የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሀገር ቤት እንገባለን አለ | ኢትዮጵያ | DW | 14.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሀገር ቤት እንገባለን አለ

በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታወቀ። ለሁለት ቀናት ከመንግስት ልዑካን ቡድን ጋር መነጋገሩን ገልጿል። ለተጨማሪ ውይይት የግንባሩ ልዑካን ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ። የኦዴግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሌንጮ ባቲ ጉዞው በቅርብ ጊዜ ይሆናል ብለዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታወቀ። ፓርቲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ግንቦት 3 እና 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን ቡድን ጋር መነጋገሩን አስታውቋል። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሌንጮ ባቲ «የእኛ ልዑካን እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት ልዑካን የመጀመሪያውን የፊት ለፊት ስብሰባ አድርገን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለውን የዴሞክራሲ እድገት እና ለውጦችን ከዳሰስን በኋላ ጠለቅ ባለ መልኩ እንዴት እንደሚጎለብቱ እና እንደሚሰፉ» ውይይት መደረጉን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ታይተዋል ያላቸው ማሻሻያ ርምጃዎች  «እንዲሰፉ፣ እንዲገለብቱና፣ ጥልቀት እንዲኖራቸው» ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን በኩል «በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉት ሁሉ ጋር ለመወያየትና ለመደራደር» ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት ለመኖሩ ማረጋገጫ ማግኘቱንም አክሏል።

«የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ላለፉት ስድስት ዓመታት አገር ቤት ገብቶ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ እና ለዴሞክራሲ እና ለዕድገት ኢትዮጵያዊ ውስጥ የሚደረገውን ትግል ለማገዝ የበኩሉን ሚና ለመጫወት እየጣረ የነበረ ድርጅት ነው" የሚሉት አቶ ሌንጮ ባቲ» ከመንግሥትም ጋር በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ግንኙነቶች" እንደነበሯቸው አስረድተዋል።

Karte Äthiopien englisch

 

በስደት የተመሰረተው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከወሰነ ከራርሟል። መጋቢት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በግንባሩ ፕሬዝዳንት በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራ አንድ የልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመደራደር ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ ሳይሳካለት ተመልሷል። በወቅቱ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ሌንጮ ለታ «ከመንግስት ጋር ውጪ ሆናችሁ ተነጋግራችሁ ያ ካለቀ በኋላ ነው ወደ ሃገር መመለስ የምትችሉት» የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አቶ ሌንጮ ባቲ ያኔ ያልሰመረው የሁለቱ ወገኖች ውይይት የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ባለው ፍላጎት አሁን ተሳክቷል ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። «በእኛ ግምገማ መንግስት ይኸ ፍላጎት እንዳለው ነው የገባን። ለማንኛውም መሬት ላይ በተግባር ሲተረጎም ነው የምናየው። አሁን ከመንግሥት በኩል ጥሩ ፍላጎት እና መልካም ፍቃድ እንዳለ ነው የተገነዘብንው» ሲሉ አክለዋል።

አቶ ሌንጮ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በኢትዮጵያ ጽ/ቤት ከፍቶ እንደሚንቀሳቀስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። «በሰላም አገራችን ገብተን ድርጅታችንን በሕጋዊ መልኩ አስመዝግበን ለሕዝብ ያለንን እይታ እና ፖሊሲ አቅርበን የዴሞክራሲያዊ ሒደት ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ነው» ሲሉም አክለዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከፍተኛ ልዑካን ወደ አዲስ አበባ ለተጨማሪ ውይይት እንደሚያቀኑ አቶ ሌንጮ ቢናገሩም መቼ እንደሚሆን ግን አልገለጹም። አቶ ሌንጮ «በቅርብ ጊዜ ነው የሚሆነው። በዚህ ቀን ነው ማለት አልችልም፤ አያስፈልግም። በቅርብ ጊዜ የሚከናወን ነው» ሲሉ ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ