የኦስትርያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የኦስትርያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት

የኦስትርያ ሕዝብ ሶሻል ዴሞክራቶቹን እና ወግ አጥባቂዎቹን ለመቅጣት ሲል እንደመረጣቸው የተገነዘቡት ሥዩሙ ፕሬዚደንት አሌግዛንደር ፋን ደር ቤለን ቅሬታ ያላቸውን መራጮችም ለመሳብ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:07
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:07 ደቂቃ

የአረንጓዴዎቹ እጩ ድል

በኦስትርያ ሁለተኛው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ባለፈው እሁድ ከተካሄደ ከ24 ሰዓታት የመጨረሻው የምርጫ ውጤት ትናንት ከቀትር በኋላ ይፋ ወጥቶዋል። በኦስትርያ ሁለተኛው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ባለፈው እሁድ ከተካሄደ ከ24 ሰዓታት የመጨረሻው የምርጫ ውጤት ትናንት ከቀትር በኋላ ይፋ ወጥቶዋል። የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እጩ አሌግዛንደር ፋን ደር ቤለን እስከ ትናንት ጥዋት ድረስ ይመሩ የነበሩትን ፣ ብዙዎች ያሸንፋሉ ብለው የጠበቁዋቸውን የቀኝ አክራሪው የኦስትርያ ነፃነታዊ ፓርቲ እጩ ኖርቤርት ሆፈርን በጠባብ የድምፅ ብልጫ በማሸነፍ አዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ሆነዋል። ይኸው ውጤት ወደቀኝ አዘንብላ የነበረችው ኦስትርያ በተቃራኒው ወደ ግራ መታጠፏን አሳይቶዋል።


ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ከሀያ ሲሆን ነበር አሌግዛንደር ፋን ደር ቤለን መራጮች በደብዳቤ የሰጡት ድምፅ ከተቆጠረበት ከኦስትሪያ ሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ማሸነፋቸው የተነገራቸው። በዚሁ ጊዜ ፣ ምንም እንኳን ፋን ደር ቤለን በጠባብ ድምፅ ብልጫ እየመሩ ቢገኙም፣ በአንፃራቸው የተፎካከሩት የቀኝ አክራሪው የኦስትርያ ነፃነታዊ ፓርቲ፣ «ኤፍ ፔ ኧ » እጩ ኖርቤርት ሆፈር ሊደርሱባቸው እንደማይችሉ ግልጽ ነበር። እና የሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ውጤቱን ሩብ ጉዳይ ለአስራ አንድ ሰዓት ላይ ይፋ ሊያደርግ ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ኖርበርት ሆፈር በፌስቡክ ገጻቸው ባስቀመጡት ጽሔፍ ሽንፈታቸውን ተቀብለዋል።
የኦስትርያ ሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ባወጣው ውጤት መሰረት፣ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ተሟጋቹ አሌግዛንደር ፋን ደር ቤለን 50,3%፣ የ«ኤፍ ፔ አ»ው እጩ ኖርበርት ሆፈር ደግሞ 49,7% የመራጭ ድምፅ አግኝተዋል።


እሳቸው እና ተፎካካሪያቸው ያገኙት ድምፅ ልዩነቱ ያን ያህል አለመሆኑን የተገነዘቡት የግራ መስመር ተከታይ ሊባሉ የሚችሉት የ72 ዓመቱ ፋን ደር ቤለን ከድላቸው በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር ላይ በቅድሚያ ኖርበርት ሆፈርን ካመሰገኑ በኋላ፣ በምርጫ ዘመቻው ወቅት በሀገሪቱ ትልቅ ልዩነት እንዳለ ለማጉላት የተደረገውን ሙከራ በመንቀፍ ይህን ለመቀየር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
« በብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወጡ ሀተታዎች በሀገራችን እንደገና ስለተቀሰቀሱ ልዩነቶች ጽፈዋል፣ እኔ ይህንን አላላጋንንም፣ እንዲጋነንም አልፈልግም። እነዚህ ልዩነቶች ድሮም የነበሩ ናቸው፣ ምናልባት ባለፉት ጊዚያት ልብ ብለን ስላልተመለከትን ይሆናል ያላየናቸው። ስለዚህ ወደፊት ሁኔታዎችን በቅርብ መከታተል እና መስራት ይኖርብናል። »
የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ አባል አሌግዛንደር ፋን ደር ቤለን ንግግራቸውን ባሰሙበት ጊዜ እንዳስታወቁት፣ የርዕሰ ብሔርነቱን ስልጣን በገለልተኛነት ለማከናወን ስለሚፈልጉ የፓርቲው አባልነታቸውን ሽረዋል። በአንጻራቸው በፕሬዚደንታዊው ምርጫ የተሸነፉት ተፎካካሪያቸው የ«ኤፍ ፔ ኧ» እጩ ኖርበርት ሆፈር ቢያሸንፉ ኖሮ አባልነታቸውን እንደማይሰርዙ ነበር ያስታወቁት። ሕዝቡ ሶሻል ዴሞክራቶቹን እና ወግ አጥባቂዎቹን ለመቅጣት ሲል እንደመረጣቸው የተገነዘቡት ፋን ደር ቤለን ቅሬታ ያላቸውን መራጮችም ለመሳብ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
« በዚች ሀገር ብዙ ሰዎች እንደሚገባው ትኩረት እንዳላገኙ እና እንዳልተደመጡ ይሰማቸዋል። ስለዚህ፣ ለራሱ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ፈንታ፣ ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ተጨባጭ ጥያቄዎች እና ስጋቶችም፣ እንዲሁም፣ በአንዳንድ ዜጎች ዘንድ ለሚታየው ቅሬታና ቁጣ ትኩረት የሚሰጥ ሌላ የውይይት ባህል እና ፖለቲካ መፍጠር ያስፈልገናል። »


በጥቂት መቶ የሚቆጠሩ ተማሪዎች የኦስትርያ «ኦባማ» የሚሉዋቸውን ፋን ደር ቤሌን በማሸነፋቸው ትናንት በመዲናይቱ ቪየና አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልጸዋል፣ ይሁንና፣ አንዱ ተማሪ እንዳመለከተው፣ አዲሱ ፕሬዚደንት በሀገር ውስጥ ፖለቲካ ላይ ለውጥ የማምጣት ተፅዕኖ እንደሌላቸው ያመለከተው አንዱ ተማሪ ፣ ወሳኙ የቀኝ አክራሪዎቹ ከፍተኛውን የሀገሪቱን ስልጣን አለመያዛቸው መሆኑን አስረድቶዋል። የወግ አጥባቂው ክርስትያን ዴሞክራት ፓርቲ ደጋፊ የባንክ ሰራተኛ ሲልቪያ ግሎግኒትሰር ከሁለቱ እጩዎች መካከል አንዱን መምረጡ ቀላል እንዳልነበረ ገልጸው፣ ለብዙዎች ስደተኞች በብዛት ወደሀገር የሚገቡበት ጉዳይ ወሳኝ እንደነበረ አስረድተዋል።
አሌግዛንደር ፋን ደር ቬለን ለዘብተኛ የስደተኞች አቀባበል ፖሊሲ እንደሚከተሉ ፣ የሀገሪቱ ድንበር ክፍት የሚሆንበትን አሰራር እንደሚደግፉ እና ከዓለም ጋ ጥሩ ግንኙነት ያላት፣ ለዓለም ክፍት የሆነች ኦስትርያን ማየት እንደሚሹ አስታውቀዋል። እንግዲህ፣ እጎአ የፊታችን ሰኔ ስምንት፣ 2016 ዓም ሁለት የስልጣን ዘመናቸውን አብቅተው የሚሰናበቱትን ሶሻል ዴሞክራቱን ሀይንስ ፊሸርን በመተካት የኦስትርያ ርዕሰ ብሔርነቱን ስልጣን የሚረከቡት ፋን ደር ቤለን የኖርበርት ሆፈር ደጋፊዎችን ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ስጋት እንዴት እንደሚቀንሱ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

ቤርንት ሪገርት / አርያም ተክሌ


ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic