የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ | ኢትዮጵያ | DW | 28.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም በተመለከተ የተዘጋጀን የአዋጅ ረቂቅ ለተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ትናንት ተገልጿል፡፡ ረቂቁ የኦሮሚያ ክልል ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ ከአገልግሎት አቅርቦት፣ ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እና የአካባቢ ጥበቃ አኳያ ያለውን ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:12

ሰማያዊ አዋጁ የህዝብን ጥቅም የሚያስከብር አይደለም ይላል

የኢትዮጵያ መንግስት እስከያዝነው ዓመት መጀመሪያ ድረስ ዘልቆ የነበረውን እና የኦሮሚያ ክልል በርካታ ቦታዎችን ባዳረሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተከታታይ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ የተወካዮችን እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶችን በመስከረም ወር መጨረሻ ሲከፍቱ ከመንግስት እቅዶች ውስጥ አንዱን እንዲህ ጠቅሰዋል፡፡       

“የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስፈጻሚውን አካል ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን የቁጥጥር ሥራ መልካም ጅምሮች የበለጠ ከማጎልበት በተጨማሪ የተያያዝነውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማሳካት የሚያግዙ አዋጆችን እንደሚያወጣ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አኳያ በዘንድሮ ዓመት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ጥቅም ለመደንገግ የሚወጣውን አዋጅ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዋጆች የሚወጡ ይሆናል” ብለው ነበር ፕሬዝዳንቱ፡፡    

በ1987 ዓ.ም ስራ ላይ በዋለው ኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 49 ላይ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ዝርዝር ወደፊት በህግ እንደሚወሰን ተደነግጓል፡፡ በህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ሲነሱ ከነበሩ ጥያቄዎች ውስጥ ኦሮሚያ በመሬት፣ በማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦት፣ በቋንቋ እና በባህል ጉዳዮች ከአዲስ አበባ ልታገኝ የሚገባትን ጥቅም አጥታለች የሚል ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አዋጁን እያዘጋጀ እንደሆነ በተደጋጋሚ ቢናገርም እስከ ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ድረስ ግን ስለ ህጉ ዝርዝር የተሰማ ነገር አልነበረም፡፡

ከሁለት ወር በፊት ሾልኮ ወጣ የተባለ የ“ኦሮሚያን ልዩ ጥቅም የሚስጠብቅ የህግ ረቂቅ” በማህበራዊ ድረ-ገጾች አማካኝነት ከተሰራጨ በኋላ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰነብቷል፡፡ ይህን አወዛጋቢ ሰነድ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት “እንደማያውቁት” ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ትናንት “የኦሮሚያ ክልል ህገመንግስታዊ ልዩ ጥቅምን” አስመልክቶ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የቀረበው መግለጫ ሾልኮ ወጣ በተባለው ሰነድ ላይ የተነሱ ጉዳዮች መካተታቸውን አመላክቷል፡፡

በአዋጁ ከተካተቱት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ፣ ሰፈሮች እና ቦታዎች ስያሜ፣ የከተማይቱ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ እና በከተማይቱ ዙሪያ የሚኖሩ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ሊያገኟቸው ይገባሉ የሚባሉ ጥቅሞች ይገኙባቸዋል። በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ሊኖረው የሚገባው ጥቅም በአዋጁ መደንገጉ ተነግሯል፡፡ የእነዚህ ልዩ ጥቅሞች ተግባራዊነትን እና ክልሉን ከከተማው ጋር የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚከታተል፣ የሚገመግም እና ድጋፍ የሚያደርግ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ይፋ ተደርጓል፡፡

የትናንቱ መግለጫ ሾልኮ በወጣው ሰነድ ላይ ላወዛገቡ አንቀጾችና አገላለጾች በተሰጡ ማስተካከያዎችና ማስተባበያዎች የተሞላ ነው ሲሉ የተቹ አሉ፡፡ ዓመታዊ የስራ መጠናቀቂያው ሰኔ 30 የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት የትኛውን ጊዜ አግኝቶ በአዋጁ ረቂቅ ላይ እንደሚወያይ የጠየቁም ነበሩ፡፡ ምክር ቤቱ በነገው መደበኛ ስብሰባው ሊመለከታቸው ካቀዳቸው 13 አጀንዳዎች መካከል የአዋጁ ረቂቅ እንደሌለ በተወካዮች ምክር ቤቱ የህግ አወጣጥ ክትትልና ቁጥጥር ሙያዊ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰመረ ሳሶ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡

“እስካሁን የማውቀው በነገ አጀንዳ አለመካተቱን ነው፡፡ የሚካተተው በአሰራር ነው፡፡ አሰራሩ አፈ ጉባኤው ጋር ይደርሳል፡፡ አፈ ጉባኤው ለምክር ቤት አባላት እንዲደርስ በአጀንዳ እንዲያዝ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ በሚቀጥሉት ሳምንታትም እስከ [ሰኔ] 30 ድረስ ጊዜ አለ፡፡ ከ[ሰኔ] 30 በኋላም በህጉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ስራ ካለ በራሱ ውሳኔ ማራዘም ስለሚችል፣ ገና ስለሆነ እና የሚቀጥለው ሳምንት ስላለ ይሄ ነው ማለት አይቻልም” ሲሉ የአዋጁ ማቅረቢያ ቀን ገና እንዳልተወሰነ ይገልጻሉ፡፡      

የኦሮሚያ ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ የቀረበውን መግለጫ የተመለከቱት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ አዋጁ “የተፈጠረውን ችግር የሚፈታ ሳይሆን በራሱ ችግር የሚፈጥር ነው” ሲሉ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡ “አገዛዙ ህዝቡን እርስ በእርሱ በማያያዝ የራሱን ዕድሜ ለማራዘም የተጠቀመበት ስልት ነው” ሲሉ አዋጁን አጣጥለውታል፡፡   

“እያንዳንዱ ዜጋ ኦሮምኛ ተናጋሪም ይሁን አማርኛ ተናጋሪ እንደ ዜጋ ያለው ጥቅም ሳይከበር ስለ ልዩ ጥቅም ማውራት ራሱ ትክክል አይደለም የሚል ነው መነሻው፡፡ የአዲስ አበባ ና የኦሮሚያ ጉዳይ ለ2008 ዓ.ም ህዝባዊ ተቃውሞ መነሻ ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ እነዚህን መንግስት በትክክል መፍታት እንዳልፈለገ የሚሳይ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ህዝብ እና ህዝብን ማጋጨት፣ አንዱ ተጠቃሚ አንዱ ቆሞ የሚያይ የሚያስመስል፣ ለአፈጻጸምም በጣም የሚቻል የማይመስል ነገር ግን ህዝቡን ለማቃቃር ሆን ብሎ ታስቦ በተንኮል የተሰራ ነው የሚመስለኝ፡፡ ለመፍትሄ ሳይሆን ለማደናገር የተፈጠረ አገዛዝ ስለሆነ ብዙ ላይገርም ይችላል” ሲሉ አቶ የሺዋስ ይተቻሉ፡፡   

“የህዝቡ የመጀመሪያ ጥያቄ በመረጥናቸው ሰዎች እንተዳደር የሚል ነው” የሚሉት አቶ የሺዋስ “ህዝቡ በመረጣቸው ሰዎች ሲተዳደር የፈለገውን ጥያቄ ማንሳት ይችላል፡፡ የሚጠየቀውም አካል መታወቅ ይችላል” ባይ ናቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ”ጠያቂውም ተጠያቂውም ራሱ ኢህአዴግ በመሆኑ የህዝብ ጥያቄ ተመልሷል አሊያም የህዝብ ጥቅም ተከብሯል” ለማለት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲያቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በጉዳዩ ላይ ህዝቡን ለማነጋገር እቅድ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የአዋጅ ረቂቁን አስመልክቶ በዶይቸ ቬለ የፌስ ቡክ ገጽ በርካታ ተከታታዮቻችን አስተያየታቸውን አጋርተውናል፡፡ ዴቪድ ፍራኦል የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ “ውሳኔው የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ እና የህገ-መንግስቱን አንቀፅ 49/5 ጠቅላላ ሀሳብ መተንተን ተስኖታል። ከመነሻው ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የህግ ምሁራን አለመሳተፋቸው ማሳያ ነው። ውሳኔው የተጣላ ሳይኖር አስታራቂ ይመስላል። በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲህ አይነት አገላለፁ ትርጉም የጎደለው ነገር አይቼ አላውቅም” ብለዋል።

በዋትስ አፕ አድራሻችን አስተያየታቸውን የላኩልን ስማቸውን ያልጠቀሱ አድማጫችን “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም መከበሩ” ጥሩ ውሳኔ ነው ይላሉ፡፡ “የኦሮሚያ ልጅ እዚያ በራሷ ቋንቋ መማር እንዳለባት ሁሉን ነገር ጥቅማ ጥቅሞች ማግኘት እንዳለባት ነው የምረዳው፡፡ የሰው ልጅ አባቱን ሲወርስ ነው የሚያምረው፡፡ የኦሮሚያ እስከሆነ ድረስ የኦሮሚያ ልጅ ጥቅም ማግኘት አለበት፡፡ መሬቱ የራሱ መሆን አለበት፡፡ ይሄን ነገር እንደግፋለን” ብለዋል፡፡
 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ       

 

 

Audios and videos on the topic