የኦባማ ስንብት፤ የዓለም መሪዎች መልዕክት | ዓለም | DW | 21.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የኦባማ ስንብት፤ የዓለም መሪዎች መልዕክት

የፖለቲካ ተንታኞች  እንደሚሉት ደግሞ ኦባማ በርሊን ላይ ለሰበሰቧቸዉ ለጀርመን፤ ለብሪታንያ፤ለፈረንሳይ፤ ለስጳኝና ለኢጣሊያ መሪዎች ከነገሩት ይልቅ ካስተናጋኛቸዉ ከጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት ጋር በዝግ ያደረጉት ምክክር ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠዉ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:27
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
14:27 ደቂቃ

የኦባማ ስንብት፤ የዓለም መሪዎች መልዕክት

ከማረከሽ-ሞሮኮ እስከ አቴን፤ ከበርሊን እስከ ሊማ በተደረጉ ጉባኤ፤ ዉይይት፤ ጉብኝቶች ላይ የተካፈሉ ፖለቲከኞች በሙሉ ስለ ዶናልድ ትራምፕ ያወራሉ።አብዛኞቹ ሥጋታቸዉን፤ ጥቂቶቹ ምክራቸዉን፤ በጣም ጥቂቶቹ ተስፋቸዉን ያጋራሉ።ተሰናባቹ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት አንዱና ዋናዉ ናቸዉ።የአቴና፤ በርሊን፤ ሊማዉ ጉብኝት፤ጉባኤ ዓላማም ለኦባማ አንድም-ሰወስትም ነዉ።አንዱ ያዉ አይዟችሁ ተስፋ።ቀሪዎቹ ስንብት፤ምስጋና እና ማፅናናኛ ወይም ተስፋ።ሥልጣን አስረካቢዉ ቀሪዉን አይዞሕ የሚልበት አቅም፤ሒያጅ ሥለመጪዉ፤ ከሁሉም በላይ ተሸናፊ ሥለአሸናፊዉ ተስፋ የሚሰጥበት መሠረት፤-ምክንያት ማጠያያቁ እንጂ አነጋጋሪዉ።  

                           

ማራክሽ-ሞሮኮ የተጀመረዉ ጉባኤ ለሰወስተኛ ቀን ሲሰየም፤ ያዩ እንደዘገቡት፤ ብዙዎቹ ጉባኤተኞች ወደ ባብ ልግሊ አዳራሽ የገቡት በቅንቅልፍ እጦት እያዛጉ፤ በስጋት፤ ድንጋጤ እያወጉ ነበር።ምክንያት ዶናልድ ትራም አሸነፉ።እርግጥ ነዉ በየአለቆቻቸዉ በመታዘዛቸዉ፤ አበል ለማግኘት፤ ከሌላዉ ላለመነጠል ብቻ ብለዉ ከጉባኤዉ የተቀየጡት ወይም የልዕለ ሐያሊቱን ሐገር የተፅዕኖ በቅጡ የማዉቁት እንቅልፍ ማጣት፤ መደንገጥ ዓይደለም የአስደንጋጩን ዜና መስማታቸዉ፤ ከሰሙም መልዕክት ይዘቱን ከቁብ መቁጠራቸዉም አጠራጣሪ ነዉ።የዓየር ንብረት ለዉጥ የሚያስከትለዉን ጉዳት ለመቀነስ ከልብ ሊጥሩ፤ ሌሎች እንዲጥሩ ሊያስተባብሩ የተሰበሰቡት ግን  የንጉስ መሐመድ ስድስተኛ ማበረታቻን፤የፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድ ተስፋን፤ የዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን አደራን፤ የባለሙያዎች ማስጠንቀቂያን በሚያደምጡ ወይም በሚናገሩበት መሐል ከዩናይትድ ስቴትስ በሰሙት ዜና የማያስቡ፤የማይደነግጡበት ምክንያት የለም።

የተባበሩት መንግስታት ለጉባኤዉ የሰጠዉ ሥም ሰወስት፤ ዓላማዉ ግን አንድ ነዉ።የማሕበሩ አባላት 22ኛዉ ጉባኤ-ይላል አንዱ(COP22)፤ የኪዮቶዉ ሥምምነትን የሚወክሉ የማሕበር አባላት 12ኛ ጉባኤ(CMP12)-ሁለተኛዉ።ሰወስተኛዉ፤ የፓሪሱ ስምምነት

ተሳታፊዎች (CMA1) ጉባኤ ይላል።ዓላማዉ የዓለም የሙቀት መጠንን መቀነስ ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ የዓለምን የአየር ንብረት በመበከል ከዓለም ቀዳሚዋ ሐገር ናት፤በክለቱን ለመቀነስም በገንዘብ፤ በዲፕሎማሲ-ፖለቲካዉ፤ ሌሎችን በማስተባበር፤ የምታበረክተዉ ወይም ታበረክታለች ተብሎ የሚጠበቀዉ አስተዋፅኦ ከየትኛዉም ሐገር የበለጠ ነዉ።የዚች ሐገር የወደፊት መሪ ግን ከዚሕ በተቃራኒዉ መቆማቸዉን በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት ካንድ ጊዜ በላይ በግልፅ ተናግረዋል።

                                      

«የመጀመሪያዎቹ መቶ የሥልጣን ቀናት የድርጊት መርሐ-ግብሬ እንደሚከተለዉ ነዉ።የአየር ንብረት የድርጊት መርሐ-ግብርንና የዩናይትድ ስቴትስን የዉሐ አጠቃቀም ሕግን ጨምሮ፤ የኦባማን ልዩ መመሪያ ርምጃዎችን በሙሉ እናግዳለን።እሺ!!! ይሕን አስታዉሱ።የከሰል ኢንዱትሪዉን እናድናል።እመኑኝ ማዳን አለብን።እዚያ የሚሰሩትን ሰዎች አወዳቸዋለሁ።ጥሩ ሰዎች ናቸዉ።የፓሪሱን የዓየር ንብረት ስምምነትን እንሰርዛለን።ዩናይትድ ስቴትስ ለተባበሩት መንግስታት የሙቀት መከላከያ የምትከፍለዉን ገንዘብ እናቆማለን።»

ትራምፕ እና መርሐቸዉ ከማራክሽ በስተሰሜን የሜድትራኒያን ባሕርን ተሻግሮ አቴና ላይም ደምቆ ነበር።ሰዉዬዉ ለዓለም የዓየር ንብረት ስምምነት አይደለም ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ለኔቶም) እንደማይመለሱም በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት አስታዉቀዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ የዓለም ልዕለ ሐያል፤ የምዕራቡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጠባቂ፤ አራማጅም መሆናን ካስመሰከረችባቸዉ ትላልቅ ተቋማት አንዱ  የጦር ተሻራኪዎቹ ድርጅት  ነዉ።ትራምፕ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ለዚሕ ግዙፍ የጦር ድርጅት አባላት የምታደርገዉን ድጋፍ እንደሚቀንሱ መዛታቸዉ አባላቱን በተለይም የደካሞቹን አባላት ፖለቲከኞች አሳስቧል።

የትራምፕ መርሕ ባለፈዉ ሳምንት አቴን ላይ እንዳዲስ ርዕስ የጎላዉ ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ኦቦማ ሥጋቱን ለመቀነስ ወይም ሰጊዎችን ለማረጋጋት አቴናን በመጎብኘታቸዉ ነበር።«የላቀ ዲሞክራሲ

ለዓለም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ ለብሔራዊ ደሕንነታችንም ጥሩ ነዉ።ለዚሕ ነዉ የአሜሪካ የቅርብ ወዳጆች ዴሞክራሲያዊ ሐገራት የሆኑት፤ ለምሳሌ ግሪክ።የዴሞክራሲያዉያን ሕብረት በሆነዉ  ኔቶ የተባበርነዉም ለዚሕ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ በዲሞክራቶች ትመራ፤ በሪፐብሊካኖች እያንዳዱን አባል ከጥቃት መከላከልን ጨምሮ ከሰባ ዓመት በፊት ያደረገቻቸዉ ዉሎች እና የገባቻቸዉ ቃላት እንደተጠበቁ እንደሚቀጥሉ አምናለሁ።»

ያምናሉ ግን እርግጠኛ መሆን አይችሉም።የአቴናን ጨምሮ የሐገራቸዉን ታማኝ ወዳጅ ሐገራት ፖለቲከኞች ሥጋት ማስወገድ መቻላቸዉም አጠራጣሪ ነዉ።ተሰናባች መሪ ሥለ ተተኪዉ በተለይ  ሥለ ተቀናቃኙ መርሕ በርግጥኝነት መናገር አይቻልምና።

ኦባማ ደጋግመዉ እንዳሉት ዩናይትድ ስቴትስ የዲሞክራሲ ቀንዲል፤የዴሞክራሲያዊ ሥራዓት መስራች፤አራማጅ፤ ጠባቂም ናት።አቴና ላይም ደገሙት።የአሜሪካና የተከታዮችዋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሁሉን አቀፍ፤ ሁሉንም እኩል የሚያገለግል፣ ደካሞችን የሚደግፍም ነዉ እያሉ።

«ዴሞክራሲያችን ሁሉን አቀፍ በመሆኑ የተቸገሩ ሰዎችና ስደተኞች ወደ ሐገራችን እንዲገቡ እንፈቅዳለን።ለዚሕ  ግሪክ ዉስጥ ካለዉ የበለጠ ሌላ መረጃ ሊኖር አይችልም።የግሪክ ሕዝብ ለስደተኞች የሚያደርገዉ እርዳታ ዓለምን እያነቃቃ ነዉ።ይሕ ማለት እናንተ ብቻችሁን ሐላፊነቱን ተወጡ ማለት አይደለም።እነዚሕ ተስፋ የቆረጡ ሕዝቦች የሚፈልጉትን ድጋፍ የሚያገኙት አዉሮጳና የተቀረዉ ዓለም በጋራ ሲሰሩ ብቻ ነዉ።»

ትራምፕ ግን  ስደተኛ እንዳይገባ የታላቅ ሐገራቸዉን ድንበር በትልቅ ግንብ እዘጋለሁ ነዉ ያሉት።ሰዉን በሐይማኖቱ እየመረጡ ሙስሊም ወደ አሜሪካ እንዳይገባ አግዳለሁ ማለታቸዉ ነዉ-የሚታወቀዉ።አክራሪዉ ቱጃር ፖለቲከኛ ከዚሕ መርሐቸዉ ጋር እንዳይመረጡ ፕሬዝደንት ኦባማ ሕዝባቸዉን  መክረዉ፤ አሳስበዉም ሰሚ ማጣታቸዉ ሐቅ ነዉ። ትራምፕ ተመርጠዋል።የተመረጡት የኦባማ ፓርቲ ካቀረባቸዉ እጩ የተሻለ የሕዝብ ድጋፍ በማግኘታቸዉ ነዉ።

በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት አዋቂዉ ነጭ አሜሪካዊ ቀርቶ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ነጭ አሜሪካዊ ልጆች ሳይቀሩ ባደባባይ ደግፈዋቸዋል።ሮያል ኦክ በተባለዉ የሚቺጋን ግዛት ከተማ የሚገኝ የአንድ ትምሕርት ቤት ነጭ ተማሪዎች «እባክዎ ያንን ግንብ ይገንቡ» እያሉ ትራምፕን እየዘመሩ ሲማፀኑ ነበር።ተማሪዎቹ የ13 እና የ14 ዓመት ልጆች ናቸዉ።ሰዉዬዉም አሉ

                            

«የአሸባሪያዊነት፤ የአክራሪያዊነት እና የፅንፈኛዊነት ትዉልድ በየትምሕር ቤቶቻችሁ እየተሰራጨ ነዉ።»ሰዉዬዉ እና ደጋፊዎቻቸዉ ከየትኛዉም ዓለም በላይ የሐገራቸዉን ዜጎች በጣሙን ጥቁር፤ ክልስ፤የዉጪ ዝርያ ያላቸዉን፤ ሴቶችን ጭምር አስግተዋል።እዉቁ የፊምልና የመፅሐፍ ደራሲ ማይክል ሙር እንደሚለዉ ከነጩ ዉጪ ያለዉ አሜሪካዊ ቢሰጋ አይፈረድበትም።አሳማኝ ምክንያት አለዉ።«ከሐገሪቱ ሕዝብ 77 ከመቶዉ ጥቁር፤ ክልስ፤ሴቶችና ወጣቶች ናቸዉ።ከእንግዲሕ ሐገሪቱን

የሚመራዉ ሰላሳ አምስት ከመቶ የማይሞላዉ የአናሳዉ ተወካይ ነጭ መሪ ነዉ።ሥጋቱ ምክንያታዊ  ነዉ።»ፕሬዝደንት ኦባማ እና ተከታዮቻቸዉ ሕዝባቸዉን ለማሳመን ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም።ከእንግዲሕ የሚያደርጉት ጥረት ዉጤትን በርግጥ ጊዜ ነዉ መስካሪዉ።በርሊን ላይ ከአዉሮጳ መሪዎች ጋር ባደረጉት ዉይይት ግን አዉሮጶች በትራምፕ መርሕ አመራር ብዙ እንዳይሰጉ ከማፅናናት ባለፍ ትራምፕ ያሉትን ሁሉ ማድረግ እንደማይችሉ ለማሳመንም ሞክረዋል።

የፖለቲካ ተንታኞች  እንደሚሉት ደግሞ ኦባማ በርሊን ላይ ለሰበሰቧቸዉ ለጀርመን፤ ለብሪታንያ፤ለፈረንሳይ፤ ለስጳኝና ለኢጣሊያ መሪዎች ከነገሩት ይልቅ ካስተናጋኛቸዉ ከጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት ጋር በዝግ ያደረጉት ምክክር ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠዉ ነዉ።

ኦባማ ከየትኞቹም መሪዎች በላይ የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥትን የአመራር ብልሐት፤ጥንካሬና ብስለት ያደንቃሉ።«ጀርመናዊ ብሆን ኖሮ ምናልባት እሳቸዉን እመርጥ፤ እደግፍም ነበር።ይሕ ይርዳ-ይጉዳ አላዉቅም።»እርግጥ ነዉ የሁለቱ መሪዎች ወዳጅነት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ፤ እየጠናከረ፤ እየደረጀ የመጣ እንጂ መጀመሪያ ላይ አልነበረም።

ፕሬዝደንት ኦባማ በዘመነ-ሥልጣናቸዉ ጀርመን እና የፈረንሳይን ያክል ደጋግመዉ የጎበኙት ሐገር የለም።ኦባማ እስያን ይጎብኙ፤ አፍሪቃን፤ መካከለኛዉ ምሥራቅ ይሒዱ አዉሮጳ ይምጡ ኤርፎርስ ዋን የተባለዉ ልዩ አዉሮፕላናቸዉ ራምሽታይን-ጀርመን እሚገኘዉ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ሳይርፍ፤ ኦባም ሜርክልን ሰላም ሳይሉ አልፈዉ አያዉቁም።በዚሕም ሰበብ ኦባማ ከሜርክል ጋር ባደረጉት ዉይይት በዘመነ-ትራምፕ ዓለምን የመምራቱን ሐላፊነት ወይዘሮ ሜርክል ቸል እንዳይሉት ጠቆም ሳያደርጓቸዉ  አልቀረም።

ኒዮርክ ታይምስ የተባለዉ የአሜሪካ እዉቅ ጋዜጣም ሜርክልን «የምዕራቡ የለዘብተኛ (የሊብራል) አስተሳሰብ የመጨረሻ መከታ» በማለት አንቆለጳጵሷቸዋል።ዘ-ጋርዲያን የተሰኘዉ የብሪታንያ ጋዜጣ ደግሞ «የነፃዉ ዓለም መሪ» በማለት አወድሷቸዋል።ሜርክልን።ኦባማ ሜርክልን ከማድነቅ፤ማወደስ፤ ለመሪነቱ እንዲዘጋጁ ከመጠቆም ባለፍ «ተስፋዬ» ያሉት ግን ያዉ ተስፋ ነዉ።«ተስፋዬ  ሥልጣን የሚይዙት ተመራጭ ፕሬዝደንት ከሌሎች ጋር ተመሳሳይ ገንቢ ግንኙነት እንዲከተሉ ነዉ።ጥቅማችን እና እሴቶቻችን ተጠብቀዉ ከሩሲያ ጋር በምንተባበርባቸዉ መስኮች ይተባበራሉ፤ የዚያኑ ያክል እሴቶቻችን ሲቃረኑና ዓለም አቀፍ ደንቦችን ሲጥሱ ይቃወማሉ የሚል ነዉ።

ሊማ-ፔሩ ላይ የተሰየመዉ የእስያ-ፓስፊክ ሐገራት የምጣኔ ሐብት ትብብር (APEC) ጉባኤተኞች ከትራምፕና መርሐቸዉ እኩል በግልም፤ በወልም የተነጋገሩበት ርዕስ የለም።ከጃፓን እስከ ካናዳ፤ ከአዉትሬሊያ እስከ ደቡብ ኮሪያ ያሉ የዩናይትድ ስቴትስ ሐብታም ታማኝ ሐገራት የሚገኙበትን የንግድ ማሕበር አፈርሰዋለሁ ብለዋልና።የትንሽቲ ሐገር የኒዉዚላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ጆን ኬይ ሥጋት ፍራቱን ጥሰዉ «ጨዉ ለራስትል----» አይነት ነዉ ያሉት።

                               

«ተመራጩ ፕሬዝደንት

ትራምፕ የAPEC ቡድን ይታገዳል ወይም ይጠፋል በማለታቸዉ ምክንያት ከፍተኛ ጥርጣሬና ሥጋት አለ።በመሠረቱ APECን የመሠረት ነዉ የአካባቢዉን ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገትን እና ትብብር እንዲጠናከር ነዉ።የአካባቢዉ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት አስፈላጊ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ የነፃ ንግድን መቀየጥ ካልፈለገች ሌሎቹ ሐገራት እንደሚፈልጉት ትራምፕ ማወቅ አለባቸዉ።ያደርጉታልም።»

ፕሬዝደት ኦባማ አቴና እና በርሊን እንዳደረጉት ሁሉ የሊማ ጉባኤተኞችንም ለማረጋጋት ሞከረዋል።ፖለቲከኞች በምርጫ ዘመቻ ወቅት ያሉትን በዘመነ-ሥልጣናቸዉ ገቢር አያደርጉትም እያሉ።እሳቸዉም ፖለቲከኛ ናቸዉ።አብዛኛ የምርጫ ዘመቻ ቃላቸዉን ሳያከብሩ ሊሰናበቱ ሁለት ወር ቀራቸዉ።ስንብቱን ማክበር ገቢር ማድረጋቸዉ ግን ርግጥ ነዉ።ግድም።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic