የኦህዴድ ውሳኔዎች እና የተጨማሪ እስረኞች ፍቺ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 10.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኦህዴድ ውሳኔዎች እና የተጨማሪ እስረኞች ፍቺ

የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እና ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በማህበራዊ ድረ ገጾች የሳምንቱ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ትላንት ሐሙስ ተጨማሪ እስረኞች እንደሚለቀቁ መነገሩም በማህበራዊ መገናኛዎች ከፍተኛ ሽፋን አግኝቷል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:53

የኦህዴድ ውሳኔዎች እና የተጨማሪ እስረኞች ፍቺ

የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እና የአባል ድርጅቶቹ የስራ አስፈጻሚም ሆነ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች እንደቀደሙት ጊዜያት ቸል ተብለው የመታለፋቸው ነገር እየቀረ የመጣ ይመስላል፡፡ ስብሰባዎች ገና በመካሄድ ላይ እያሉ ጭምር እየሾለኩም ሆነ በይፋ የሚወጡ መረጃዎች የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ዋነኛ አጀንዳ ሲሆኑ ታይተዋል፡፡ ድርጅቶቹ በስብሰባቸው ማገባደጃ ላይ የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ደግሞ በፈርጅ በፈርጁ እየተቀመጡ የድጋፍ እና የትችት አስተያየቶች ሲያስተናግዱ ይስተዋላል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ለ10 ቀናት የዘለቀውን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ባለፈው ረቡዕ ጥር 29 ሲያጠናቅቅ የሆነውም ተመሳሳዩ ነው፡፡ 

የኦህዴድን አጠቃላይ ውሳኔዎች የተመለከቱ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች እጥር ምጥን ባሉ ቃላት ሀሳባቸውን ለማስቀመጥ ሞክረዋል፡፡ ብሩህ አለምነህ በፌስ ቡክ “ኦህዴድ ግስጋሴውን ቀጥሏል” ሲል አሰፋ ገዳሙ ደግሞ “ኦህዴድ ምጥን አልፎ ተገላግሏል” ብሏል፡፡ ሌላኛው የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ኬና ከበደ ኮሩ “ኦህዴድ አስደምሞኛል” በማለት መደነቁን ሲገልጽ ሁማኔ አለም በበኩሉ “ኦህዴድ ተራማጅነቱን በግልጽ አሳይቷል” ሲል ጽፏል፡፡ አሉላ መኮንን በፌስ ቡክ “በአለም የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ በአንድ ጊዜ የመንግስትንም፣ የተቃዋሚ ፓርቲንም ሚና የተጫወተ ፓርቲ ኦህዴድ ብቻ ይመስለኛል፡፡ እንግዳ እና አስገራሚ ነው” ሲል ስሜቱን አጋርቷል፡፡ 

ረመዳን ከድር ባለፈው ሳምንት የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ካጠናቀቀው ህወሓት ጋር በማነጻጸር “ተማሪው አስተማሪውን ሲበልጥ እንዴት ደስ እንደሚል - ልክ እንደ ኦህዴድ” ብሏል በፌስ ቡክ፡፡ ዳዊት ቲ. ብስራትም ሁለቱን የገዢው ግንባር አባል ፓርቲዎችን ማነጻጸር መርጧል፡፡ ኦህዴድ ስብሰባውን እያካሄደ ባለበት ባለፈው ሰኞ ረዘም ያለ አስተያየቱን በፌስ ቡክ ያወጣው ዳዊት “ኦህዴድ ምን እያደረገ ነው?” ሲል ጠይቆ ተከታዩን ምላሽ ራሱ ሰጥቷል፡፡ 

“ኦህዴድ ምን አደያደረገ ነው? የወጣቱን ድምፅ ሰምቶ፤ ለጥያቄያቸው መልስ እየሰጠ ነው፡፡ ከፌደራል መንግስት ጋር እየተወያየም፣ እየተከራከረም ለኦሮምያ ወጣቶች ስራ እየፈጠረ ነው፡፡ የብድር ስምምነቶች እየተደረጉ ነው፡፡ የአምራችነት ስራዎች ተላልፈው ለወጣቱ እየተሰጡ ነው፡፡ 'ብራቮ' ኦህዴድ!! የምትመራውን ህዝብ ልብ መግዛት እየጀመርክ ነው፡፡ ኦሮምያ ውስጥ ብዙ ተቃዋሚዎች አሉ፡፡ ቀስ በቀስ ነፃነታቸውን እያገኙ ነው፡፡ ኦህዴድ የህዝቡን እሮሮ አዳምጦ መፍትሔ ለመስጠት እየሞከረ ነው፡፡ በእኔ ግምት ከጥቂት አመታት በኋላ አንፃራዊ ዲሞክራሲ በኦሮምያ እናያለን፡፡ ትግራይ ውስጥ አንድ ሕወሓት አለች፡፡ ነፃነት ያለው የተቃዋሚ ድርጅት የላትም፡፡ የወጣቱ ድምፅ ተሰሚነት የለውም ብቻ ሳይሆን ‘እኛ ነን የምናውቅልህ’ የሚል አካሄድ ተጠናክሯል፡፡ የተለየ ሃሳብ የመቀበል ባህልዋ ጠፍቷል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በንፅፅር ዲሞክራሲ የሌላት በአምባገነኖች የምትመራ ትግራይ እናያለን፡፡ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት፣ ያለ አማራጭ እየተመራህ፣ ዲሞክራሲ አያብብም፤ እንዲያውም አይኖርም፡፡ የአንድ ድርጅት ሁለት አባላት እንዲህ አይነት ልዩነቶች እንዲኖራቸው ያደረገው ምክንያት ግልፅ እና ግልፅ ነው፡፡ ለህዝብ ጥቅም መቆም እና አለመቆም ነው” ሲል ልዩነቱን ለማስረዳት ሞክሯል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ካወጣው ረዘም ያለ መግለጫ ውስጥ የብዙዎቹን ቀልብ የገዙት አራት ጉዳዮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ኦህዴድ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሀገር እና በኦሮሞ ህዝብ የጋራ ጥቅም ላይ አብረውት እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረቡ ነው፡፡ በዚህ የድርጅቱ ውሳኔ ላይ በርካታ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች የድጋፍ አስተያየቶች ሰንዝረዋል፡፡ 

ዴጌባሳ ፈይሳ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ግን ሀሳቡ ዕውን ሆኖ እስኪያዩ ድረስ ለማመን የተቸገሩ ይመስላል፡፡ “ይህ በጥቅሉ የተቀመጠ ነገር ዝርዝር አቅድ ተዘጋጅቶለት ወደ ስራ ሲተገበር ለማየት ያብቃን፡፡ ወሬ ሆነው ከቀሩት እንዳይቀላቀል እንመኛለን” ብለዋል፡፡ በኦህዴድ ውሳኔ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት መስፍን ጎሴ ቤኮም ተመሳሳይ ሀሳብ በፌስ ቡክ ገጻቸው አንጸባርቀዋል፡፡ “ኦህዴድን የምመክረው ከፊቱ የሚጠብቀው ህዝብ ትግስቱ የተሟጠጠ እና በፖለቲካ ‘ውሳኔዎች’ እምነት ያጣ ህዝብ ነው። በሳምንት ሳይሆን በየሰዓታቱ የተገቡት ቃል መተግበራቸውን፣ ለውጥ መምጣቱን ማየት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ እናንተ ቃልን በጊዜው በማክበር እንዴት ለህዝብ ጥያቄ መልስ እንደሚሰጥ ‘ኢህአዴግን’ አስተምሩት። ወር የለንም፤ ከነገ ጠዋት ጀምሮ በየቀኑ የምንፈልገውን ለውጥ አሳዩን!  ‘ኢህአዴግን’ አቃታችሁ ብለን አንወቅሳችሁም፡፡ እናንተ እንኳን ማድረግ የምትችሉትን አድርጉ፡፡ አሁኑኑ!” ብለዋል፡፡

የድርጅቱ “የአብረን እንስራ” ጥያቄ ካልተዋጠላቸው አንዱ የሆኑት ሱልጣን አብዳ “ኦህዴድን በጭፍን ለሚደግፉ ሰዎች አንድ ጥያቄ አለኝ?” በሚል ርዕስ ተከታዩን በፌስ ቡክ አስፍረዋል፡፡ “ኦህዴድ በውጪ ሀገር ካሉ እንደ ኦዴግ እና ኦነግ ካሉ የኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር መስራቱን ለግዜዉ እንተወዉና በሀገር ውስጥ ካሉት እንደ ኦፌኮ ካሉት ተቀዋሚ ፓርቲዎች ጋር ‘በኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ ላይ’ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ ቢሆን ኖሮ የኦፌኮ አባላት የሆኑ የኦሮሞ ልጆች ከአመራራቸዉ ጭምር በእስር ቤት እየማቀቁ እያየ ዝም አይልም ነበር። ኦህዴድ የኢህአዴግ አካል እስከሆነ ድረስ በቁመናዉ ልክ የፌዴራል መንግሥት ላይ ጫና በማሳደር እንዲለቀቁ ሊያደርግ ይገባ ነበር፡፡ ይህ ትልቁ የቤት ሥራቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም በሺህዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች በዚህ መንግስት ለረጅም ጊዜ ታስረዋል፡፡ ከአገርም ተሰድደዋል፡፡

ዶ/ር መራራን ጨምሮ ለእስር የተዳረጉት፣ እስካሁንም ብዙዎች በእስር ላይ ያሉት፣ የኦሮሞ ህዝብን ጉዳይ ስላነሱ እኮ ነው፡፡  ተራ መብት ወንጀል ለሆነበት ለኦሮሞ ህዝብ ታዲያ ትልቁን የቤት ሥራ ያልተወጣው ኦህዴድ አሁን ‘በኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ ላይ’ ተባብረን ለመስራት እንፈልጋለን ሲል ምን ማለቱ ነው? ከእዚህ የበለጠ አሳሳቢ የኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ አለ? ወይስ የቀሩትን የኦሮሞ ልጆችን ሰብስቦ ለማሳሰር ነዉ? መልስ እፈልጋለሁ” ብለዋል ለደጋፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት።

ከኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔዎች ውስጥ ከየአቅጣጫው በርካታ አስተያየት ያጎረፈው የቀድሞው የድርጅቱ አባል እና የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጉዳይ ነው፡፡ በፈደራል መንግስት ሊያገኙት ይገባ የነበረውን ጥቅማ ጥቅም ለተነፈጋቸው ለዶ/ር ነጋሶ 30 ሺህ ብር ወርሃዊ የጡረታ ደመወዝ እንዲከፈላቸው እና ተሽከርካሪ እንዲገዛላቸው የማዕከላዊ ኮሚቴው ወስኗል፡፡ ያለባቸውን ህመም ከሀገር ውጭ በመጓዝ ጭምር እንዲታከሙ የህክምና ወጪያቸው እንዲሸፍንም ተሰማምቷል፡፡ 

ለውሳኔው አድናቆታቸውን ከገለጹ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች መካከል አንዱ የሆኑት ውብሸት ሙላት ጉዳዩን “ለህሊና የመታመን ዋጋ” ሲሉ ጠርተውታል፡፡ “የፌደራሉ መንግስት ፕሬዝዳንቱን ቢያዋርዳቸውም፣ ኦህዴድ የሀገራችንንም፣ የፕሬዝዳንቱንም ክብር እንዲመለስ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል” ሲሉ ለድርጅቱ ያላቸውን አድናቆት በፌስ ቡክ ገልጸዋል፡፡ “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” ሲሉ ውሳኔውን ያወደሱት ደግሞ ፌቨን አንቶኒዮስ ናቸው፡፡ 

Dr. Negasso Gidada

ቶሌራ ጫላ በፌስ ቡክ ገጻቸው “አዲሶቹ የኦህዴድ አመራሮች እየወሰዱት ያሉት እርምጃ ከቀን ወደቀን እየጨመረ እና የህዝብን ልብ እየገዛ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ከሁሉም በላይ ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ያደረጉትን ክብር ስሰማ ውስጤ ብዙ ነገር እንዲመኝ እና ከእነርሱም ብዙ እንደጠብቅ አድርጎኛል፡፡ በዚሁ ቀጥሉበት ብያለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡ “ህዝብንና መንግስትን ያገለገሉትን ማክበር ይልመድብን” ሲሉ የተንደረደሩት ሰለሞን ደቻሳ በበኩላቸው “ኦህዴድ ለዚህ ተግባር ፈር ቀዳጅ በመሆናችሁ ትመሰገናላችሁ፤ ልትኮሩም ይገባችኋል” ሲሉ ድርጅቱን አሞካሽተዋል፡፡ “የፓለቲካ ልዮነት ጠላትነት ሳይሆን የአመለካከት ልዮነት ብቻ ነው። ዲሞክራሲ የሚገነባው በዚህ ፅኑ እምነት እና መሰረት ላይ ብቻ ነው” ሲሉ በዶ/ር ነጋሶ ፎቶ ያጀቡትን መልዕክት ቋጭተዋል፡፡

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የኦሮምኛ ቋንቋ የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን ድርጅቱ እንደሚታገል ማስታወቁም ትኩረት ስቧል፡፡ ኦህዴድን ወክለው በኢህአዴግ ምክር ቤት ይሳተፉ የነበሩ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሌሎች እንዲተኩ መወሰኑ፣ አራት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ማገዱ እና ለአንደኛው ማስጠንቀቂያ መስጠቱም አነጋግሯል፡፡ ኦህዴድ ባስተላለፋቸው ውሳኔዎች ላይ በርካታ የድጋፍ አስተያየቶች በማህበራዊ ድረ ገጾች ቢነበቡም በእስር ላይ ከሚገኙ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና ከክልሉ ተወላጆች ጋር በተያያዘ ግን ተደጋጋሚ ትችቶች እየተሰነዘሩበት ይገኛሉ፡፡

ሆላ ጂ. ኤሬንሶ ይህንን የሚያንጸባርቅ አስተያየት በፌስ ቡክ ገጻቸው አጋርተዋል፡፡ “በቀለ ገርባ እና ሌሎች በግፍ ታስረው በይስሙላው ፍርድ ቤት ውሃ ቀጠነ ተብለው በየቀጠሮው የስድስት ወር እስራት እየተፈረደባቸው ያሉት የኦፌኮ መሪዎች ጉዳይ የኦሮሞ ህዝብን እና ኦህዴድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያቆራርጥ ይመስለኛል፡፡ በተለይም የሰለጠነ ሰላማዊ ተቃውሞና እምቢተኝነት ተምሳሌት የሆነው በቀለ ገርባ በሕመም እሥር ቤት ውስጥ መሰቃየት የኦሮሞ ህዝብ ስቃይ እየሆነ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ የሚሰማውን ህመም  ኦህዴድ የማይሰማው ከሆነ ወሬው ምን ያደርጋል? ከእነ ኦቦ ለማ መገርሳ መፍትሔውን መስማት ሳይሆን በድርጊት ተፈፅሞ ማየት እንፈልጋለን” ብለዋል።

የተቃዋሚው የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር የአቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ ትላንት ከተሰማው ተጨማሪ “እስረኞች ሊለቀቁ” ዜና ጋርም በድጋሚ ተነስቷል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትላንት ባስታወቀው መሰረት 746 ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወስኗል፡፡ ይፈታሉ ከተባሉት ውስጥ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌ ብቻ በስም የተጠቀሱ ሲሆን የሌሎቹ ማንነት እስካሁን ግልጽ አልተደረገም፡፡ እስረኞቹ ሊፈቱ ነው መባሉ ለብዙዎች ደስታን ቢፈጥርም የአቶ በቀለን መፈታት አጥብቀው የሚሹቱ ግን “ለምን በዝርዝሩ አልተካተቱም?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የዲንኮላስ ለሚፍ የፌስ ቡክ  አስተያየት ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡

“ሀገርን አስተዳድራለሁ የሚለው አካል ከህዝብ ጋር እልህ መጋባት የለበትም፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ከኦሮሞ ጋር እልህ ተጋብታለች፡፡ እነ እስክንድር ነጋ እና አንዱዓለም አራጌ ይፈታሉ መባሉን ስንሰማ ደስ ይለናል፤ መሆንም አለበት፡፡ አሁን አንዱን ፈትቶ ሌላውን አልፈታም ማለት የሚያሳየው ምን ታመጣላችሁ ዓይነት ፉከራ ነው፡፡ በቀለን አለመፍታት ከዚህ በፊት የኦሮሞ ህዝብ ለነጻነቱ ከከፈለው በላይ እንዲከፍል መጋበዝ ነው፡፡ ኦሮሞ ለእነዚህ መሪዎቹ ከዓይን ብሌን በላይ ይሳሳል፡፡ ምናልባት የኦሮሞ ህዝብ ለኢህአዴግ ይሰጥ የነበረውን ዕድል ከአሁን በኋላ አይሰጥም፡፡ ኦህዴድም ጎራውን መምረጥ ያለበት በእነዚህ የህዝብ መሪዎች ጉዳይ ላይ ይሆናል” ሲሉ ጽፈዋል ዲንኮላስ ለሚፍ። 

በእስረኞች ይፈታሉ መባል የተበረታቱ የሚመስሉት በረከት ሀሰን በትዊተር “ለሀገራችን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የይቅርታ ዘመን ይሁን” ብለዋል፡፡ መስፍን ደብሊው አስቻለውም ከእስረኞች መለቀቀቅ ጋር የተያያዘ መልዕከቱን በትዊተር አስፍሯል፡፡ “ኢትዮጵያ ከቤት ጸባችን የበለጡ አደጋዎች አሉባት፡፡ ሳይመሽ መደንገጥ አለብን፡፡ ተወቃቅሰን፣ ተካክሰን ሕመማችንን ካከምን የሌሎችም ተስፋ እንኾናለን፡፡ ታሪክም ያንን ሚና ሰጥቶናል፡፡ ገዢዎች ሆይ ፍቱና ተፈቱ፡፡ ክቡር ለነጻነት፣ ክቡር ህይወታቸውን ላጡ” ብሏል፡፡ ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ “ዛሬ እስክንድር ነጋ እና አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ ከ700 በላይ የፖለቲካ እስረኛ የሚያስፈታ የህዝብ ትግል፣ ነገ ታሳሪዎቹ መስዋዕት የከፈሉለት የተሻለ ሥርዓት የመገንባት አላማ ግቡን እንደሚመታ ተስፋ የሚሰጥ ነው” ብሏል በዚያው በትዊተር፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ሂሩት መለሰ 

Audios and videos on the topic