የእነ ሐብታሙ አያሌው የፍርድ ቤት ውሎ  | ኢትዮጵያ | DW | 02.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የእነ ሐብታሙ አያሌው የፍርድ ቤት ውሎ 

የእነ ሐብታሙ አያሌው የፍርድ ቤት ውሎ 

የኢትዮጵያ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት በሽብር ተከሰው ይግባኝ የተጠየቀባቸው የቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ፍትህ ፓርቲ አባል አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና የአረና ትግራይ አባል አቶ አብርሃ ደስታ እንዲከላከሉ ዛሬ ብይን ሰጠ። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በእነ አቶ ሐብታሙ አያሌው የክስ መዝገብ ከተካተቱ አምስት ተከሳሾች መካከል ሶስቱን በነፃ አሰናብቷል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:04
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:04 ደቂቃ

አብርሐ ደስታ እና ዳንኤል ሺበሺ ተከላከሉ ተባሉ

በሽብር ወንጀል ተከሰው ከሁለት አመታት በላይ በእስር የቆዩት የቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ ፓርቲ ፖለቲከኛ አቶ ሐብታሙ አያሌው  ዛሬ ድብልቅል ስሜት ተሰምቷቸዋል።አቶ ሐብታሙ ጤናቸው የተቃወሰው በሽብር ተከሰው ለእስር ከተዳረጉ በኋላ መሆኑን ይናገራሉ ። በሥር ፍርድቤት ከቀረበባቸው ክስ ነፃ የተባሉት አቶ ሐብታሙ ከእስር ከተፈቱም በኋላ ህመማቸውን በቅጡ መታከም አለመቻላቸውን ተናግረዋል። አቶ ሐብታሙ አቃቤ-ሕግ ይግባኝ በመጠየቁ ምክንያት የሕክምና ጉዞ እንዳያደርጉ እገዳ ተጥሎባቸው ቆይቷል። 
የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ዓርብ ኅዳር 23, 2009 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በእነ ሐብታሙ አያሌው ከተካተቱ አምስት ተከሳሾች መካከል ሶስቱን በነፃ አሰናብቷል። በሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም. ለእስር የተዳረጉት እና የሽብር ክስ ከተመሰረተባቸው ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መካከል የአረናው አብረሐ ደስታ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገቢራዊ ከሆነ በኋላ ለእስር የተዳረጉት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ግን እንዲከላከሉ ብይን ተላልፏል። በፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ከተበየነላቸው በኋላ አቃቤ ሕግ ይግባኝ ከጠየቀባቸው ተከሳሾች መካከል አንዱ አቶ አብርሐ ደስታ ችሎቱን የተከታተሉት መቀሌ ላይ ሆነው ነው። በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ እንዲከላከሉ ብይን የተላለፈባቸው አቶ አብርሐ ደስታ ጉዳዩ በሥር ፍርድ ቤት መታየት ሲጀምር ተመልሰው ሊታሰሩ እንደሚችሉ ጥርጣሬ አላቸው።
 አቶ አብርሐ ደስታ እንዲከላከሉ የተበየነባቸው መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ካደረገ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉት ቃለ-መጠይቅ ተጠቅሶ ነው። አቶ አብርሐ ክሱ «ህግን ለመጣስ ተቃርበዋል» ወደ ሚል መቀየሩን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በተለያዩ የጤና ችግሮች አልጋ ይዘው የቆዩት አቶ ሐብታሙ አያሌው አገግመው የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ ታድመዋል። እርሳቸው እንደሚናገሩት ተከላከሉ የተባሉት የአቶ አብርሐ እና አቶ ዳንኤል ቀድሞ «የሽብር ተግባር ማቀድ፤ማሴር እና ማነሳሳት» የሚለው ክስ አሁን ተቀይሯል።
አቶ ሐብታሙ ከጉዞ ያሳገዳቸው እና አቃቤ-ሕግ ይግባኝ የጠየቀበት የክስ መዝገብ በመዘጋቱ ህክምና የማግኘት እድላቸውን አስፍቶታል ብለው ተስፋ አድርገዋል። አቶ ሐብታሙ የሕክምና ጉዟቸውን ለማድረግ የተጣለባቸው እግድ መነሳቱን የሚገልፅ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ከፍርድ ቤት መፃፍ ይኖርበታል።


እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic