የኦባማ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት | ዓለም | DW | 20.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኦባማ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚያደርጉት የአራት ቀናት ጉብኝት ዛሬ ቴልአቪቭ ገቡ። በዚሁ ወቅት የእሥራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና መላው የመንግሥት ካቢኔ ለአሜሪካዊው ፕሬዚደንት አቀባበል አድርገዋል።

ፕሬዚደንት ከሆኑ በኋላ አሁን እሥራኤልን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጎበኙት ባራክ ኦባማ በእሥራኤል እና በፍልሥጤማውያን መካከል ካለፉት ብዙ ዓመታት ወዲህ ወደፊት መራመድ የተሳነውን የመካከለኛ ምሥራቅ ድርድር ማነቃቃት የሚቻልበትን ሀሳብ ያቀርባሉ ተብሎ አይጠበቅም። በዚህ ፈንታ የኦባማ እና የእሥራኤል ባለሥልጣናት ውይይት በተለይ ላካባቢው ትልቅ ስጋት ደቅኖዋል በሚባለው በኢራን የአቶም መርሀግብር እና በሶርያ ውዝግብ ላይ እንደሚያተኩር ነው የሚጠበቀው።
ፕሬዚደንት ኦባማ ከእሥራኤል ቀጥለው ወደ ፍልሥጤማውያን ራስ ገዝ አስተዳደር እና ወደ ዮርዳኖስ ያመራሉ።
የዩኤስ አሜሪካ መንግሥት ምክትል ቃል አቀባይ ጆሽ ኧርንስት ፕሬዚደንቱ ጉዞ ሊጀምሩ ጥቂት ጊዜ ሲቀራቸው እንዳስታወቁት፡ ኦባማ በዚሁ ጉዟቸው ተጨባጭ ዕቅድ ይዘው አልተጓዙም።
« እርግጥ፡ ፕሬዚደንቱ ተጨባጭ የሰላም ዕቅድ ይዘው አይደለም የሚሄዱት። ሁለቱ ወገኖች፡ ማለትም፡ ፍልሥጤማውያኑ እና እሥራኤላውያኑ፡ የሰላም ስምምነት የሚደረስበትን መንገድ ቢከተሉ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ብለው ነው የሚያስቡት። »


አሜሪካዊው ፕሬዚደንት በእሥራኤል፡ በምዕራባዊ ዳርቻ እና በዮርዳኖስ የሚያደርጉትን ጉብኝት ለእሥራኤል ያላቸውን ድጋፍ ለማረጋገጫ ሊጠቀሙበት ማሰባቸውን ነው ጆሽ ኧርንስት የገለጹት።
« ኦባማ በዚሁ ቆይታቸው ከእሥራኤል ሕዝብ ጋ ለመነጋገር ፅኑ ፍላጎት አላቸው። ጉብኝቱ ለኦባማ ያለፈውን ዓመት በሙሉ ስንወያይበት የነበረውን፡ ማለትም፡ ለእሥራኤል ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት እና የሕዝቧንም ደህንነት ለማስጠበቅ ቆርጠው መነሳታቸውን ለማረጋገጥ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። »
ምንም እንኳን የፕሬዚደንት ኦባማ መስተዳደር ለእሥራኤል ሰፊ የጦር እና የፊናንስ ርዳታ ቢያደርግም፡ ፕሬዚደንቱ ለእሥራኤል የሚያደርጉት ድጋፍ በቂ አይደለም በሚል አዘውትሮ ከእሥራኤላውያን እና ከአሜሪካውያኑ የሬፓብሊካን ፓርቲ አባላት ወቀሳ ሲሰነዘርባቸው ይሰማል። በተለይ ኦባማ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን እአአ መጋቢት 2010 ዓም በኋይት ሀውስ ተቀብለው ላጭር ጊዜ ካነጋገሩ በኋላ ከእሥራኤላዊው ባለሥልጣን ጋ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑበት ርምጃቸው ወቀሳውን አጠናክሮታል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የሁለቱ ባለሥልጣናት ግንኙነት የተቀዛቀዘ እንደመሆኑ፡ የእሥራኤል መንግሥት በተያዘው የፍልሥጤማውያን ግዛት የጀመረውን የሠፈራ መርሀግብር ኔታንያሁ እንዲያስቆሙ ለማግባባት የጀመሩትን ጥረት ማቋረጥ ግድ ነው የሆነባቸው። እና ይኸው ያሁኑ ጉብኝታቸው ከኔታንያሁ ጋ የተፈጠረውን የሀሳብ ልዩነት ለማስወገጃም ሊረዳ እንደሚችል የስድስት የእሥራኤል ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች አማካሪ የነበሩት አሮን ዴቪድ ሚለር ይገምታሉ።
« ይህ ፕሬዚደንቱ ብዙ ጉዳዮችን ለማስተካከያ፡ አለመግባባቶችን ለማስወገድ፡ በእሥራኤል አኳያ ጥላቻ እንዳላቸው እና ከእሥራኤል ጋ ስሜታዊ ግንኙነት የላቸውም በሚል የሚሰሙ አስተያየቶችን ለማስወገድ የሚደረግ ጥረት ይመስለኛል። »

ይህ በመሆኑም አሁን በኔታንያሁ ላይ የሠፈራውን ግንባታ እንዲያስቆሙ እንደገና ግፊት ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ኦባማ ከእሥራኤላዊው ጠቅላይ ሚንስትር በሚያደርጉት ውይይት ላይ ላካባቢው ስጋት ደቅኖዋል የሚባለው በኢራን አቶም መርሀ ግብር ሰበብ የተፈጠረው ውዝግብ ሰፊ ቦታ መያዙ አይቀርም። በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ አለመስራቱን ኔታንያሁ ማጉላታቸው አይቀርም። ለችግሩ በዲፕሎማቲኩ ዘዴ መፍትሔ የማይገኝለት ከሆነ፡ አሮን ዴቪድ ሚለር እንደሚሉት፡ አሜሪካዊው ፕሬዚደንት ወታደራዊ ርምጃ ማሰላሰል ሊገደዱ ይችሉ ይሆናል።
ኦባማ እና ኔታንያሁ ያነሱዋቸዋል የሚባሉት የሶርያ ጊዚያዊ ሁኔታ እና የግብፅ ውዝግብ ዩኤስ አሜሪካ ለመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ድርድር ትኩረት እንዳትሰጥ ያም ቢሆን ግን፡ የእሥራኤል ፕሬዚደንት ሺሞን ፔሬስ የመሳሰሉ ፡ ተቀናቃኞቹ ፍልሥጤማውያን እና እሥራኤላውያን የኦባማ ጉብኝት የሰላሙን ሂደት፡ ማለትም፡ እሥራኤል እና ፍልሥጤማውያን ጎን ለጎን ሁለት መንግሥታት መሥርተው መኖር የሚችሉበት ሊያነቃቃ የሚችል መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል የሚል ትፅቢት እንዳላቸው ገልጸዋል። በዋሽንግተን ዲ ሲ የብሩኪንግስ ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ኻሊድ ኤልጂንዲ አስተያየት መሠረት፡ ለራስ ገዙ የፍልሥጤማውያን ግዛት የሰላሙ ሂደት መነቃቃት ወሳኝ ትርጓሜ አለው።
« የፍልሥጤማውያን አመራር የፖለቲካ ህልውና የሰላሙ ሂደት በሁለት መንግሥታት ምሥረታ ላይ በሚያስገኘው የመሻሻል ርምጃ ላይ ጥገኛ ነው። »
በዚሁ ረገድ ዩኤስ አሜሪካ ገንቢ ታታሪነት እንድታደርግ ፍልሥጤማውያን ፕሬዚደንት ማህሙድ አባስ ከብዙ ጊዜ ወዲህ ጠብቀዋል። ይሁንና፡ ፕሬዚደንት ኦባማ በመጀመሪያ ሥልጣን ሲይዙ የነበራቸው ተስፋ አሜሪካዊው የመካከለኛ ምሥራቅ ልዑክ ጆርጅ ሚቼል እአአ ግንቦት 2011ዓም ሥልጣናቸውን ከለቀቁ ወዲህ ደብዞ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ሂደት በፖሊሲያቸው ውስጥ ወደኋላ ተገፍቶዋል። ከዚህ ሌላም፡ እሥራኤላዊው የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች አማካሪ አሮን ዴቪድ ሚለር እንደሚሉት፡ እሥራኤላውያን እና ፍልሥጤማውያን ራሳቸው ለሰላሙ ድርድር እስካልቆሙ ድረስ በወቅቱ በይበልጥ በሀገር ውስጥ ጉዳዮች የተጠመዱት የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ኦባማ ብዙም ሊለውጡት የሚችሉት ነገር እንደማይኖር ገምተዋል።

ክሪስቲና ቤርግማን/አርያም ተክሌ
ተክሌ የኋላ


Audios and videos on the topic