«የኦሮሞ መገፋት ይቁም» ሰልፈኞች | ኢትዮጵያ | DW | 12.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

«የኦሮሞ መገፋት ይቁም» ሰልፈኞች

የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ፎቶግራፎች ይዘው በወሊሶ ከተማ አደባባይ የወጡት ተቃዋሚዎች "ለማ መገርሳ የእኛ ነው" ሲሉ ተደምጧል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሻሸመኔና በምዕራብ ሐረርጌ ትናንት በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ስድስት ሰዎች ተገድለው ከ30 በላይ መቁሰላቸውን አስታውቋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:50 ደቂቃ

ሻሸመኔ እና ምዕራብ ሐረርጌ ቦኬ ትናንት 6 ሰዎች ተገድለዋል

ተማሪዎች፤ የከተማ እና የገጠር ነዋሪዎች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ ዛሬ በወሊሶ ከተማ ተካሒዷል። የወሊሶ ከተማ ነዋሪ "ኃይለኛ ነበር" ባሉት የተቃውሞ ሰልፍ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳን የሚያወድሱ መፈክሮች ተሰምተዋል።
በተቃውሞ ሰልፉ ሰልፉ ላይ "ወያኔ የታሰሩ የፖለቲካ ሰዎችን ይፍታልን። ወያኔ ዳውን ዳውን እያሉ፤ለማ መገርሳን እያወደሱ፤መሬታችን ይመለስልን፤ወያኔ አብቅቷል ካሁን በኋላ ምንም ማድረግ አይችልም" የሚሉ መፈክሮች መስማታቸውን የተናገሩ የአይን እማኝ በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራሮች እንዲፈቱ መጠየቁንም አክለዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው በተደረጉ ተቃውሞዎች የሕዝብ ማመላለሻዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሚያስታውሱ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው የዛሬው ሰልፍ ሰላማዊ ነበር ሲሉ ይናገራሉ። 

"የተባለው ነገር የኦሮሞ ሕዝብ መገፋት፤ መባረር፤ መፈናቀል ይቁም። የአማራ መገፋት ይቁም፤ መገደል ይቁም፤ መሞት ይቁም። ኢሕአዴግ ወያኔ ይብቃው ነው መፈክሩ ማለት ነው። ቻው ቻው ወያኔ ሲባል ነበር የተዋለው። አብዛኛው ወጣት ነው። ከሁለተኛ እና ከመሰናዶ ት/ቤትም ሁሉም በቡድን በቡድን እየወጣ ነው ያደረገው። የእነ በቀለ ገርባንም ፎቶ ይዘው እነ ዶ/ር መረራ ጉዲናም ይፈቱ፤ ለማ መገርሳ የእኛ ነው። የኦሮሚያ ፖሊስ የኛ ነው። ወያኔ ገዳያችን ይቁም። የኦሮሞ መፈናቀል ይቅር። ምናምን የሚሉ ተቃውሞዎች ነበሩ።"

በፖሊስ ላይ ድንጋይ የወረወረ ወጣት ከጸጥታ አስከባሪዎች በተተኮሰ አስለቃሽ ጭስ ቆስሏል የሚል ወሬ መስማታቸውንም የዓይን እማኙ ጨምረው ተናግረዋል። 

"የጸጥታ አስከባሪ ነበር። ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ከሕዝብ ጋር ነበር እንቅስቃሴ የሚያደርጉት። ነገሮች  እንዳይበላሹ እና እንዳይጠፉ በትዝብት እያዩ ነበር እንጂ ሰላማዊ ሰልፉን ለመበተንም ግቡም ለማለት አልቻሉም። የቆሙ መኪናዎች ከፊታችሁ አሳልፉ ነበር የሚሉት።"

በትናንትናው ዕለት በአምቦ፤ ሻሸመኔ፤ በምዕራብ ሐረርጌ ቦኬ እና ዶዶላ ከተሞች ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገው ነበር። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በሻሸመኔ እና በቦኬ ከተማ በተደረጉት ተቃውሞዎች 6 ሰዎች ተገድለው ከ30 በላይ ቆስለዋል ብለዋል። 

"በሻሸመኔ እና በአምቦ ከተሞች እንዲሁም በምዕራብ ሐረርጌ ቦኬ ከተማ አካባቢ ሰላማዊ ሰልፎች ነበሩ። ሰልፎቹ በተደረጉበት ሁኔታ ላይ ትንሽ ከአቅጣጫ የመውጣት በዛም ሒደት ወደ ግርግር ተቀይሮ ሰዎች የሞቱበት ሁኔታ ነው ያለው። እስካሁን ባለኝ መረጃ በሻሸመኔ ከተማ ትናንት በነበረው ሰልፍ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሶስት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። ወደ ሰላሳ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ምዕራብ ሐረርጌም ቦኬ ወረዳ ላይ ሰልፍ ወጥቶ ሰልፉ ወደ ረብሻ ተቀይሮ የሶስት ሰዎች ያለፈ ሲሆን ሌሎች ሶስት ሰዎችም ቆስለዋል።"

የወሊሶ ከተማው ነዋሪ ከትናንት ጀምሮ የተቃውሞ ሰልፍ ሊደረግ እንደሚችል መረጃ ተሰራጭቶ እንደነበር ተናግረዋል። የዓይን እማኙ እንደሚሉት መረጃው የተሰራጨው ፌስ ቡክን በመሰሉ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች ነበር። 

አቶ አዲሱ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ "የማዕድን ቦታዎችን፣ የኮንትሮባንድ ንግድንና በመዋዕለ-ንዋይ ስም መሬት ይዘው በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚሔዱ" ያሏቸውን ኃይሎች ተጠያቂ ያደርጋሉ። አቶ አዲሱ ተቃውሞዎቹን የጠሩ ወገኖች ማንነት በይፋ ባይገልጹም ክልላዊ መንግሥቱን የሚደግፉ የማስመሰል ሥልት እየተከተሉ ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

"ያመጡት ሥልት ምንድነው የተሐድሶውን አመራር የሚደግፉ በማስመሰል ወጣቱን ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮችን በማንሳት ጭምር ወደ ሰልፍ እንዲወጣ የማድረግ፤ ሰልፉ ወደ ረብሻ እንዲቀየር ፤ ሰልፉን በሚያስከብሩ አካላት እና በተሰላፊዎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር በዚያ ሂደት ሰው እንዲሞት እና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን እንዳይረጋጋ፤ የጀመራቸውን ሥራዎች እንዳይቀጥል የማድረግ ፤ በህዝቡ እና በመንግሥት መካከል የተፈጠረው መተማመን እና አንድነት ቁርሾ እንዲኖረው የማድረግ ሁኔታዎች ያሉበት ነው ብለን ነው ያየንው።"

ስሜት ቀስቃሽ ርዕሰ-ጉዳዮችን በማንሳት ወጣቶችን ለተቃውሞ እየቀሰቀሱ ነው ያሉት ኃላፊው ሰልፎቹ ወደ ረብሻ እንዲቀየሩ ጥረት ተደርጓል ሲሉም ተናግረዋል። በተቃውሞ ሰልፎቹ የአካባቢ ሹማምንት እና የጸጥታ ኃይሎች ተሳትፈዋል የሚለው መረጃም ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል። 

"አንዳንድ አራማጆች በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የክልሉን የመንግሥት አካላት ግርግር እና ኹከት ፈጣሪ አስመስሎ የማቅረብ ሲያሻቸውም ደግሞ ኦነግ እንደዚህ አደረገ ብሎ ሌብል የማድረግ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው፤ ጥቅማቸው ከተነካባቸው ኮንትሮባንዲስቶች መሬት ዘራፊዎች እና ማዕድን ቦታዎችን ሲዘርፉ ከነበሩ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የማኅበራዊ  ድረ-ገፆች አራማጆች ነገሩ በዚህ አግባብ እንዲጨበጥ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የስራ አመራሮች ከላይ እስከታች ያለውን የመንግሥት ኃላፊዎችን ሌብል የማድረግ ነገር እንደገና ደግሞ ሰልፉን እንዳቀነባበሩ እና በሰልፉ አገርን እያፈረሱ ነው የሚል አቅጣጫ እንዲያዝ የማድረግ ሁኔታ ነው ያለው።"

ወጣቶች ተቃውሞ፤ ትችት እና ድጋፋቸውን በሰከነ መንገድ ሊገልፁ ይገባል ያሉት አቶ አዲሱ «የተሐድሶውን አመራር እደግፋለሁ ብሎ ሰልፍ የሚወጣ አካል ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት ሊደግፈን አይችልም» ብለዋል። 


እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic