1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ግጭት መወሳሰብ፡ የንጹሃን እልቂትና መከራ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ኅዳር 12 2017

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በንጹሃን ላይ ይፈጸማል ያለው ጥቃት እንዲቆም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጠየቀ። ፖርቲው እየተባባሱ ለሚገኙት የንጹሃን ግድያዎች በቀዳሚነት የሚጠየቀው መንግስት ነው ሲል ከሷልም። መንግስት በፊናው በክልሉ ተወሳስቦ ለቀጠለው ግጭት እና አለመረጋጋት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ይወቅሳል፡፡

https://p.dw.com/p/4nGDL
አርማ ፤ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
አርማ ፤ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያ ግጭት መወሳሰብ፡ የንጹሃን እልቂትና መከራ

የኦሮሚያ ግጭት መወሳሰብ፡ የንጹሃን እልቂትና መከራ

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በንጹሃን ላይ ይፈጸማል ያለው ጥቃት እንዲቆም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጠየቀ። ፖርቲው እየተባባሱ ለሚገኙት የንጹሃን ግድያዎች በቀዳሚነት የሚጠየቀው መንግስት ነው ሲል ከሷልም። መንግስት በፊናው በክልሉ ተወሳስቦ ለቀጠለው ግጭት እና አለመረጋጋት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ይወቅሳል፡፡ 

ስለግድያዎቹ የኦ.ነ.ግ. መግለጫ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ “ሰሞነኛው የማዕከላዊ ኦሮሚያ ሰላሌ ደራ ግድያ አሰቃቂ ነው፡፡” ፓርቲው በዚሁ ዘለግ ያለ መግለጫው “በአከባቢው በስፋት በኦሮሞ ህዝብ ላይ ተነጣጥሮ ይፈጸማል”ያለውን ግድያ የተቀናጀ ብሎታል፡፡ ኦነግ በዚህ መግለጫው አክሎ እንዳብራራው “መንግስት የኦሮሞ ነጻነት ጦርን ለመውጋት ያስታጠቃቸውና ያሰለጠናቸው የፋኖ ታጣቂች” ያለውን በአከባቢው ንጹሃን ላይ አስከፊ ያለውን በደል በማድረስ ከሷልም፡፡ ኦነግ በዚሁ እንዳብራራም “ከሰላሌ ደራ በተጨማሪ በቡድኑ በምስራቅ ወለጋ ዞን እና በወሎ አከባቢዎችም የጦር ወንጀል ሊባሉ የሚችሉ ንጹሃን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተፈጽመዋል” ሲል መግለጫውን አትቷልም፡፡

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ የመግለጫውን ጭብጥ ጉዳይ በተመለከተ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም፤ “ሰብዓዊነት የጎደለና የተቀናጀ ጦርነትን ያወገዝንበት ነው፡፡ ባለድርሻ አካላት ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ እንዲሆኑ በመጠየቅ ግድያውን ያወገዝንበት፤ ግድያውን የፈጸሙ ከዚህ በፊት በፓርላማ ስገለጹ እንደነበሩ በመንግስት የሰለጠኑ የታጠቁ፤ አሁን ላይ ግን ህዝባችን ላይ ሁለንተናዊ ጦርነት ተከፍቶበት ሀብት-ንብረቱን እያጣ ቀየው እየወደመ ህይወቱንም እያጣ ያለበትን ተግባር አውግዘናል” ብለዋል፡፡

ስለኦሮሚያ ግጭት ውስብስብነት የመንግስት አስተያየት

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ትናንት በሰጡን ቃለምልልስ በኦሮሚያ በተለይም ደግሞ በሰላሌ ደራ አከባቢ ግጭት መወሳሰብ “አሸባሪው ሸነ” ያሉት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና “ፅንፈኛ ፋኖ” ያሉዋቸውን የታጠቁ ቡድኖችን ንጹሃንን በግፍ በመግደል ከሰዋል፡፡ የዛሬው የኦነግ መግለጫ ግን መንግስት እና የፋኖ ታጣቂዎችን ከመክሰስ ባለፈ መንግስት ሸነ ያለው በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ላይ ስለሚቀርበው ክስ ያለው ነገር የለም፡፡

ንጹኃን በግጭት ውስጥ እንዳይጎዱ መንግስት ሚናውን በምን አግባብ እየተወጣ ይሆን በሚል የተጠየቁት የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ አክለው እንደነገገሩን ግን፤ “የመንግስት እርምጃ አሸባሪና ጽንፈኛውን ቡድን ላይ የሚያተኩር ቢሆንም፤ አሸባሪ ሸነም ሆነ ጽንፈኛው ፋኖ እርምጃ ስወሰድባቸው ንጹሃን ሞቱ ብለው የአዞ እንባ ያለቅሳሉ” ሲሉ ነው ምላሽ የሰጡት፡፡ አቶ ኃይሎ አክለውም “መንግስት ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ንጹሃንን የመታደግ ጥንቃቄ እያደረገ እርምጃ ይወስዳል” ሲሉ መንግስታዊ የጦር እርምጃዎች በስልት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸው ሞግተዋል፡፡

የክልሉን ሰላም በማወክና ንጹሃን ላይ አነጣጥሮ ግድያዎችን በመፈጸም በመንግስት በኩል ሰፊ ክስ የሚቀርብባቸው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ እና ኦነሰ ታጣቂዎች በዚህ ላይ ያላቸውን ምላሽ ለማካተት ግን ዶይቼ ቬለ ኃላፊነት ወስዶ አስተያየት የሚሰጥ ባለማግኘቱ ለጊዜው ሃሳባቸውን በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም፡፡

ኦሮምያ ክልል
ኦሮምያ ክልል ምስል Seyoum Getu/DW

የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ፤ የመንግስት ኃላፊነት

ኦነግ በዛሬው መግለጫው እንዳመለከተው ግን ደራ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አዋሳኝ አከባቢዎች ተወሳስቦ የሚገኙ ግጭቶች በንጹሃን የኦሮሞ ህዝብ ላይ ይፈጸማል ላለው ጥቃት ቀዳሚው ተጠያቂ መንግስት ነው፡፡ ቃል አቀባዩ አቶ ለሚ፤ “እኛ የህዝባችን ሁለንተናዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ መፍትሄ ያልነውን ስናስቀምጥ ነበር፡፡ የህዝቡ ሰላምና መረጋጋት መረጋገጥም ያለበት በመንግስት እንጂ ከታጠቀ አካል የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ግን መንግስት ላለፉት ስድስት ዓመታት የወሰደው እርምጃ ይህን እንዳላመጣ ነው ያስተዋልነው” ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኩል ዛሬ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ እንዳመለከተውም ከሰሞኑ “በጽንፈኞች ጭካኔ በተሞላ አኳሃን የተወሰደው ዘግናኝ ግድያ” ያለው ተግባር አውግዞ፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ይሰራል ብሏል፡፡ ከሰሞኑ ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ውስጥ መሳሪያ የታጠቁ አካላት አንድን ግለሰብ ፀያፍ ስድም እየተሳደቡ የፈጣሪንም ስም እየጠሩ እንዲታረድ ስፈርዱበት የሚሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጋርቶ ብዙዎችን አስቆጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡  

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ