የኦባማ አዲስ መርሕ፦ የአለም አሮጌ ችግሮችና አለም የሚጠብቀዉ | ዓለም | DW | 26.01.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኦባማ አዲስ መርሕ፦ የአለም አሮጌ ችግሮችና አለም የሚጠብቀዉ

የኦባማ ስብዕና፣ ፅናት፣ የትልቂቱን ሐገር ነባር ታሪክ የመለወጣቸዉ ብቃት፣ የራዕያቸዉ ብስለት ያስደሰተዉ፣ የጥረታቸዉ በጎ አስተምሕሮት ያነቃቃዉ

default

ኦባማ ከመጪዉ ትዉልድ ጋር

የአለም ብቸኝኛ ሐያል፣ ትልቅ ሐገር ትልቅ አመራር በመለወጡ እፎይታ፥ ደስታ፣ እርካታዉን ያልገለጠ፣ ለዉጡ የአለምን ችግሮች ለማቃለል-እንዲረዳ ተስፋ ያላደረገ፣ ያልፀለየ ሕዝብ የለም።ለአዲሱ መስተዳድር አዲስ መርሕ ገቢራዊነት ድጋፍ-እገዛዉን ለመለገስ ቃል-ያልገባ ፖለቲከኛ-ዲፕሎማት የለም።ካለም-ቢያንስ እስከ ዛሬ በይፋ አልተናገረም።የፖለቲከኛ-ዲፕሎማቶቹ ቃል፣ ለኦባማ የ«ለዉጥ-ይቻላል» ሰናይ መርሕ ገቢራዊነት ጥሩ ግብአት፣ለተራዉ ሰዉ ተስፋ-ፀሎት ስምረት ደግ ምልክት ይሆን ይሆናል።የአለም እዉነት-ሒደት፣ ልምድ፣ የጠባቂነቱ ለከት እጦት የግባት-ምልክቱን ጥሩ-ደግነት እንዳይቀጨዉ ማስጋቱ-ነዉ ጭንቁ።እንዴት-ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
ድምፅ

እሳቸዉ ምናልባት ፖለቲከኛ ለመሆን ከወሰኑበት ጊዜ ጀምረዉ-አምነዉበት፣ከሐቻምና ጀምሮ ደግሞ ብዙ ጊዜ ብለዉት አስብለዉትም ነበር።
ድምፅ 1 (አዎ እንችላለን።)
ብዙዉ ግን የለም ሐብታምነቷ ፀጋ፥ አንጡራ-ሕዝቧ በነጭ መጤዎች በመገደል-በመነቀል፤ መጋዙ የግፍ ታሪኳ-የሚጠፋባት፣ የዲሞክራሲ የሰብአዊ መብት ቀንዲልነቷ-ሰናይ መርሕ በባሮች መሸጫ-መለወጫነቷ፣በጥቁሮች-መጨቆኛ-መገለያነቷ እኩይ ሐቅ-በሚበከልባት ትልቅ ሐገር-ዘንድሮ የሆነዉን ትልቅ ሁነት ከመሆኑ በፊት ይሆናል ብሎ መገመት እንኳን በርግጥ ከብዶት ነበር።

ግን ሆነ።ከመሆኑ አስደናቂት እኩል አስተምሕሮቱም እጅግ-ነዉ ይላሉ አሜሪካዊታ መምሕርት።
ድምፅ 2
«ለዚሕ ዕለት እንደርሳለን ብለን ጨርሶ አስበን አናዉቅም።አሁን ግን ጥቁር ወጣቶቻችን የሚያልሙትን እዉን ለማድረግ ማንኛዉንም ነገር ማድረግ እንደማይሳናቸዉ ልናስተምራቸዉ እንችላለን።»

ለአለም ሰላም፣ ለሕዝቦች ነፃነት የመሟገት፤ የመዋጋት አኩሪ ገድሏ፣ አለምን በማበጥ-በማበላለጥ-፣ሕዝብን በመግደል-ማስገድል መርኋ የሚጫጫባት፣ ደሆችን የመርዳት ደግነቷ፣በሐብታሞች በሚቀየስ ለሐብታሞች-ባደረ ሥርዓት በመመረቷ የሚደፈለቅባት ሐገር-የእስካሁን ታሪክ በርግጥ ተቀየረ።ታሪካዊን ለወጥ ለመረዳት አዋቂ-ምሑርነትን፤ የፖለቲካ፤ የእድሜ ብስለትን፣ አሜሪካዊነትንም አልጠይቀም። ወጣት ተማሪዎችም አሉት።
ድምፅ 3

«ታሪክ፥ እዚሕ ታሪክ ተሰራ።ታላቅ ለዉጥ፣ ከፍተኛ ተስፋ ነዉ።ከንግዲሕ አመፅና ግጭት አይኖርም።አዲስ ጅምር ነዉ።»

የደሐ ሐገር ደሐ፥ የጥቁር ሙስሊም መጤ፣ ልጅ ያመኑ-ያሉትን ለማድረግ ከሐብታም፣ ከነጭ፤ በፖለቲካ ብቃት፤ በልምድ ብዛት ስም ዝና ካተረፉ ተቀናቃኞቻቸዉ ጋር የመጋፈጣቸዉ ፅናት ያስደነቀዉ፣ የፍልስፍናቸዉ ጥልቀት፣ የአንደበታቸዉ ርቱዕነት፣ የግርማ ሞገሳቸዉ ግዝፈት የማረከዉ፥ ትልቂቱን ሐገር ለትልቅነት ባበቁት ትላልቅ በጎ ታሪኮችዋ ላይ ታላቅ ሰናይ ታሪክ ሲያክሉበት የማይደሰትበት ምክንያት በርግጥ የለም።
ድምፅ 4 (ሙዚቃ)

ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ በበሳል የፖለቲካ ፍልስፍናዉ፤ በጥልቅ ራዕዮ፣ በረጅም ጊዜ መርሁ፣ ሕዝብን የሚያማልል፣ በንግግር-ክሒል፣ በስብእናዉ ግርማ ሞገስ ሰዎችን የሚማርክ መሪ ምናልባት ከማንዴላ ሌላ አለም አላየም።እንደ ኩባንያ ስራ-አስኪያጅ ሥልጣናቸዉ እስካልተነካ፣ የሐገራቸዉ ጊዚያዊ ጥቅም እስካልተጓደለ ድረስ የበታች የበላዮቻቸዉን ጥፋት እንደደገፉ-በመምጣት መሔዳቸዉ ጥፋት ላዘነዉ፤ ወይም ለተሰላቸዉ አለም የኦባማ ስብዕና ራዕይ-መርሕ ጥሩ መፅናኛ፣ አዲስ ለወጥም ነዉ።

የኦባማ ስብዕና፣ ፅናት፣ የትልቂቱን ሐገር ነባር ታሪክ የመለወጣቸዉ ብቃት፣ የራዕያቸዉ ብስለት ያስደሰተዉ፣ የጥረታቸዉ በጎ አስተምሕሮት ያነቃቃዉ፣ ተስፋ ያሰነቀዉ ሕዝብ የጭፈራ-ቡረቃዉን ምዕራፍ አሁን አጠናቋል።የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽነር ፕሬዝዳት ሆዜ ማኑኤል ባሮሶ ባለፈዉ ማክሰኞ እንዳሉት ከጭፈራ-ቡረቃዉ- ማግስት አለም ድርጊት ይጠብቃል።
ድምፅ 5
«ዛሬ የአለም አይኖች በሙሉ በፕሬዝዳት ኦባማ ላይ ተተክለዋል።ነገ-ግን በጣም ባስቸኳይ ትልቁ ነገር ሁሉ የአለም ጉዳይ ነዉ።የእሳቸዉን ትኩረት፤ የኛንም ትኩረት የምትሻዉ አለም። እኛ እዚሕ አዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ያለነዉ ግሎባላይዜሽን የገጠመዉን ፈተና ለማስወገድ ከዩናይትድ ስቴትስና ከሌሎች ወዳጆቻችን ጋር ተባብረን ለመስራት ዝግጁ ነን።እኔ በግሌ የፕሬዝዳት ኦባማ መመረጥ ለአሜሪካ ወሳኝ የለዉጥ ክስተት ነዉ-ብዬ አምናለሁ።አሁን ደግሞ ለተቀረዉ አለም በጣም አስፈላጊ የለዉጥ መሠረት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ።

ባሮሶ እንዳሉት ኦባማ ለአመለም መሪዋ ሐገራቸዉ ጥሩ ሲሉ የሚያደርጉት ለአዉሮጳም ይተርፋል ነዉ-እምነቱ።አዉሮጳ በሐብቷ፣ ዘር ቋንቋ በመጋራቷ፥ ሥር በሰደደ ወዳጅነቷም አሜሪካ ጋር ለመተባበር ቀዳሚ፤ ተፈላጊ የመሆንዋን ያክል አሜሪካ ከሚታየዉ ለዉጥ ተጠቃሚ የመሆን ተስፋዋም የናረ ነዉ።

ደቡብ አሜሪካ-መናልባት በጉርብትና እስያ-መካከለኛዉ ምሥራቅ በሐብት፥ ስልታዊ ጥቅማቸዉ፣አዉሮጶችን ለመቀጠል-መሻማታቸዉ አይቀርም።አፍሪቃም ከሽሚያዉ መግቢያ ሰበብ አላጣችም።በርግጥም ከኬንያዊ አባት የሚወለዱት ኦባማ ለትልቂቱ ሐገር ትልቅ ስልጣን በመብቃታቸዉ በጣሙን ኬንያዊዉ በጥቂቱ አፍሪቃዊዉ መኩራት መደሰቱ-ተስፋ ማድረጉም አልቀረም።

ኩራት ደስታ ተስፋዉ ግን ሰዉነታቸዉን አስዘንግቶ-በከሐሌኩሉነት ሊያጃጅል፣ የቀድሞዉ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሳሊም አሕመድ ሳሊም እንዳሉት የዩናይትድ ስቴትስ መሪናተቸዉን አስዘንግቶ የአፍሪቃ-ወይም የአለም የሆኑ ያክል ሊያስወበራ አይገባም።ኦባማ በርግጥ ጠንካራ-ሰዉ፣ በሳል ፖለቲከኛ ናቸዉ።በቦን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ክርስቲያን ሐከ እንዳሉት ግን ተአምር ይሰራሉ ብሎ መጠበቅ ቂልነት ነዉ።
ድምፅ 6

«በኦባማ ላይ የተጣለዉ ተስፋና የሚጠበቀዉ እጅግ ከፍተኛ ነዉ።እሳቸዉ በወንዝ-ባሕር ላይ መራመድ እንደማይችሉ ግን በግልፅ መታየት አለበት።ተአምር ሊሰሩ ጨርሶ አይችሉም።»

ባሮሶ «ነገ» ባሉት ሮብ፣ «ፈጣን ትኩረታችን ይጠብቃል» ካሉት አለም-ኦባማ ያተኩሩበትን አለም ለአለም አሳይተዋል።መካከለኛዉና፥ ሩቅ ምሥራቅ።

የእስራኤል-ፍልስጤሞችን ግጭት ለማስወገድ የሚደረገዉን ጥረት እንዲያስተባብሩ በልዩ መልዕክተኛነት የተሾሙት ጆርጅ ሚቼል ግጭቶች የማይወገዱበት ምክንያት የለም ይላሉ።ሰዉ ሰራሽ’ ናቸዉና።የአፍቃኒስታን፥ፓኪስታን፣ ሕንዱ ልዩ መልዕክተኛ ሪቻርድ ሆል ብሩክም ተመሳሳይ አቋም ነዉ-ያላቸዉ።

ሶማሊያ በሰዉ ሰራሽ ግጭት፤ እልቂት፣ ፍጅት እንደዳከረች ጆርጅ ኤች ቡሽ፣ በቢል ክሊንተን፤ ክሊንተን በጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ፣ ቡሽ በኦባማ ተተኩ።ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990 ዉጊያ እንደገጠሙ የያኔዋ የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሱዛን ራይስ ለሽምግልና አስመራ-አዲስ አበባ ተመላልሰዉ ነበር።ከምልልሱ ባንዱ ራይስ ያሉት ያልጣማቸዉ ፕሬዝዳት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላሳ-አራት አመትዋ ሴትዮ-ምን ማድረግ እንዳለብኝ ልትነግረኝ ትሞክራለች በማለት ወርፏዋቸዉ ነበር።

ራይስ ፕሬዝዳት ክሊንተንን አጅበዉ ዩጋንዳን ሲጎበኙ-የዩጋንዳዉ ፕሬዝዳት ዩዌሪ ሙሳቬኒ እንግዶቻቸዉን ሲያመሰግኑ ከትንሿ ልጄ የሚያንሱት ዶክተር-ሱዛን ራይስ ብለዉ ብዙዎችን አስቀዉ ነበር።ራይስ በአስራ አንደኛ-አመታቸዉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሆነዉ ከአለም ዲፕሎማሲ ዳግም ሲቀየጡ ሶማሊያ እንደሾቀች፤ የኢትዮ-ኤርትራ ግጭትም እንደነበረ፤ ፕሬዝዳት ኢሳያስ፤ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ፣ ፕሬዝዳት ሙሳቬኒም በየነበሩበት ጠበቋቸዉ።ድንቅ ነዉ።

ራይስ ባለፈዉ ቅዳሜ-ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንደነገሩት ለሶማሊያ ሠላም ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ማዝመት ብዙም አስፈላጊ አይደለም።ኢትዮ-ኤርትራ ድንበር፤ ኤርትራ ጅቡቲ ጠረፍ፤ ሰሜን ዩጋንዳ፤ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ ዳርፉር፣ ቻድ፤ ሰላም የለም።ጊኒ በመፈንቅለ መንግሥት፤ ዚምባቡዌ በመፖለቲካ ቀዉስ ይተራመሳሉ።

አብዛኛዉ አፍሪቃ በአንባገነን፣ በአጭበርባሪዎች፤ በሙስና በላሸቁ ገዢዎች ተቀይዷል።አብዛኛዉ አፍሪቃዊ በረሐብ፣ በበሽታ ግጭት ያልቃል።ኦባማ በአበለ ሲመት ንግግራቸዉ አምባገነኖችን፣ በሙስና የላሻቁ ገዢዎችን ሲያስጠነቅቁ፣ «ማሳዎቻችሁ ሰብል-እንዲያፈሩ፤ የመጠጥ ዉሐ እንዲፈስላችሁ እንጥራለን» ሲሉ ከማንም በላይ ለአፍሪቃዉያን መሆኑ አያነጋግርም።ማለት በማድረግ ሲለካ ዘንቀ ብዙዉ የአፍሪቃ ችግር-የአፍቃኒስታን፣ ወይም የእስራኤል-ፍልስጤምን ቅንጣት አለመመዘኑ እንጂ-ድንቁ።
ጀርመናዊቷ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ከተናገሩት ግማሹን እንኳን ገቢር ቢያደርጉት የአለምን ችግር ማቃለል-አይገድም።
ድምፅ 7

«እስካሁን ከተናገሩት ግማሹን እንኳን ገቢር ካደረጉት ለመላዉ አለም አንድ ትልቅ እመርታ ነዉ-የሚሆን።በዚሕ ተስፋ ምክንያትም ከልቤ ተደስቻለሁ።»

የአለም የአሜሪካም ችግር-ዉስብስብ፤ ስር-የሰደደ ነዉ።ኦባማ ራሳቸዉ እንዳሉት ችግሩን ለማቃለል የአሜሪካ፣ የአለምም ሕዝብ፣ ፖለቲከኛ፣ ምሁር ባለሐብት ትብብር ያስፈልጋል።የአለም መሪዎች የትበብር ቃላቸዉን ማዥጎድጎዳቸዉ አልቀረም።ቃሉ-ከዲፕሎማሲ ሽገላ ባለፍ የምር ለመሆኑ ግን ምንም ማረጋገጪያ የለም።የኦባማ መርሕ-አዲስ ነዉ።አዲሱን መርሕ ገቢር የሚያደርጉበት አዲስ መዋቅር-አለምም አሜሪካም የላትም።አዲሱን መርሕ ባሮጌ መዋቅር፣ በአሮጌ ሥልት ተጠቅሞ-ስር የሰደደዉን አሮጌ ችግር እስከምን ማቃለል-ይችላል ነዉ-የከንግዲሑ ጥያቄ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Negash Mohammed

Qullen:DW,SPR (nur Ö-Töne),CNN,Wikipedia