1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

የእነ ቀሲስ በላይ የችሎት ውሎ

ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2016

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍረቃ ኅብረት ቅርንጫፍ የሂሳብ ቁጥር አስመስሎ በተሰናዳ ሐሰተኛ ሰነድ ገንዘብ ለማውጣት ሞክረዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው የእነ ቀሲስ በላይ የክስ መዝገብ ላይ ዛሬ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ሲሰማ ዋለ ።

https://p.dw.com/p/4hpfx
Äthiopien Addis Abeba | Eingang | Bundesgerichtshof
ምስል Seyoum Hailu/DW

በእነ ቀሲስ በላይ ክስ አቃቤ ሕግ ምስክሮች ሲሰማ ዋለ

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍረቃ ኅብረት ቅርንጫፍ የሂሳብ ቁጥር አስመስሎ በተሰናዳ ሐሰተኛ ሰነድ ገንዘብ ለማውጣት ሞክረዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው የእነ ቀሲስ በላይ የክስ መዝገብ ላይ ዛሬ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች ሲሰማ ዋለ ። አቃቤ ሕግ አዘጋጅቶ ነበር ከተባለው አራት ምስክሮች አንዱን በማሰናበት የሦስቱ የምስክርነት ቃል ብቻ ይደመጥልኝ ያለው ከሳሽ አቃቤ ሕግ፤ ስላቀረባቸው ምስክሮች አግባብነት ለችሎቱ ካስረዳ በኋላ በተከሳሾች ጠበቆች ተቃውሞ ሳይገጥመው የሦስቱ ምስክሮች የምስክርነት ቃል ዛሬ ተደምጧል ።

የችሎቱ መሰየም

ዛሬ ረፋዱን አዲስ አበባ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተሰየመው ችሎት ላይ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት የፌዴራል ጊዜያዊ ታራሚዎች ልብስ ላይ ብጫ ጋቢ ከክህነት ቆባቸው ጋር ለብሰው ከሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር የቀረቡት  ቀሲስ በላይ መኮንን  ከሳሽ አቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን የሰው ምስክሮች ሲያደምጡ ውለዋል፡፡ ተከሳሾቹ በተናጥል ያቁሙአቸው ጠበቆቻቸውም ጋር ነው በዛሬው ችሎት ላይ የታደሙት፡፡ በክስ መዝገቡ በአራተኛ እና አምስተኛ ተከሳሽነት የተጠቀሱት ተጠርጣሪዎች ግን እስካሁንም ችሎቱ ባዘዘው መሰረት ተገኝተው በፖሊስ ተይዘው ባለመቅረባቸው ችሎቱ ለጊዜው የክስ መዝገባቸው ተዘግቶ አቃቤ ህግ ሰዎቹ ስገኙ ክሱን ሊያስነሳው እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

ዛሬ የችሎቱን መጀመር ተከትሎም ሦስት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ህብረት ሰራተኞችን በምስክርነት ያቀረበበትን አግባብነትና ምክንያታዊነት አቃቤ ህግ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ በምስክሮቹ አግባብነት ላይ ተቃውሞ ካላቸው የተጠየቁት የተከሳሾች ጠበቆችም በዚያ ላይ የሚያነሱት ጥያቄ አለመኖሩን አስረድተው ችሎቱ ወደ ምስክሮቹ ቃል ማድመጥ ገብቷል፡፡

ሰፋፊ ጊዜ ተሰጥቶ በርካታ የመስቀለኛ እና የማጣሪያ ጥያቄዎች ከከሳሽ እና ተከሳሽ ወገኖች እንዲሁም ከችሎቱ የተሰነዘረባቸው ሁለት ምስክሮች በጠዋቱ የችሎት ጊዜ ስደመጡ፤ ጊዜው ባለመብቃቱ አንድ ቀሪ ምስክር ግን ከሰኣቱን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከቀረቡት ምስክሮችም የደንበኞች ባለሙያ እና የቅርንጫፉ የውስጥ ቁጥጥር የባንክ ባለሞያ እንደሚገኙ ተገልጾ ይህም የሆነው በእለቱ ለባንኩ ቀረበ ስለተባለው ሀሰተኛ ሰነድ ላይ ገጠመን ያሉትን ሁኔታ እንዲያስረዱ ነው ተብሏል፡፡

የምስክሮቹ ቃል አሰማም ሂደትና ጭብጦቹ

ምስክሮቹም ሚያዚያ 07 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ገደማ  ቀሲስ በላይ መኮንን  ባጠቃላይ ስምንት ገጽ የሆነው አራት የክፍያ መጠየቂያ ሰነዶች ይዘው ለባንኩ ማቅረባቸውን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በነዚህ አራት የክፍያ መጠየቂያ ሰነዶችም የተለያዩ መጠን ያላቸው ክፍያ መጠየቁንና አጠቃላይ የተጠየቀውም የክፍያ መጠን ስድስት ሚሊየን ሃምሳ ዶላር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰነዱም የሚጠይቀው ከአፍሪካ ህብረት የሂሳብ ቁጥር በተናጥል በአራት ሰነዶች ወደ ተጠየቁ የሂሳብ ቁጥሮች እንዲገባ ነው ተብሏል፡፡

ምስክሮቹ በቀሲስ በላይ አማካኝነት ለባንኩ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገለግሎት ኦፊሰር የቀረበው የክፍያ ሰነድ የተለያዩ አጠራጣሪ ነገሮች ያሉት መሆኑ ሀሰተኛ የክፍያ መጠየቂያ ሰነድ ይሁን አይሁን እንዲጣራ በየደረጃው ላሉ የባንኩ ኃላፊዎች እንዲሰጥና እንዲጣራ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ምስክሮቹ የሰነዱን አቀራረብ አጠራጣሪ ካደረገው ጉዳይ አንዱ ሁል ጊዜም በተለመደው አሰራር ሰነዱ በሚታወቁ የህብረቱ ጉዳይ አስፈጻሚ በኦፕሬሽን ወይም ብዝነስ ማናጀር በኩል ማቅረብ ስገባቸው በተገልጋይ በደንበኞች አገልግሎት በኩል መቅረቡ፣ የተጠየቀው የገንዝብ መጠን እጅግ ከፍ ያለ መሆኑ፣ ሰነዱ የቀረበበት ወረቀትና ፊርማው እንግዳ ነግር መሆኑ የሰነዱን ትክክለኛነት እጅጉን አጠራጣሪ በማድረጉ ባለሙያዎቹ ሰነዱን ወደ ኃላፊዎቻቸው መርተው ሀሰተኛ ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡

ቀሲስ በላይ
ቀሲስ በላይ ከመከሰሳቸው በፊት የተነሳ ፎቶግራፍ፤ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

ለምስክሮቹ በአቃቤ ህግ ከቀረበላቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ በተከሳሾች ጠበቆች በኩልም በርካታ የመስቀለኛ ጥያቄዎች ቀርበው ችሎቱም የማጣሪያ ጥያቄዎች ሰንዝሮላቸው መልሰዋል፡፡ ችሎቱም ዛሬ በጠዋትና ከሰዓት መርሃግብሮች የሶስቱን ምስክሮች ቃል አድምጦ ካጠናቀቀ በኋላ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሃምሌ 18 ቀን 2016ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡

የክሱ መነሻ እና አጠራጣሪው ድርጊቱ

ሚያዚያ 07 ቀን 2016 ዓ.ም የአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብ "ከኅብረቱ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ" በተባሉ ሀሰተኛ ሰነዶች በመጠቀ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከህብረቱ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ ሒሳብ ለማዘዋወር ሲሞክሩ ተገኝተዋል በሚል በፖሊስ ተይዘው ክስም የተመሰረተባቸው ሊቀ ዐዕላፍ  ቀሲስ በላይ መኮንን እና ሌሎች ተከሳሾች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የሙስና ወንጀል ችሎት «በከባድ የአታላይነት የሙስና ወንጀል እና ሰነዶችን አስመስሎ የማዘጋጀት» ወንጀል ተጠርጥረው የክስ ሂደት ላይ ነው፡፡

ክሱ ከአስር ዓመት በላይ የሚያስፈርድ ከባድ ክስ ነው በሚል ከዚህ በፊት የዋስትና መብት ማስከልከሉም ተከሳሾች ማረሚ ቤት በመውረድ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱም ይታወሳል፡፡ የአፍሪቃ ኅብረት በሚያዚያ ወር ባወጣው ፋዊ መግለጫ "በሀሰተኛ ሰነድ” ከህብረቱ ሂሳብ ገንዘብ የማውጣት ጥረት መክሸፉንና "የተጭበረበረ ሰነድ” ወደ ባንኩ ያመጡት ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ላይ መሆናቸውን፤ ነገር ግን በህብረቱ ሂሳብ ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ማሳወቁም አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር