የኦሮሞ ልጃገረዶች በጠፍ ጨረቃ | ባህል | DW | 14.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የኦሮሞ ልጃገረዶች በጠፍ ጨረቃ

ልጃገረዶቹ ከቤት ወላጆቻቸውን አስተኝተው ሲወጡ በሙሉ ነፃነት ነው። በኢትዮጵያ የኦሮሞ ልጃገረዶች ካላገቡ ወጣት ወንዶች ጋ እኩለ ሌሊት ላይ በአንድነት ተሰባስበው የሚዘፍኑበትና የሚጨፍሩበት ባህላዊ ክንዋኔ። ይህ ባህል ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ትውፊት ነው።

የተለያዩ ባህላዊ ዜማዎችን ከተቃራኒ ፆታ አቻዎቻቸው ጋ ሆነው ሌሊት ላይ ከሚከወነው ጭፈራ እየሰሙም እያዜሙም ያደጉ ኦሮሞዎች ዛሬ ምን እንደሚሰማቸው ማወቁ ይከብዳል። ምክንያቱም ይህ ባህላዊ ጭፈራ በሂደት ክንዋኔው እየደበዘ በመምጣት ላይ ነውና። በጨረቃ ብርሃን የሚከወነው ይህ ባህላዊ ጭፈራ በተለያየ ቦታ የተለያየ ስያሜ እንዳለውም ይጠቀሳል።

የኦሮሞ ልጃገረዶች ካላገቡ ወንዶች ጋ ተሰባስበው ሌሊት ላይ የሚያከናውኑትን ባህላዊ እንቅስቃሴ ለ15 ዓመታት ግድም በቅርበት የተከታተሉት አቶ በቀለ ለሙ ክንዋኔውን እንደሚከተለው በዝርዝር ያብራሩልናል።

በእዚህ ባህላዊ የሌሊት ጭፈራ ላይ የሚሳተፉ ወንዶች ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 ሲደርስ የልጃገረዶቹ ደግሞ ከ16 እስከ 24 መሆን አለበት እንደ ዶክተር ገመቹ መገርሣ ገለፃ። ዶክተር ገመቹ የዶክትሬት ማዕረጋቸውን በኦሮሞ ባህል ጥናት ላይ የሰሩ የስነ-ሠብ ተመራማሪ ሲሆኑ፤ ለረዥም ዓመታት በዩኒቨርሲቲ መምህርነት አገልግለዋል። ይህ ባህላዊ ክንዋኔ ከቦታ ቦታ የተለያየ ስያሜ እንዳለው ጠቅሰው የሌሊት ጭፈራው ዘርፈ-ብዙ ነው ይላሉ።

ወጣቶቹ ወንዶች ከቀርቀሃ ተቦርቡሮ የተሰራውን ፋጋ የተሰኘውን የሙዚቃ መሳሪያ ሌሊት ላይ መንፋት ይጀምራሉ። ይህ ጥሪ በአካባቢው የሌሊት ጭፈራ መኖሩን ማብሰሪያ ነው። ያኔ ልጃገረዶች ከጎረቤት ወንዶች ልጆች ጋር ተያይዘው ፋጋውን ወደሰሙበት ለመድረስ ይጣደፋሉ። ወንዶቹ ለጭፈራው የሚረዳቸውን ረዣዥም ዱላዎች አለያም ጦሮች ይይዛሉ። ሴቶች በሚገባ በሹሩባ ተጎንጉነው ነጠላ ያጣፋሉ፤ ነጠላዋ በኋላ ላይ ተጨማሪ ፋይዳ ይኖራታል። ክንዋኔው በሳምንት ሁለት ወይንም ሶስት ግዜም ሊደገም ይችላል በማለት አቶ በቀለ ለሙ ድርጊቱን በምናባችን እንድንስለው ለማድረግ ይሞክራሉ ።

በጨረቃ ብርሃን ታግዘው

በጨረቃ ብርሃን ታግዘው

እስኪ አሁን ደግሞ በዚህ የሌሊት ጭፈራ ላይ ከሚዜሙ ዜማዎች መካከል የተወሰኑት ምን አይነት ትርጓሜ እንዳላቸው እንመልከት። አቶ በቀለ ለሙ ይቀጥላሉ።

በዚህ ትውፊታዊ ክንዋኔ ከዜማና ጭፈራ ባሻገር ወጣቶቹ በነጠላ ተሸፋፍነው ከንፈር ለከንፈር ቢሳሳሙ ቤተሰብ ቅሬታ አይሰማውም። በእርግጥ ድርጊቱ ፈፅሞ ከመሳሳም ባሻገር እንዲዘልቅ አይፈቀድም። በስህተት ከመሳሳም ያለፈ ድርጊት የፈፀመ ወጣት ከማኅበረሰቡ የሚደርስበት ቅጣት እጅግ ከባድ እንደሆነ ዶክተር ገመቹ ይገልፃሉ።

የኦሮሞ ባህል እንደ ብዙው የዓለም ማኅበረሰብ ባህል በስልጣንና በአስተዳደር ረገድ ወንዶችን ቀዳሚ የሚያደርጉ ነው። ሴቶች በዚህ መሰሉ ባህላዊ ክንዋኔ መሳተፋቸው በወንድ እና በሴት መካከል ያለውን ልዩነትም ለማጥበብ ይረዳል ይላሉ ዶክተር ገመቹ። መሰረታዊ ባህሉ ጥልቅ እንደሆነ በማብራራትም ይቀጥላሉ፤

በተለያዩ ምክንያቶች በመክሰም ላይ የሚገኘውን ይህን የኦሮሞ ባህላዊ ጭፈራ አቶ በቀለ ለሙ እና ዶክተር ገመቹ በፅሁፍ ለማስቀመጥ ሙከራ አድረገዋል። ለአብነት ያህል በላምቤርት ባርቴልስ የተፃፈው Oromo Religion የተሰኘው መፅሐፍ ይጠቀሳል። በዚህ መፀሐፍ ላይ ሁለቱም ምሁራን የበኩላቸውን አበርክተዋል። የተወሰኑትን ስነቃሎች ከአቶ በቀለ እናዳምጥ።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎች ባለቤት፣ የተለያዩ ትውፊቶች ባለሀብት ናት። አሁን በቁንፅሉ ያቀረብንላችሁ የኦሮሞ ባህል ከውቅያኖሱ ባህላችን በጭልፋ የመጨለፍ ያህል ነው። ይህ ልጃገረዶች እና ወንዶች ልጆች የሚሳተፉበት የሌሊት ጭፈራ በተለያዩ ምክንያቶች በመጥፋት ላይ እንደሚገኝ ሁለቱም ምሁራን ያስጠነቅቃሉ።

ዘርፈ-ብዙ የባህል እሴቶቻችን እንዳይጠፉ የሚመለከታቸው አካላት በአጠቃላይ ልይ ክትትል ሊያደርጉበት እና ሊረባረቡበት እንደሚገባ በመጥቀስ የዛሬውን የባህል መድረክ ጥንቅር በዚህ እናጠቃልላለን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ሂሩት መለሠ

Audios and videos on the topic