የኦርላንዶዉ ግድያና ዉዝግቡ | ዓለም | DW | 14.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኦርላንዶዉ ግድያና ዉዝግቡ

ፌደራዊ የምርመራ ቢሮ ሰዉዬዉ እራሱ እንዳለዉ ከISIS ወይም ከሌላ አሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት ያለዉ መሆኑን የሚያረጋግጥ መረጃ እስካሁን አልተገኘም ባይ ነዉ።መርማሪዎቹ እንደሚሉት ወጣቱ ካምደ መረብ ባገኘዉ መረጃ እራሱን ወደፅንፈኝነት የቀየረ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:55

የኦርላንዶዉ ግድያና ዉዝግቡ

አሜሪካዉያን እና ወዳጆቻቸዉ ኦርላንዶ-ፍሎሪዳ ዉስጥ አንድ ታጣቂ የገደላቸዉን ወዳጅ ዘመዶቻቸዉን በየአካባቢዉና በየኤምባሲዉ እያሰቡ ነዉ።በሐዘን መግለጫ እናማፅናናቱ መሐል የገደዩ ማንነት፤ አላማዉ እና ጤንነቱ እያነጋገረ፤ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞችን እያወዛገበ ነዉ።ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ለግድያዉ ከገዳዩ የጥላቻ አስተሳሰብ በተጨማሪ ገደብ የለሹ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ ሽያጭን ተጠያቂ አድርገዋል።የዴሞክራቲኩ ፓርቲ እጩ ፕሬዝደንት ለመሆን የሚወዳደሩት ወይዘሮ ሒላሪ ክሊንተን ከኦባማ ጋር ተመሳሳይ አቋም ሲያንፀባርቁ፤ የክሊንተን ተቀናቃኝ ፅንፈኛዉ የሪፐብሊካን ቱጃር ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ ግን ሙስሊሞች አሜሪካ መግባት የለባቸዉም እያሉ ነዉ።

አሜሪካ በየግዛቱ፤ በአብዛኛዉ ዓለም ደግሞ በየኤምባሲና አደባባዩ ለቅሶ፤ሐዘን፤ማፅናኛዉ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።የሟቾች ስም፤የአሟሟታቸዉ አሳዛኝነት በተነሳ

ቁጥር፤ የገዳዩ ማንነት፤ የአላማ ፍላጎቱ ምንነት መነሳቱ ግድ ነዉ።ኡመር ማቴን።አሜሪካ ተወልዶ፤ አሜሪካ ያደገ፤ በስፖርት የዳበረ፤ ለፀጥታ ጥበቃ የሠለጠነ የ29 ዓመት ወጣት ነበር።«ከሌላዉ ጊዜ ምንም የተለየ ነገር አላየሁበትም» አሉ አባት።

«ትናንት እኔና እናቱን ሊጠይቀን መጥቶ ነበር።ለመጨረሻ ጊዜ ያየነዉ ያኔ ነዉ።ከሌላዉ ጊዜ ምንም የተለየ ነገር አላየሁበትም።»

ለካ-ስንብት ኖሯል።በማግስቱ ጠመንጃዉን አንግቦ ከዚያ ግብረ-ሰዶማዉያን ከሚያዘወትሩት ዳንኪራ ቤት ገባ።ሥልክ ደወለ።ለፖሊስ።እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራዉ ቡድን አባል መሆኑን ነገረ።ከዚያ ጠመንጃዉን ያንፈቀፍቀዉ ገባ።አራባ-ዘጠኝ ገደለ።ከሐምሳ በላይ አቆሰለ።ለምን? አባትም ይጠይቃሉ።

«በሕይወት ቢኖር ኖሩ እንደ ወላጅ አንድ ጥያቄ ብቻ እጠይቀዉ ነበር።ለምን ይሕን አደረክ፤ ለምን?»መልስ አልባ ጥያቄ።ፌደራዊ የምርመራ ቢሮ ሰዉዬዉ እራሱ እንዳለዉ ከISIS ወይም ከሌላ አሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት ያለዉ መሆኑን የሚያረጋግጥ መረጃ እስካሁን አልተገኘም ባይ ነዉ።መርማሪዎቹ እንደሚሉት ወጣቱ ካምደ መረብ ባገኘዉ መረጃ እራሱን ወደፅንፈኝነት የቀየረ ነዉ።

የቀድሞ ባለቤቱ ግን «እብድ» አለችዉ።«በሽተኛ ነበር።የተሳከረበት ሰዉ ነዉ።እብድ ነበር።ግብረ-ሠዶማዉያንን እንደማይታገስ ተናግሮም ነበር።»

ታዛቢዎች እንደሚሉት ፖለቲካዊ ፅንፈኝነትም፤ ግብረ-ሠዶማዉያንን ጥላቻም የሽብር ግድያዉ ምክንያት ሊሆን ይችላል።ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ሰወስተኛ ምክንያት ያክሉበታል።

«እንደሚገመተዉ ገዳዩ ጠመንጃና በጣም ከባድ የዉጊያ መሳሪያ ታጥቆ ነበር።ሥለዚሕ መደዳ ግድያዉ የሚያስታዉሰን ነገር፤ ትምሕርት ቤት ይሁን፤ ቤተ-እምነት፤ ፊልም ቤት ወይም የምሽት ክለብ ዉስጥ የሚገኙ ሰዎችን መግደል የሚፈልግ ሰዉ የሚገድልበትን ጦር መሳሪያ በቀላሉ እንዴት በቀላሉ ማግኘት እንደሚችል ነዉ።የምንፈልጋት ሐገር የዚሕ አይነት መሆን-አለመሆንዋን መወሰን አለብን።ምንም አለማድረግም ራሱ ዉሳኔ ነዉ።»

ኦባማ ለቅሶ ለመድረስ ከነገ ወዲያ ኦርላንዶ ይሔዳሉ።በመጪዉ ሕዳር ለሚደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የዴሞክራቲኩ ፓርቲ እጩ ይሆናሉ ተብለዉ የሚጠበቁት ሒላሪ ክሊንተንም የፀጥታ ቁጥጥሩ መጠናከር፤ የጦር መሳሪያ ሽያጭም ገደብ ሊበጅለት ይገባል ባይ ናቸዉ።የተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ መብት ጉዳይ ሐላፊ ዘይድ ረአድ አል ሁሴይንም ዩናይትድ ስቴትስ የዜጎችዋን ደሕንነት ለመጠበቅ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለባት ብለዋል።ለፕሬዝደንታዊዉ ዉድድር የሪፐብሊካኑን ፓርቲ እጩነት ያገኛሉ የሚባሉት ዶናልድ ትራምፕ ግን ተቃራኒዉን ነዉ ያሉት።ቀኝ ፅንፈኛዉ ቱጃር ፖለቲከኛ ሙስሊሞች አሜሪካን እንዳይረግጡ መታገድ አለባቸዉ እያሉ ያቅራራሉ።ሰዉዬዉ ፕሬዝደንት ኦባም ሥልጣን እንዲለቁ እስከመጠየቅ ደርሰዋል።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic