የኦሮሞ ተቃውሞና የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም | ኢትዮጵያ | DW | 23.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኦሮሞ ተቃውሞና የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም

አዲስ አበባ እና አጎራባች ዞኖችን ለማስተሳሰር በኢትዮጵያ መንግስት የተነደፈውን እቅድ በመቃወም በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ መረጋጋቱን የመንግስት ኮምዩንኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። ሚኒስትሩ በተቃውሞ ወቅት 75 ሰዎች ተገድለዋል በማለት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች ያወጣውን ዘገባም አጣጥለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:22
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:22 ደቂቃ

የኦሮሞ ተቃውሞና የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም

በቃውሞ መዘዝ ለእስር የተዳረገየ ኦሮሚያ ቴሌቭዥን የዜና አንባቢ መኖሩን የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው ኮሚቴ (ሲፒጄ-በምሕፃሩ) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ጋዜጠኛ ፍቃዱ ሚርከና በምን ምክንያት እና የት እንደታሰረ አይታወቅም ያለው የሲፒጄ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋዜጠኛውን ከእስር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። የኢትዮጵያ መንግስት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የጋዜጠኛውን መታሰር አረጋግጠው ይሁንና እስራቱ ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ባወጣው መግለጫ ሣምንታትን ባስቆጠረው ተቃውሞ ቢያንስ 75 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን አስታውቋል።የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ተቃውሞውን ተከትሎ የሞቱ፤የቆሰሉ እና ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር አላስታወቀም።የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያወጣውን ዘገባ የኮነኑት አቶጌታቸው ረዳ የሟቾችን ቁጥር በማጣራት«አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ» ይፋ እንደሚደረግ ይናገራሉ።

ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የኢትዮጵያ መንግስት ተቃውሞውን ለማብረድ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል ሲሉ ይወቅሳሉ።የሒውማን ራይትስ ዎች የአፍሪቃ ክፍል ምክትል ኃላፊ ሌስሊ ሌፍኮው የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን «ሽብርተኛ» ሲል መፈረጁ እና ተቃውሞው በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የጦር ኃይል ማሰማራቱ ሁኔታውን ሊያባብስ የሚችል አደገኛ እርምጃ ብለውት ነበር። ሌስሊ ሌፍኮው የከፋ ደም መፋሰስ ሊያስከትል እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውም አይዘነጋም። የጸጥታ ኃይሎች ከተቃዋሚዎች «በጦር መሳሪያ»የታገዘ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል የሚሉት አቶ ጌታቸው ግን አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል ሲሉ ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic