የኦሮሚያ ክልል ከ2ሺህ በላይ እስረኞችን ለመልቀቅ ወሰነ | ኢትዮጵያ | DW | 26.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኦሮሚያ ክልል ከ2ሺህ በላይ እስረኞችን ለመልቀቅ ወሰነ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በዛሬዉ ዕለት ከ2 ሺህ በላይ ለሆኑ ታሳሪዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታወቀ። ከነዚህም ዉስጥ 1 ሺህ 568 ቱ ተፈረዶባቸዉ በእስር ላይ ይገኙ እንደነበር ተገልጿል። ቀሪወቹ ጉዳያቸዉ በፍርድ ቤት ሲታይ የነበረና በፖሊስ ምርመራ ላይ የነበሩ ናቸዉ ተብሏል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:08

«የሚፈቱት በተቃዉሞ በመሳተፋቸዉ የታሰሩ ሰዎች ናቸዉ»

የኢትዮጵያ መንግሥት ለተሻለ ሀገራዊ መግባባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል በመላዉ ሀገሪቱ የተወሰኑ እስረኞችን ለመፍታት መወሰኑ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ባለፈዉ  ሳምንት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲናን ጨምሮ 115 ሰዎች ከእስር ተፈተዋል። በደቡብ ክልልም ከ500 በላይ እስረኞች በተመሳሳይ ተለቀዋል። በዛሬዉ ዕለት ደግሞ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ከ2 ሺህ የሚበልጡ እስረኞች እንዲለቀቁ መወሰኑን የክልሉ የፍትህ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ሀላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

«በዛሬዉ እለት 2345 እስረኞች እንዲፈቱ ተወስናል።ከእነዚህ ዉስጥ 1538 የተፈረደባቸዉ ናቸዉና የተለቀቁ ናቸዉ።250 የሚሆኑት ደግሞ ክሳቸዉ በዓቃቬ ህግ ተይዞ እያለ ተቋረጠ ነዉ።557 የሚሆኑት ደግሞ ተይዘዉ በፖሊስ ምርመራ እያሉ የተቋረጠ ነዉ»ብለዋል።

በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራዉ የክልሉ ካቤኔ ታሳሪዎቹ ከእስር እንዲለቀቁ  መወሰኑን የገለፁት ሀላፊዉ ፤ ዉሳኔዉ የተላለፈላቸዉ የማረሚያ ቤቶች ከዛሬ ጥር 18 ቀን 2010 ጀምሮ እስረኞችን መልቀቅ እንደሚጀምሩ አስረድተዋል። እንደእሳቸው ገለጻም፤ በዚህ የይቅርታ ዉሳኔ ይፈታሉ የተባሉት አብዛኞቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ በተደረገ ህዝባዊ ተቃዉሞ ሳቢያ ታስረዉ የነበሩ ናቸዉ። የይቅርታዉ መነሻ የፌደራል መንግሥት በቅርቡ ያሳለፈዉን ዉሳኔ መሠረት ያደረገ ቢሆንም ከባድ የአካል ጉዳት የያደረሱ እና የሰዉ ሕይወት ካጠፉ እስረኞች ዉጭ ሁሉም እንዲለቀቁ መወሰኑንም አብራርተዋል። 

«በኛ በኩል ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ከተቃዉሞዉ ጋር በተያይዞ የታሰሩ ናቸዉ የሚፈቱት።በመደበኛ ወንጀሎች የሚመለከት ጉዳይ ሳይሆን ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከዚህም ጋር ተያይዞ የታሰሩ ናቸዉ የተፈቱት ። ጉዳያቸዉ ከዚህ ጋር ተያይዞ ያልተፈቱት አንደኛ የሰዉ ህይወት ያጠፉ ማለት ልክ ቢፈቱ ከሟች ቤተሰብ ጋር ግጭት ሊኖር ስለሚችል ይሄ ነገር በባህላዊ መንገድ መፍትሄ እስኪያገኝ አሁን መልቀቅ ሌላ«ኪኦስ» የሚፈጥር እንዳይሆን እነዛ አልተለቀቁም።ከባድ የአካል ማጉደል ያረሱትም ጉዳዩ በተቃዉሞ ዉስጥ ሆኖ በዚህ ዓይነት ጉዳት ያደረሱ ለጊዜዉ ጉዳያቸዉ በሌላ መልኩ መፍትሄ እስኪያገኝ አይለቀቁም።ከዚህ የቀረ ግን ይለቀቃሉ» ነዉ ያሉት።

እነዚህ ሰዎች መለቀቅም በክልሉ በፖለቲካ አመለካከት ምክንያት የሚፈጠር የእርስ በርስ መጠራጠርን እና አለመተማመን  ያስቀራል ሲሉም ኃላፊዉ አክለዋል።
ላላፉት ሦስት ዓመታት ክልሉ የመብት ጥያቄን በሚመለከት የተቃዉሞ ዓመፅ ሲናጥ የቆየ እና አብዛኛዎቹ ሰዎችም ከዚህ ጋር በተያያዘ የታሰሩ በመሆናቸዉ የታሳሪዎቹ መለቀቅ የህዝብ ጥያቄም  በመሆኑ ጥሩ ርምጃ ነዉ ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ዶክተር ሚልኬሳ ሚደጋ ናቸዉ።

በይቅርታ ዉሳኔዉ በተፈፀሙ ችግሮች የሰዉ ህይወት ያላጠፉ ከባድ የአካል ጉዳት ያላደረሱ ትልልቅ የኢኮኖሚ አዉታሮችን ለማዉደም ቀጥተናኛ ተሳትፎ ያላደረጉ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ ቁልፍ ሚና ያልነበራቸዉና መንግስት መስራት ሲገባዉ ባልሰራቸዉ ስራወች ምክንያት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ተነድተዉ በግጭትና በሁከት ዉስጥ የተሳተፉ ተጠቃሚ እንደማይሆኑ መንግስት ቢገልፅም በአንፃሩ ግን የኦሮሚያ ክልል  ለህዝብ ሲሉ የታሰሩ ይፈታሉ ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል።

ፀሐይ ጫኔ

ሸዋዬ ለገሰ

 

Audios and videos on the topic