1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ የተጠራው አድማ መወያያ ሆኗል

ዓርብ፣ ነሐሴ 19 2009

በኦሮሚያ ክልል የተጠራው የአምስት ቀን አድማ፤ ሳምንቱን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ፀሐፍትና ትኩረት ከሳቡት ጎላ ያለዉ ጉዳይ ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አምስተኛ ሙት ዓመት እና የአጼ ምኒልክ የልደት መታሰቢያ በዓልም ያነጋገሩ ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ የአሸንዳ በዓልም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰፊ ሽፋን አግኝቷል፡፡

https://p.dw.com/p/2ireQ
Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

በኦሮሚያ የተጠራው አድማ መወያያ ሆኗል

ኦሮሚያ ያለፈውን ዓመት፤ እዚህም እዚያም በሚገነፍሉ ተቃውሞዎች ስትናጥ ነበር ያሳለፈችው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ተቃውሞ ረገብ ብሎ ነበር፡፡ የፌደራል እና የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት የችግሩን መንስኤ አውቀናል፣ መፍትሄዎች አበጅተናል፣ በጥልቅ ታድሰናል ሲሉም ነበር።

Äthiopien Unruhen
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

ይሁንና አስር ወር የዘለቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተነሳ በቀናት ውስጥ በኦሮሚያ እና አማራ ዳግም ተቃውሞ ለመቀስቀስ  ብዙ ጊዜ አልወሰደም፡፡ ከግብር ጭማሪ እና በእስር ላይ ከሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር በተያያዘ ለጥቂት ቀናት የቆዩ ተቃውሞዎች በተለያዩ ከተሞች ሲታዩ ሰነበቱ፡፡ 

በኦሮሚያ ወጣቶች (ቄሮዎች) ለዚህ ሳምንት ተጠራ የተባለው እና በማህበራዊ ድረገጾች አማካኝነት የተሰራጨው የአምስት ቀን የአድማ ጥሪ ግን ባለፉት ሳምንታት ከታዩት ከበድ ያለ ይመስላል፡፡ “የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ የሶማሌና ኦሮሚያ ድንበር ጉዳይ እልባት ያግኝ፣ ከአቅም በላይ የተጫነው ግብር ይነሳ” በሚል የተጠራው አድማ በማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዋነኛ መወያያ እንደሆነም አለ፡፡  

ወንድወሰን ቲኢ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ባለፈው ረቡዕ ባሰፈሩት ጽሁፍ ተቃውሞ እና የሚሰጠው ምላሽ “ውሃ ቅዳ፣ ውሃ መልስ” አይነት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ “አገር አንቀጥቅጥ ተቃውሞ፣ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ፣ የጅምላ ግድያ፣ አፈሳ፣ እስርና "ስልጠና"፣ ጥልቅ ተሃድሶ፣ አገር አንቀጥቅጥ ተቃውሞ እንደገና። Back to square one እንዲል ፈረንጅ። ምርጫው ሁለት ነው። ወይ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ማድረግ ወይ ደግሞ በህዝባዊ ማዕበል ተጠራርጎ መወሰድ። ከዚህ በኋላ የጥቂቶች ፍጹም የበላይነት የሰፈነበትን ስርዓት የሚሸከም ትከሻ ያለው ህዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። መልዕክቱ ግልጽ ይመስለኛል!” ሲሉ ጽፈዋል፡፡  

በርካታ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ግን እንደ ወንድሰን ቲኢየአድማውን ጥሪ በተቃውሞ ወስደው አልደገፉትም፡፡ አድማው መጀመሪያ እንዲካሄድ ታስቦ የነበረባቸው ነሐሴ 15 እና 16 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የፍልሰታ ጾም ፍቺ ሃይማኖታዊ ስነስርዓት የሚካሄድባቸው መሆኑ ተቃውሞ ቀስቅሷል፡፡ የሃይማኖቱ ተከታዮች “እንዴት በዚህ ቀን ከቤት አትውጡ፤ ከወጣችሁ እርምጃ ይወሰድባችኋል እንባላለን” ሲሉ ቁጣቸውን በተለያዩ ጽሁፎች አንጸባርቀዋል፡፡ ይህንን ተቃውሞ የተመለከቱ የአድማው አስተባባሪዎች “የጾም ፍቺውን ታሳቢ በማድረግ እና የሁለት ቀን አድማ ተጽእኖ ለመፍጠር በቂ አይደለም” በማለት የቀናት ለውጥ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

Äthiopien Jimma Geschlossene Geschäfte
ምስል DW User via Whatsapp

አድማው ከነሐሴ 17 ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ የሚያስገነዝቡ ማስታወቂያዎች መውጣት ሲጀምሩ ሌላ ውዝግብ ተከተለ፡፡ በማስታወቂያዎቹ  እና መግለጫዎቹ ከአድማው ጋር በማይተባበሩት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መገለጹ ተተችቷል፡፡ ከማስታወቂያዎቹ መካከል አንደኛው “የአንድ ብሔር ነጋዴዎችን ኢላማ አድርጓል” በሚልም ተወግዟል፡፡

አገኘሁ አሰግድ በፌስ ቡክ ገጹ “በኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች እና በኦሮሚያ ክልል ተዘዋዋሪዎች ለሆናችሁ በሙሉ፣ እንኳን ከኢሕአዴግ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወደ ጃዋር የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በሰላም አሸጋገራችሁ፡፡ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሰላም፣ የፍቅር እና የብልፅግና ይሁንላችሁ” ሲል ተሳልቋል፡፡  መዲ መንገሻ አወዛጋቢው ማስታወቂያ ከትችቶች በኋላ በአርትኦት መስተካከሉን አድንቀው ይዘቱ ላይ ተከታዩን አስተያየት በፌስ ቡክ ሰጥተዋል፡፡ “የተቃውሞ ጥሪ ላይ ያልተሳተፈን ሁሉ ጠላት አድርጎ መፈረጅ አግባብ ነው አይደለም ? «ከኔ ጋር ካልሆንክ ከነሱ ጋር ነህ» አይነት በመንግስታችን ላይ የምንጠላው አስገዳጅ ፀባይ በተቃውሞውም ጎራ ሲሆን ተቀባይነት ይኖረዋል ወይ ? አጠያያቂ ነው ! በተለይ ግን! የአንድ ብሄረሰብ ነጋዴ ላይ ያነጣጠረ የሚመስል ጥሪ በፌስቡክ ገፁ መለጠፉ በሚዛናዊነት እና ማቻቻል ሰበብ ተሸፋፍኖ ሊታለፍ የሚችል አይደለም ። አገላለፆቹ ያሳቅቃሉም ትክክልም አይደሉም” ብለዋል፡፡

ብሩክ አምባቸው ደግሞ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት አስተያየት “አድማው ጥቅም የለውም” የሚለውን አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ “እኔ እንደማምነው በቤት ውስጥ የመቀመጥ ተቃውሞ የጊዜ እና የገንዘብ ብክነት ነው፡፡ ቤት ውስጥ በመቀመጥ እና ምንም ባለመስራት ምንም የምንለውጠው ነገር የለም፡፡ እንለውጣለን እንዴ? በዚያ ላይ በቤት ውስጥ እንድቆይ የሚነግሩን ሰዎች በውጭ ሀገር የሚኖሩ ናቸው፡፡ ምናልባትም ይህን ጊዜ እየጠጡ ይሆናል፡፡ ንቁ ሰዎች!” ብለዋል፡፡ 

በዚያው በትዊተር ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩት አህመድ አብዱራህማንም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ “ሰው አገር ቁጭ ተብሎ ትዕዛዝ የሚሰጥበትን የትኛውንም ዓይነት አድማ በአገሬ ላይ እቃወማለሁ። ትዕዛዝህን ቤትህ አስቀምጠው። አንተ በምላሹ ዋጋ የማትከፍለበትን ጉዳይ በምን ሞራል ታዘዋለህ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የማህበራዊ መገናኛዎች ንቁ ተሳታፊው እሸቱ ሆማ ቀኖ ግን በዚህ አይስማም፡፡ “ይሄ ሁሉ ህዝብ ከቤት ባለመውጣት አድማ በነቂስ እየተሳተፈ የሚገኘው ከዲያስፖራ በሚያገኘው ትዕዛዝ ምክንያት ነው እያሉ መቀደድ ሕዝብን መናቅ ነው” ሲል አስተያየቱን አጋርቷል፡፡

ዘውዴ ታደሰ በፌስ ቡክ ገጻቸው ከእሸቱ ጋር የሚመሳሰል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ “የትግሉ ባለቤት የተጨቆነ፣የተረገጠ፣በደል አናቱ ላይ የወጣበት ድህነት የቀጠቀጠው አንባገነን ስርዐት የሰለቸው በሀገር ቤት የሚኖር ነፃነት ናፍቂ ትውልድ ነው። በውጭ ያለው የፕሮፓጋንዳ እና የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል ከዛ ውጪ ግን የትግሉ መሪ ወይንም ባለቤት ሊሆን ከቶም አይችልም ሆኖም አያውቅም። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት እኮ ፍዳውን ሲበላ የነበረው ህዝብ በሀገር ቤት ያለው ይህ ወጣት እንጂ ባህር ተሻግሮ በድሎት የሚኖረው ሰው አይደለም፡፡ ስለዚህ ዛሬም ከአምባገነን ገዥዎች ጋር አንገት ለአንገት እየተናነቀ ያለው የተበደለ ግፍ የበዛበት ወጣት መሆኑን ማወቁ ደግ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የተነሱ ሀሳቦችን በሁለት አስተያየቶች ላጠቃልል፡፡ ገዢውን ፓርቲ በግልጽ የሚደግፉት ሰናይት መብራህቱ የአድማውን ጥሪ ተከትሎ በፌስ ቡክ ገጻቸው “አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን በከፊል መነሳት ነበረበት” ሲሉ ጽፈዋል፡፡ መርዕድ አርማ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ “ቄሮዎች ለአምስት ቀናት ያልተቋረጠ አድማ ማካሄድ ከቻሉ በኦሮሚያ ውስጥ አዲስ አዛዥ አለ ብሎ መገመት ይቻላል” ብለዋል፡፡  

Äthiopien Stadt Mekelle Atse Yohannes
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ሳምንቱ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች የነበሩትን የአጼ ምኒልክ እና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም በማህበራዊ ድረ ገጽ ተደጋግሞ የተነሳበት ነበር፡፡ የአጼ ምኒልክን የውልደት ቀን አስመልክቶ እስከ ትውልድ ስፍራቸው አንጎለላ ድረስ የዘለቀ መታሰቢያ ተደርጎላቸዋል፡፡ ወደ አንጎለላ በተደረገው ጉዞ የተሳተፉ በቦታው የነበረውን የአከባበር ሥነ ሥርዓት በፎቶዎች አስደግፈው አጋርተዋል፡፡ መኩ ደማ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “አጤ ምኒልክን አብዝቼ እወደዋለሁ፤ አከብረዋለሁ፤ አደንቀዋለሁ። ይኽን ስል በምክንያት ነው። ምኒልክ የሚወደድ ስብዕና ያለው መሪ ነበር። ሀገሩን ለማዘመን ሳይታክት ለፍቷል። ተራራ ቧጧል፤ ቋጥኝ ፈልፍሏል። ያ ማለት ግን ምኒሊክ ፍፁም ሰው ነበር ማለት ግን አይደለም። ኢትዮጵያን የመሰለች ታሪካዊትና ኃያል ሀገር ወደ ቀደመ ክብሯ የመለሰ ታላቅ ሰው ነበር። በዚህ ሁላ ሂደት ውስጥ 'ፍፁም ሰው' መሆን አይቻልም!” ሲሉ በአጼው ዙሪያ ለሚነሱ ትችቶች ምላሽ የሚመስል ጽሁፍ አስንብበዋል፡፡ 

“የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ መሪ” በሚል መፈክር የታሰበው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አምስተኛ ሙት ዓመትም በርካታ የሙገሳ እና የትችት አስተያየቶችን አስተናግዷል፡፡ ሃይከል የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ የመታሰቢያውን መሪ ቃል ሲያነብ በጆርጅ ኦርዌል “1984” መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰውን “ጦርነት፤- ሰላም ነው፡፡ ነጻነት፤- ባርነት ነው፡፡ መሀይምነት፤- ጥንካሬ ነው” የሚለውን አባባል አስታወሰኝ ብሏል፡፡ ተክሊት ኃይላይ በዚያው በትዊተር “መለስን መጥላት መብት ነው፡፡ መለሲዝምን ለማወቅ አለመሞከር ግን ራስን ከዕውቀት ማጽዳት ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡ 

ማክሰኞ ነሐሴ 16 በሺህዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶች በመቀሌ ከተማ የአሸንዳን በዓልን በደማቀ ሁኔታ አክብረዋል፡፡ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች የበዓሉን ድባብ፣ በቦታው የነበረውን ስነስርዓት እና የሙዚቃ ድግስ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች አጋርተዋል፡፡ በባህል አልባሳት የተዋቡ ልጃገረዶች ፎቶዎችም የብዙ የማህበራዊ ድረ ገጾች ማድመቂያ ነበሩ፡፡ እንደ አሸንዳ አይነት በየክልሉ ያሉ በዓላት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቁ፣ እንደ ቡሄ ያሉ ሀገር አቀፍ በዓላት ደግሞ እየከሰሙ መምጣታቸውን አንስተው የተቆጩ አሉ፡፡ ከበዓል ድባቡ ወጣ ያሉ እና በዓሉ መጀመሪያ መከበር ከጀመረበት ቦታ ጋር የተያያዙ ብሽሽቆችም ተስተውለዋል፡፡

ይህን የታዘቡት ቦረና ቦረና በሚል ስም የፌስ ቡክ ገጽ ያላቸው ተጠቃሚ ተከታዩን አስተያየት ባለፈው ሰኞ አስነብበው ነበር፡፡ “ሻደይ፣አሸንድዬ፣ሶለል እና አሸንዳ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በድምቀት ይከበራሉ፡፡ ስያሜቸው ይለያይ እንጂ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው የጋራ ሃብት ናቸው፡፡ እንደ እድል ሆኖብን መሰለኝ የዚህ ከልል ነው፣ የዚያኛው ነው እያልን መነዛነዝ አልተውንም፡፡ የሰሞኑ በዓል አንድ ትልቅ የሀይማኖት አባት የተናገሩትን ያስታውሰኛል፡፡ ምን አሉ መሰላችሁ ፡- ፈረንጆቹ በሀገራት መካከል ወንዝ ሲያገኙ በጋራ ያለሙትና ለመዝናኛነት ይጠቀሙበታል እኛ ደግሞ ወንዝ ሲኖረን ደንበር ለማድረግ እንጣላበታለን ብለዋል፡፡ እና ምን ለማለት ነው እኛ እጣፈንታችን የጋራ እና አብሮ የመኖርን ነው!” ሲሉ ጽፈዋል፡፡የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አብርሃ ደስታ ደግሞ “አሸንዳ ባህልን ጠብቆ መከበር አለበት ሲባል ከባህል ወደ ፖለቲካ መቀየር አለበት ማለት ነው እንዴ?” ሲል ጠይቆ በበዓሉ የታዘበውን በፌስ ቡክ ገጹ አካፍሏል፡፡ “ድሮ አሸንዳ ሴቶች ከበሮ ይዘው የሚጫወቱበትና በወላጆች የሚመረቁበት አስደሳች የጨዋታ ቀን ነበረ። ዘንድሮ ሴቶች በአደባባይ ተሰብስበው የባለስልጣናት ረዣዥምና አሰልቺ ንግግሮችን የሚያዳምጡበት የስብሰባ ቀን ሆኗል። ባጭሩ አሸንዳ ባህልን ከሚንፀባረቅበት የጨዋታ ቀን ፖለቲካ ወደሚሰበክበት የስብሰባ ቀን የተቀየረበት ሁኔታ ነው ያለው። በዚሁ ጉዳይ 11 በመቶ ዕድገት አስመዝግበናል” ሲል ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በአብዛኛው የሚጠቀሰውን አኃዝ በመጥቀስ አነጻጽሯል፡፡ 

Äthiopien Abreha Desta in Mekelle
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

ኡሙ ጁዲ ተመስገን ከበዓሉ በኋላ ከአዲስ አበባ በፌስ ቡክ በጻፈችው አስተያየት “አሸንዳ አለቀ፤ ከተማዋ ውበትዋ ፈዘዘ፤ የሹሩባ ወረፋም ቀነሰ፡፡ አቦ! እንዴት አባታቸው ያምሩ ነበር፡፡ በእውነት ውብ ነበር” ስትል በዓሉ ፈጥሮ የነበረውን ስሜት አጋርታለች፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ