1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

የእነአቶ ዮሐንስ ቧያለው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሆነ፣ የእነ ፕሮፌሰር ዝናቡ ዋስትና አልተከበረም

ረቡዕ፣ ሰኔ 12 2016

በእነ አቶ ዮሃንስ ቧያሌው የክስ መዝገብ ዛሬ ልደታ ፀረ ሽብር ችሎት የቀረቡ ተከሳሾች ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ፣ የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት የዋስትና መብታቸውን የሚነፍግ ነው በሚል ውድቅ ተደረገ። የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራን ጨምሮ በገንዘብ ዋስትና ከእሥር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት የወሰነላቸው ዋስትናው አልተከበረላቸውም።

https://p.dw.com/p/4hG5C
Äthiopien Oberlandesgericht Lideta
ምስል Seyoum Getu/DW

የእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ፣ የእነ ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ የተፈቀደ ዋስትና ዛሬም አልተከበረም

 

የእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

 

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሃንስ ቧያሌው 1ኛ ተከሳሽ በሆኑበት የክስ መዝገብ ሥር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስትያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል  ዶክተር ካሳ ተሻገርን ጨምሮ የጋዜጠኞችና የሌሎችንም የክስ መዝገብ የሚመራው የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት፤ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄው ውድቅ አድርጓል፣ የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ለማድመጥ ደግሞ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ከጠበቆቻቸው አንደኛው ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።እሥር ፣ የሽብር ክስ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማብቃት

 

ባለፈው ሳምንቱ ችሎት ከተከሳሾች መካክል አቶ ዮሃንስ ቧያሌው እና አቶ ክርስትያን ታደለ ማንነትን መሰረት ያደረገ የመብት ጥሰት እየደረሰባቸው መሆኑን፣ በዚህም የሕሊና ጉዳት እንደሚደርስባቸው እና በአማራነታቸው ምክንያት ከሌሎች ታራሚዎች በተለየ መብታቸው እየተጣሰ መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ በማረሚያ ቤቶቹ አስተዳደሮች ላይ ተገቢ ቅጣት እንዲጥል ጠይቀው ነበር።

 

የእነ ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ የተፈቀደ ዋስትና ይግባኝ ተጠይቆበታል

 

የዳኛ መዶሻ በፍርድ ቤት
የዳኛ መዶሻ በፍርድ ቤት ምስል picture-alliance/dpa/U. Deck

የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራን ጨምሮ በአዋሽ አርባ ታሥረው ቆይተው ወደ አዲስ አበባ የተዛወሩ ዘጠኝ ሰዎች በገንዘብ ዋስትና ከእሥር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ሰኞ እለት የወሰነ ቢሆንም ፌዴራል ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቁ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለአርብ ቀጠሮ ሰጥቷል። የአቶ ታዬ ደንደዓ እና የእነ ቀሲስ በላይ የችሎት ውሎ

የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ዛሬ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት፤ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው የወሰነላቸው ዘጠኙ ሰዎችን ከእሥር እንዲወጡ ለዋስትናው የተጠየቀውን ገንዘብ ከፍለው ነበር።

 

በሌላ በኩል በእነ ዶ/ር ወንዶሰን አሰፋ መዝገብ የተከሰሱ ሰዎች ትናንት ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ አሻሽሎ እንዲቀርብ በሚል ለሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል።በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው 51 ተከሳሾች ችሎት

ለበርካታ ወራት በእሥር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መካከል የተወሰኑት መፈታታቸውን በበጎ እንደሚመለከተው የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተማጋቾች ማዕከል፤ መንግሥት የተፈፃሚነት ጊዜው ባበቃው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት "አለአግባብ በሰብዓዊ መብት ሥራቸው ምክንያት በእሥር የሚገኙትን ጋዜጠኞች ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በሙሉ እንዲፈታ" እና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ እና ሌሎች መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያስችል የፖለቲካ እና የሲቪክ ምህዳር እንዲፈጠር የድርሻውን እንዲወጣ ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ