የእስያ የጦር መሣሪያ ሽያጭና አቅርቦት | ዓለም | DW | 17.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የእስያ የጦር መሣሪያ ሽያጭና አቅርቦት

ከዓለም የጦር መሣሪያ በመግዛት ብዛት ቻይና ፣ህንድ እና ፓኪስታን የመጀመሪያውን ስፍራ ይዘዋል ይላል የዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ንግድን የሚመረምረው «የሰላም ጥናት ተቋም» በምህፃሩ «ሲፕሪ» ዛሬ ያወጣው ዘገባው።

«የሰላም ጥናት ተቋም» በምህፃሩ«ሲፕሪ» ተመራማሪ የሆኑት እና ዘገባውን ካጠናቀሩት መካከል አንዱ የሆኑት ፒተር ቬዘማን እንዳመለከቱት፣ የጦር መሣሪያ፣ ማለትም፣ የጦር መርከቦች፣ባህር ሰርጓጅ መርከቦች፣ የጦር አይሮፕላኖች፣ ታንኮች እና ሮኬቶችን ሽያጩ በወቅቱ እርግጥ ከቁጥጥር ውጪ ባይሆንም ችግር ይዞ መምጣቱ አይቀሬ ነው ። በጥናቱ መሠረት ህንድ ባለፉት አምስት አመታት ብቻ በ111 ከመቶ የጦር መሣሪያ ግዢዋን ከፍ አድርጋለች። ህንድ በጀቷን ከፍ ካደረገች ደግሞ ቻይና እና ፓኪስታን መከተላቸው አይቀርም ይላሉ ቬዘማን። በዚህ በጎርጎሮሲያኑ 2014 የቻይና ሸንጎ የጦር መሣሪያ ባጀቱን በ12 ከመቶ ከፍ ለማድረግ ወስኗል። ከሩሲያ መሣሪያ የምትሸምተው ቻይና ግዢዋን ብቻ ሳይሆን ያጠናከረችው የጦር መሣሪያ ፋብሪካዋንና እና በንግድ ወደ ውጭ የምትልከውን የጦር መሳሪያ መጠንንም ጭምር ነው። ታድያ እንደ ፓኪስታን፣ ባንግላድሽ፣ እና ማይናማርን የመሳሰሉ ሀገራት የጦሩን መሳሪያ ተፎካካሪ ከሆነችው ቻይና መሸመታቸው አይቀርም ነው የሚለው የሲፕሪ ዘገባ።

« የቻይና ጠመንጃዎች ከዚህ ቀደም ዘመናዊ ያልሆኑ፣ ርካሽ አብዛኛውን ጊዜ ጥራት የጎደላቸው እና የሚመከሩ አልነበሩም። ይህ ግን አሁን ተቀይሯል።»ይላሉ ቬዘማን። የጦር መሣሪያ ፋብሪካዎችን ምርት ቀስ በቀስ በዓለም አቀፍ ዘንድ ስኬታማ እየሆኑ ከመጡት የኤሎክትሮኒክስ መገልገያዎች ጋር ያመሳስሏቸዋል። ነገሩ አስጊ ነው ይላሉ። ቦን- ጀርመን የሚገኘው የዓለም አቀፍ የሰላም እና የግጭት መፍትሄ ተቋም በምህጻሩ«ቢክ» የሳይንስ ተመራማሪ ያን ግሬበ።

« ምክንያቱም ቻይና ልክ እንደ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት፣ ዮናይትድ ስቴትስ ወይም ካናዳ መቆጣጠሪያ የላትም። ከዚህ በስተጀርባ የጦር መሣሪያ የመሸጥ ትልቅ ፖለቲካዊ ፍላጎት አለ። በርግጥ ይህ የቻይና መንግሥት ፖለቲካዊ መሣሪያ ነው።»በማለት እንደ ምሳሌ ቻይና ለማይናማር የሸጠችውን የጦር መሣሪያ ጠቅሰዋል። ይህ ብቻ አይደለም «ቻይና ወደፊት የመግዛት አቅም ለማይችሉ ሀገራትንም መሣሪያ መሸጧ አይቀርም ።»

«ቢክ» ስቶኮልም እንደሚገኘው የጥናት ተቋም « ሲፕሪ» ሁሉ በየዓመቱ የዓለም የጦር መሣሪያን ሽያጭ እና አቅርቦትን በተመለከተ ዘገባ ያወጣል። አጠቃላይ የእስያ አህጉር የጦር መሣሪያ ግዢን በተመለከተ ከዓለም የመጀመሪያ እንደሆነች ያን ግሬብም ይጠቁማሉ። አዲስ በወጣው የ«ሲፕሪ» ዘገባ መሠረት ሩስያ የጦር ማምረቻ ፋብሪካዎቿን የበለጠ ለማጠናከር ትፈልጋለች።

«የሞስኮ መንግሥት ባለፉት አመታት በተደጋጋሚ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለመሣሪያ ፋብሪካዎች እንዳዋለ አስታውቋል። ይህም የሚውለው ለእድሳት፣ አዲስ ቴክኖሎጂ ለመፍጠር እና አዲስ የጠመንጃ ዘይቤ ለመፍጠር ነው።»

ከቀዝቃዛው ጦርነትም በኋላ ሩሲያ ከአለም በጦር መሣሪያ ሽያጭ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘችው አሁንም ዮናይትድ ስቴትስ ናት። የሩስያ የጦር መሣሪያ ንግድ ኢኮኖሚያዊ ገቢ ላይ ብቻ የተመረኮዘ አይደለም ይላሉ ቬዘማን ፤ ሩሲያ ፖለቲካዊ ትስስርንም ለመፍጠር ትፈልጋለች።ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠሯት ሀገር ሶርያ ናት። ሩሲያ ምንም እንኳን ኤኮኖሚያw ጥቅም ባያመጣላትም፣ ለሶርያ ፕሬዚዳንት ባሽር አል አሳድ አሁንም የጦር መሣሪያ ለማቀበል ፍቃደኛ እንደሆነች ገልፃለች።

በዚሁ በዛሬው የ« ሲፕሪ» ዘገባ መሰረት አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራትም ገበያተኞቻቸውን ሌላ ቦታ መፈለግ ይኖርባቸዋል። የፈረንሣይ የጦር ፋብሪካዎች በቻይና ፋብሪካዎች ተቀድመዋል። ባለፏት አምስት አመታት የፈረንሳይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ በ30 በመቶ ቀንሷል። ጀርመንም ብትሆን ወደውጭ ሀገር የምትሸጠው ከባድ የጦር መሣርያ ምርት በ24 ከመቶ ዝቅ ብሏል። ለዚህ አንዱ ምክንያት ሀገራቱ የጦር መሳሪያ ምርታቸውን በመቀነሳቸው ነው። ቻይና በጦር መሳሪያ ሽያጭ ከጀርመን ቀጥላ ከዓለም የ4ኛውን ስፍራ ይዛለች። በዘገባው እንደተጠቀሰው፣ ከአፍሪቃ የጦር መሣሪያ በመግዛት አልጄሪያ፣ሞሮኮ እና ሱዳን ቀዳሚውን ቦታ ይዘዋል።

ሐሌ ጄፕሰን

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች