቃኞች ጋር መሻረካቸዉን ለሕዝባቸዉ ጥቅም ካላዋሉት ካለፈዉ ጥፋት አልተማሩም ግብፅ፣-የዩናተድ ስቴትስ ታማኝ፣ታዛዥ፣የግብፆች የረጅም ጊዜ ጨቋኝ ገዢን ለማስወገድ አንድ-ሁለት ማለት ከጀመረች ጀምሮ የተጣባት ሕዝባዊ አድማ፣ ቁጣ፣ ወደ ሁከት ቁልቁል ሲደፍቃት፣ ሊቢያ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ቀንደኛ ጠላት፣ የሊቢያዎች አምባገነን ገዢን በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ አስገድላ በሠላምና ግጭት መሐል ስትዳክር፣የማሊ ሠላም በቀድሞ ቅኝ ገዢዋ በፈረንሳይ ጦር ሲጠበቅ፣ ማዕከላዊት አፍሪቃ ኮንጎን አለያም ሶማሊያን ለመቀየጥ ስትዳክር፣ የደቡብ አፍሪቃዉ የጥቁሮች የነፃነት አርበኛ ሲያጣጥሩ ከአፍሪቃዊ አባት የሚወለዱት አሜሪካዊ ፕሬዝዳት ቻይናዊ አቻቸዉን በሰወስት ወር አስቀድመዉ አፍሪቃን ጎበኙ።ባራክ ሁሴይን ኦባማ።ጉብኝታቸዉ መነሻ፣ የአፍሪቃ እዉነት ማቀሻ፣ የዋሽግተን-ቤጂንጎኝ ሽኩቻ መድረሻችን ነዉ።


አፍሪቃ አሜሪካዊ ፕሬዝዳት አንዳዶች እንደሚሉት አፍሪቃን ዘንግተዋል።ወይም ዘንግተዋት ነበር።ሌሎች ብዙዎች እንደሚያምኑት ደግሞ አፍሪቃን ባይዘነጓት እንኳን አፍሪቃን ለመጎብኘት ዘግይተዋል።በኢትዮጵያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዴቪድ ሺን በዚሕ ይስማማሉ።«ትክክል ነዉ።በመጀመሪያ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ለአፍሪቃ ብዙም ትኩረት አልሰጡም።ሰዎች ብዙ ጠብቀዉ ነበር።በሌላ በኩል ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ያሉ በርካታ ጉዳዮች፥ በተለይም የገንዘብ ቀዉሱ፥ ለአፍሪቃ የበለጠ ትኩረት የሚሠጥ መርሕ እንዳይኖር እንቅፋት ሆኗል።»ዳካር-ሴኔጋል።ሐሙስ።«ክቡር ፕሬዝዳት እንኳን ደሕና መጡ።»

«አሁን በሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ያንን (ያለፈዉን) ለማካካስ እየሞከሩ ይመስለኛል።ለዚሕም የሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣናቸዉን በጀመሩበት ዓመት፥ ሴኔጋል፥ ደቡብ አፍሪቃ እና ታንዛኒያን የሚጎበኙት።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ዳካር ከመድረሳቸዉ በፊት፥ የአሜሪካዉ ታዋቂ ጋዜጣ ዋሽግተን ፖስት እንደዘገበዉ፥ የኦባማና የሚመሩትን ቡድን አባላት ደሕንነት ለመጠበቅ በመቶ የሚቆጠሩ ልዩ የሥለላና የፀጥታ ሐይላት አስቀድመዉ አፍሪቃ ሠፍረዋል።

የተሟላ የሕክምና ማዕከል ያለዉ አዉሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከብ ከተሟላ ጦር ጋር አፍሪቃ ባሕር ጠረፍ መሕለቁን ጥሏል።የአሜሪካ ዘመናይ-ፈጣን ተዋጊ ጄቶች በአፍሪቃ ሰማይ ላይ መዓልት ወሌት-እየበረሩ የአፍሪቃን የአየር እንቅስቃሴ ይቆጣጠራሉ።ድፍን ሃያ-አራት ሠዓታት። ፕሬዝዳንቱ፥ ባለቤታቸዉና ልጆቻቸዉና ባለሥልጣኖቻቸዉ የሚጓዙባቸዉን አስራ-አራት ሊሞዚኖችን ጨምሮ ሐምሳ ስድስት መኪኖች በበርካታ የጭነት አዉሮፕላኖች ተጭነዉ ወደ አፍሪቃ ተዘርግፈዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሚያርፉባቸዉ ሆቴሎች መስኮቶች ላይ የሚለጠፍ ጥይት ተከላካይ መስተዋት በሰወስት የጭነት መኪኖች ተጭኖ፥ የጭነት መኪኖቹ በጭነት አዉሮፕላን ተጭነዉ አፍሪቃ ገብተዋል። ፕሬዝዳቱ በሚያርፉ፥ በሚያልፉ፥ በሚናገሩበት፥ ሥፍራ ሁሉ የራዲዮ ሞገድን የሚያፍኑ፥ ኬሚካዊና ባዮሎጂያዊ ንጥረ ነገሮችን የሚከላከሉ የኤክስሬይ መሳሪያዎች፥ ሌሎችም ለብዙዎቻችን እንግዳ የሆኑ ብዙ መሳሪዎችና ከነባለሙያዎቻቸዉ አፍሪቃ ሠፍረዋል።

ሁሉ በሁሉ ዋሽግተን ፖስት እንደዘገበዉ የአፍሪቃ-አሜሪካዊዉን ፕሬዝዳንትና የሚመሩትን ቡድን ደሕንነት ለመጠበቅ ሲያንስ ስልሳ ሚሊዮን ሲበዛ መቶ ሚሊዮን ዶላር ወጥቷል።ብቻ ብዙዎቹ አፍሪቃዉን «ዌልካም ሚስተር ፕሬዝዳት አሉ።» ጎሬ ደሴት-ሴኔጋል።

ምናልባት የሚሼል ኦባማ ቅድምያት ወይም ቅም-አያት በዚሕ በኩል ካለፉ-በሕይወት አሜሪካን ለመርገጥ ከታደሉ አንዱ ነበሩ።አዉሮጳዉያን አፍሪቃዉያንን በባርነት እየተፈነገሉ ያኔ-አዲሱ ዓለም ይሉት ወነበረዉ አሜሪካ ያሻግሩ የነበሩበት ሥፍራ ነዉ።ጎሬ።

ፕሬዝዳንት ኦባማ ያቺን የአፍሪቃዉያን ማከማቻ፥ በመርከብ ማጨቂያ ደሴትን ሲጎበኙ-ስሜታቸዉ እንደ ሰዉ ሐዘን፥ እንደ አፍሪቃ-አሜሪካዊ ፖለቲከኛ ፀፀት፥ እንደ ትልቅ ሐገር ፕሬዝዳት ለሰባዊ መብት መከበር ይበልጥ የመታገል እልሕ ብጤ ነበር።ቅይጥ።

«ለኔ ባጠቃላይ ከዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ያሉ ሐገራትን መጎብኘት ትልቅ ትርጉም አለዉ።ግን በግልፅ እንደሚታወቀዉ፥ እንደ አፍሪቃ አሜሪካዊ ፕሬዝዳት ይሕን ሥፍራ መጎብኘት መቻሌ ሠብአዊ መብትን ለማስከበር በመላዉ ዓለም የሚደረገዉን ትግል ለማጠናከር ከፍተኛ ብርታት ይሰጠኛል።»

U.S. President Barack Obama and first lady Michelle Obama (L) are greeted by an honor guard at the Presidential Palace June 27, 2013 in Dakar, Sengal. Obama's trip, his second to the continent as president, will take him to Senegal, South Africa and Tanzania. REUTERS/Gary Cameron (SENEGAL - Tags: POLITICS)

Barack Obama Senegal Afrika-Reise Dakar

ለሠብአዊ መብት መከበር-ያዉም በመላዉ ዓለም እታገላለሁ ማለታቸዉን ሁሉም አፍሪቃዊ አላመኗቸዉም። እንዲያዉም ታላቁን የዓለም የሠላም ሽልማት ኖቤልን ተሸላሚዉ የታላቂቱ ሐገር መሪ የዓለምን ሠላም፥ ፍትሕ ርትዕትን አለከበሩም ባይ ተቃዋሚዎችም ገጥመዋቸዋል።በተለይ ስዌቶ-ደቡብ አፍሪቃ መቶዎች በሰልፍ ዉግዘት ነዉ-የተቀበሏቸዉ።

እዚዉ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ ባልደረባችን ሉድገር ሻዶምስኪ እንደዘገበዉ ሠልፈኛዉ የኦባማን ዝነኛ መፈከር-«አዎ እንችላለን-የስ ዊካን»ን ገልብጦ፥ «የለም አትችልም፥ኖ ዩካንት» እያለ ተቃዉሟቸዋል።ኦባማ ሥልጣን ሲይዙ እንደዛቱት የዃንታናሞ ማጎሪያ ጣቢያን አለመዝጋታቸዉ፥ የአሜሪካ ጦር አፍቃኒስታን፥ ፓኪስታን እና ሌሎች ሥፍራዎች ድሮን በተባለዉ ሰዉ አልባ አዉሮፕላን ሠላማዊ ሰዎችን መግደሉን ሠልፈኛዉ በሰልፍ አዉግዞታል።


ፖሊስ በተነዉ።ለደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝዳት ለጄኮብ ዙማና ለብዙ ደቡብ አፍሪቃዉያን ግን ኦባማ-ማንዴላን ባይሆኑ ማንዴላን ብጤ ናቸዉ።የየሐገራቸዉ የመጀመሪዎቹ ጥቁር መሪዎች።የጥቁር ሕዝብ የእኩልነት አብነቶች።

«ሁለታችሁም የየሐገራችሁ የመጀመሪያ ፕሬዝዳቶች በመሆናችሁ በታሪክ ተቆራኝታችኋል።በዚሕም ምክንያት አፍሪቃ ዉስጥ እና ከአፍሪቃ ዉጪ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በፊት ይጨቆኑ የነበሩ አፍሪቃዉያንን ሕልም እዉን የማድረግ ሐላፊነትን ተሸክማችኋል።»

አሉ ዙማ።ኦባማ ደቡብ አፍሪቃን ሲጎበኙ ሆስፒታል ተኝተዉ የሚያጣጥሩትን ማንዴላን አላዩዋቸዉም። ማንዴላ ታስረዉበት የነበረችዉን የሮቢን ደሴት የእስር ክፍላቸዉን ግን ጎብኝተዋል።የማንዴላ ቤተ-ሰቦችን አጋግረዋል።ከሁሉም በላይ ለማንዴላ ያላቸዉን አድናቆትና ክብር ዳካር ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ገልፀዋል።

U.S. President Back Obama walks from Section B, prison cell No. 5, on Robben Island, South Africa, Sunday, June 30, 2013. This was former South African president Nelson Mandela's cell, where spent 18-years of his 27-year prison term on the island locked up by the former apartheid government. (AP Photo/Carolyn Kaster)

ማንዴላ ከታሠሩበት ቤትእዉቁን የጥቁሮች የነፃነት አርበኛ እንደሩቅ መሪ በመደበኛ ሥማቸዉ ሳይሆን እንደ ቅርብ ሰዉ የማንዴላ ጎሳ አባላት በሚጠሩበት ሥም ማንዴላ ብለዉ አወደሱ።ጀግናዬ-ብለዉ አደነቋቸዉም።

«ማዲባን የማግኘትና የማነጋገር እድል አጋጥሞኝ ነበር።እና በግሌ ጀግናዬ ናቸዉ።በዚሕ ረገድ እኔ የተለየሁ ነኝ ብዬ አላምንም።እንደሚመስለኝ የዓለም ጀግና ናቸዉ።ካለፉ እና ቢያልፉ ሁላችንም የምናዉቀዉ አንድ ነገር ያለ ይመስለኛል።የመርሕ፥ ምግባር ዉርስ-ቅርሳቸዉ ለዘመናት እንደፀና እንደሚኖር።»

ያም ሆኖ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ደቡብ አፍሪቃን የጎበኙት የማንዴላ ሐገር በመሆኗ ብቻ አይደለም።ሴኔጋልን የጎበኙት የሴዳር ሴንጎር ወይም አፍሪቃዉያን ይታገቱ፥ይገረፉ፥ ይገደሉ፥ ይጋዙ፥ የነበሩባት ሐገር በመሆንዋ አይደለም።ታንዛንያን የሚጎበኙት የጁሊየስ ኔሬሬ ሐገር በመሆንዋ አይደለም።

ጉብኝታቸዉ ግላዊ ቢሆን ኖሮ ከአባት-አያት ቅድመ አያቶቻቸዉ፥ ከወድም-እሕቶቻቸዉ ሐገር ኬንያ ይልቅ ሰወስቱን ሐገራት ባለስቀደሙም ነበር።ጉብኝታቸዉ ፖለቲካዊ ከፖለቲካዊም ፕሬዝዳንታዊ ነዉ።ለጉብኝቱ የመስተዳድራቸዉ መመዘኛ ደግሞ ሰወስቱ ሐገራት ከአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሐገራት የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የመሠረቱ፥ የየሕዝባቸዉን መብት ነፃነት በሚያከብሩ፥ በሕዝብ ድምፅ በተመረጡ ፖለቲከኞች የሚመሩ በመሆናቸዉ ነዉ።እና የተረጋጋ የምጣኔ ሐብት ዕድገት ያስመዘገቡ ሐገራት ሥለሆኑ።

U.S. President Barack Obama delivers remarks at the University of Cape Town, June 30, 2013. REUTERS/Jason Reed (SOUTH AFRICA - Tags: POLITICS EDUCATION) / Eingestellt von wa

ኬፕ ታዉን ዩኒቨርስቲ

ጥቅል አፍሪቃም ኦባማ ኬፕታዉን ላይ እንደመሠከሩት እየተንቀሳቀሰች ነዉ።

«አፍሪቃ እየተንቀሳቀሰች መሆኑ አያጠያይቅም።»

አዎ አፍሪቃ እየተንቀሳቀሰች ነዉ።እንቅስቃሴዉ ወደ ጥፋትም፥ስጋትም፥ ወደ ልማት-እድገትም መሆኑ እንጂ ተቃርኖዉ።ጥር ሁለት ሺሕ ዘመኝ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን በይፋ በተረከቡ በመንፈቁ የጎበኟት ግብፅ አፍሪቃም ተባለች አረብ ያኔ የነበረችዉ አይነት አይደለችም።

የግብፅ ሕዝብ በሁለት ሺሕ አስራ-አንድ የጀመረዉ ትግል የረጅም ዘመኑን አምባገነን ገዢ ሁስኒ ሙባረክን ከሥልጣን ሲያስወግድ ሐገሩን ወደ ዲሞክራሲ፥ ፍትሕ፥ ነፃነት አቅጣጫ የማንቀሳቀሱ ጅምር ነበር።ቱኒዚያዎች ጀምረዉት ግብፆች የደገሙት ሕዝባዊ አብዮት ተደንቆ፥ ተወድሶ፥አጓጉቶ ሳያበቃ የግብፅ ፖለቲከኞች የተነከሩበት እሰጥ አገባ ወደፊት የተንቀሳቀሰችዉን ሐገር የኋላት እያነዳት፥ ለደም አፋሳሽ ግጭት እየጋለባት ነዉ።

የሊቢያ ሕዝባዊ አብዮት ገና ከጅምሩ ወደ በጠምንጃ ዉጊያ ተቀይሮ፥ የምዕራባዉያን ጦር ሐይልን ጣልቃ አስገብቶ የረጅም ጊዜ መሪዋን ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ጨምሮ በሺየሚቆጠሩ ዜጎቿን ሕይወት፥ በቢሊዮን የሚቆጠር ሐብት ንብሯትን አጥፍቶ ሐብታሚቱን ሐገር የዛሬም የዉር ድብር ያላጋታል።

የሊቢያ መዘዝ ለማሊ ተርፎ ያቺን የጥንታዊ እዉቀት መከማቻ፥ ታሪካዊት ሐገር፥ ያቺን የሙዚቃ መቀኛ፥ መፈሰሻ ምድርን አንኩቶ-ጥሏቷል።የድሮ ዜጎችዋ ለነፃነት ከተፋሏማቸዉ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዎችዋ እጅ ዶሏታል።አፍሪቃ፥ ኦባማ እንዳሉት እየተንቀሳቀሰች ነዉ።በሁለት ሺሕ ዘጠኝ ለሃያ-ሁለት ሠዓታት የጎበኟት ጋና እና አሁን የጎበኙና የሚጎበኟቸዉ ሐገራት አፍሪቃ በበጎ አቅጣጫ የመንቀሳቀሷ አብነቶች ሊሆኑ ይችላሉ።ከናይጀሪያ እስከ ኢትዮጵያ ግን ብዙ የሚነገርለት የምጣኔ ሐብት እድገት ብዙ በሚወራበት ሙስና፥ የመብት ረገጣ እና አፈና እንደተበተበ ነዉ።ሱዳኖች ሠላም ናቸዉ ማለት ስሕተት ነዉ።ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፐብሊክ፥ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፥ እና ሶማሊያ ከማሊ ቢብሱ እንጂ እይሻሉም።የዓለም ብቸኛ ልዕለ ሐያል ሐገር መሪ ይሕን አላጡትም።መፍትሔ የሚሉትም አላቸዉ።አዲስ ትብብር ይሉታል።

«አሜሪካ በአፍሪቃ ጉዳይ ለብዙ አስርታት ተሳትፋለች።አሁን ግን ድጋፍ፥ የዉጪ ርዳታ ከመስጠት ወደ አዲስ ትብብር እየተሸጋገርን ነዉ።የአሜሪካና የአፍሪቃ አዲስ ወዳጅነት።ችግሮቻችሁን የማስወገድ እና የማደግ አቅማችሁን በማዳባር ላይ ያተኮረ የእኩያሞች ወዳጅነት።ጥረታችን ኑሯችንን በሚቀርፁ በሰወስት መስኮች ላይ ያተኩራል።(በሥራ) ዕድል፥ በዲሞክራሲ እና በሠላም።»

ለዚሕ ስኬት የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን የጀመሩትና AGOA በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የዩናይትድ ስቴትስና የአፍሪቃ የንግድና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ትብብርን ለማራዘምና ለማጠናከር ኦባማ ቃል ገብተዋል።ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ የኤች አይ ቪ ኤድስ ሥርጭትን ለመከላከል የመደቡትን ገንዘብና መርሐ-ግብር ይቀጥሉበታልም።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት የአፍሪቃ ሐገራት የኤሌክትሪክ ሐይል ምንጭን ለማስፋፋት ለሚያደርጉት ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ ሰባት ቢሊዮን ዶላር እንደምትረዳ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝዳት ኦባማ ዘግይተዉም ቢሆን አፍሪቃን መጎብኘታቸዉ በርግጥ ለሁለቱም ወገኖች ጥሩ ነዉ። የገቡትን ቃል ገቢር ማድረግ ከቻሉ ደግሞ ሲበዛ ጥሩ ነዉ።ቃሉ ገቢር ሆነም-አልሆነ ቃል የተገባና ተስፋዉ የተጣለዉ ምጣኔ ሐብቷ አለቅጥ የጠረቃዉ ቻይና የአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሐገራት ምጣኔ ሐብትን በጠንካራ ጥርስ-ጥፍሯ መቧጠጥ ከጀመረች በኋላ መሆኑ ነዉ ለአሜሪካኖች-አሳሳቢዉ ሐቅ።

የቀድሞዉ የቻይና ፕሬዝዳት ሁ ጂንታኦ አፍሪቃን አምስቴ ጎብኝተዋል።ያሁኑ ፕሬዝዳት ሺ ጂፒንግ ሥልጣን በያዙ ማግስት ከሞስኮ ቀጥሎ የጎበኙት አፍሪቃን ነዉ።ታንዛኒያ፥ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና ደቡብ አፍሪቃ።ዩናይትድ ስቴትስ በ2011 ከአፍሪቃ ጋር ያደረገችዉ የንግድ ልዉዉጥ ሃያ-አንድ ቢሊዮን ዶላር ነዉ።የቻይና የንግድ ልዉዉጥ ባጭር ጊዜ ከአሜሪካ ጋር ተስተካክሏል።በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ደግሞ አሜሪካን ልትበልጥ ምንም አልቀራት።ሕንድ፥ ብራዚል፥ ቱርክና ሌሎችም የአፍሪቃን ገበያና ጥሬ ሐብትን ለማግኘት እየተራኮቱ ነዉ።


አፍሪቃዉያን ከዘየዱ ከፉክክር ሽሚያዉ ብዙ መጠቀማቸዉ አይቀርም።ኦባማም ካንገትም ይሁን ካጀት ይሕን ሐቅ አልካዱትም።እንዲያዉም አፍሪቃዉያንን መክረዋል።

«አፍሪቃ ከቻይና፥ ከብራዚል፥ ከሕንድና ቱርክ ትኩረት ማግኘቷ በደስታ ነዉ የምቀበለዉ።ይሕ ያሰጋናል የሚል ስሜት የለኝም።ጥሩ ነገር ይመስለኛል።ለአፍሪቃ አስፈላጊዉ ጉዳይ እነዚሕ ግንኙነቶች ለአፍሪቃ መጥቀማቸዉን ማረጋገጥ ነዉ።»

አፍሪቃዉያን ፖለቲከኞች በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት ለምሥራቅ-ምዕራብ ሐያላን ማደራቸዉ ለአፍሪቃ ሕዝብ በጦርነት፥ በረሐብ፥ በሽታ ከማለቅ፥ መሰደድ ሌላ ያተረፉትለት የለም።የዛሬዎቹ የአፍሪቃ መሪዎች ቤጂንግ-ዋሽግተኖች ከሚመሩት ከብሪክስ፥ እና ከቡድን ሰባት ተቀናቃኞች ጋር መሻረካቸዉን ለሕዝባቸዉ ጥቅም ካላዋሉት ካለፈዉ ጥፋት አልተማሩም።

ነጋሽ መሐመድ

ሂሩት መለሰAudios and videos on the topic