የእስያና የአዉሮጳ ሐገራት ጉባኤና ዉጤቱ | ኤኮኖሚ | DW | 12.09.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የእስያና የአዉሮጳ ሐገራት ጉባኤና ዉጤቱ

ማሕበሩ እስካሁን የሚጠበቅበትን አላደረገም።መኖሩ ግን ካለመኖሩ ብዙ መሻሉ ሊያነጋግር አይገባም።

የእስያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ሐገር (ጃፓን) ጠሚ ንግግር ሲያሰሙ

የእስያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ሐገር (ጃፓን) ጠሚ ንግግር ሲያሰሙ


ፊንላድ-ሔልሲንኪ ለሁለት ቀን የመከረዉ የአዉሮጳና የእስያ ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ብዙም ዉጤት ሳያታይበት ትናንት ተጠናቋል።የሠላሳ ስምንት ሐገራት መሪዎችና ተወካዮች የተካፈሉበት ጉባኤ ሁለቱን ክፍለ-አለማት ለማቀራረብ የሚረዳ ተጨባጭ ዉሳኔና ስምምነት አልታየበትም። ጉባኤዉን የተከታተለዉ የዶቼ ቬለዉ ባልደረባ Bernd Riegert እንደሚለዉ ግን ጉባኤዉ የተፈለገዉን ዉጤት ባያመጣም የሁለቱ ክፍለ-አለማት መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተዉ መነጋጋራቸዉ ራሱ ለወደፊቱ መቀራራብ ጠቃሚ ነዉ።የRiegertን አስተያየት ነጋሽ መሐመድ ተርጉሞታል።

እርግጥ የሁለት ቀኑ ጉባኤ ያመጣዉ ተጨባጭ ዉጤት የለም።ASEM በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ ማሕበር የሚያስተሳስራቸዉ የሰላሳ-ስምንቱ ሐገራት ርዕሣነ-ብሔራትና መራሒያነ መንግሥታት እንዲሕ እንደ ሰሞኑ ፊት ለፊት ተገናኝተዉ መነጋገራቸዉ ግን በሁለቱ ክፍለ አለማት ዘንድ ዉይይት፣ የሐሳብ ልዉዉጥን ለማዳበር ጠቃሚ፣ አስፈላጊ፣ ተገቢም ነዉ።ፊት ለፊት-በሪገርት ቃል-አራት አይኖች መታየታቸዉ ራሱ ፖለቲካዊ ድርድር-ዉይይትን ለማዳበር፣ አንዱ የሌላዉን አቋምና እምነት የማድመጥና የራሱን የማስደመጥ ባሕልን ለማጎልበትም ይበጃል።

ጉባኤዉ የተደረገዉ ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች የተጠቃችበት አምስተኛ አመት በተዘከረበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ሁለቱ ክፍለ-አለማት ሥለ አደጋዉ እንዲመክሩ፣ ያን መሰል አደጋ እንዳይደገም ለመከላከል የጋራ ሥልት እንዲቀይሱ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ-የሆነዉ።ብዙዎቹ ተቺዎች ጉባኤዉን በተናጥል ፣ ASEM ን በጥቅሉ ጥርስ የለሽ፣ የወረቀት ላይ ነብር አልፎም ተርፎም ጊዜ ማባከኛ ሥብስብ እያሉ ይወቅሷቸዋል።እንደ እዉነቱ ከሆነ ማሕበሩ ገና ዳዴ የሚል ጨቅላ ነዉ።ምንም ካለማድረግ ትንሽ መሞከር ደግሞ በብዙ እጅ መሻሉ ሊካድ አይገባም።

የአዉሮጳና የእስያ ፖለቲካ የሁለቱ ክፍለ-አለማት ምጣኔ ሐብት ከረጅም ጊዜ በፊት የደረሰበትን የግንኙነት ደረጃ መከተል ይገባዋል።የሁለቱ ክፍለ-አለማት ምጣኔ ሐብት በጅጉ ተሳስሯል።ከአዉሮጳ ወደ እስያና በተቃራኒዉ የሚደረዉ የሸቀጥና የንግድ ልዉዉጥ በጣም ጠንካራ ነዉ።ጠንካራዉ የምጣኔ ሐብት ትስስር ለፖለቲካዉ መቀራረብ መሠረት ሊሆን ይገባል።በሌላ አባባል የፖለቲካዉ መቀራረብ የምጣኔ ሐብቱን ፈለግ መከተል አለበት።የሔልሲንኪዉ ጉባኤ የፖለቲካዉን ትስስር እንደ ምጣኔ ሐብቱ ለማጎልበት ሁነኛ እርምጃ አልታየበትም።


ጉባኤዉ የንግድ ልዉዉጡ የድሆች ሐገራት ሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና ለመለወጥ የሚረዱ ስምምነቶች ሊደረጉበት በተገባም ነበር።የሔልስንኪ ጉባኤተኞች የአለም ንግድ ድርጅት ሥራና አሠራር የአብዛኛዉን በተለይም የደሐዉን ዓለም ፍላጎት የሚያረካ አይነት እንዲሆን የሚሹ መሆናቸዉን በሰፊዉ ሲናገሩ ነበር።በተመሳሳይ ጊዜ ብራዚል ዉስጥ ተስይሞ የነበረዉ የአለም ንግድ ድርጅት ሥብስሰባ ተሳታፊዎች ባንፃሩ በዚሁ ርዕስ ላይ መግባባት አቅቷቸዉ ነበር።አስገራሚዉ ነገር በብራዚሉ ስብሰባ ከተሳተፉት ባለሥልጣናት ገሚስ ያሕሉ በሔልሲንኩ ጉባኤ የተሳተፉት ሐገራት ተወካዮች መሆናቸዉ ነዉ።

ሰብአዊ መብትን በተመለከተም የማይታረቁ እምነቶች ሲፋተጉ ታይተዋል።አዉሮጶች ከቻይኖች ጋር ባንድ አዳራሽ ተሰብስበዉ መምከር-መነጋገሩን አልጠሉትም።ማይናሚር ግን የሐገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት ሰብአዊ መብት ይረግጣል በሚል ሰበብ በጉባኤዉ እንድትሳተፍ አልፈቀዱላትም።ቻይና ከማይናሚር የምትለየዉ በምጣኔ ሐብቱ እጅግ የደረጀች በመሆንዋ ብቻ እንጂ ኮሚንስታዊ ሥርአትዋ ሰብአዊ መብት የሚከበርበት ሆኖ አይደለም።አዉሮጶች ቻይናን አቅርበዉ ማይናሚርን ማራቃቸዉ ለምጣኔ ሐብታዊዉ ጥቅማቸዉ ሲሉ ተቃራኒ አቋም መያዛቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ።

የአዉሮጳ ሐገራት በምጣኔ ሐብት የተሳሰሩ፤ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመሩ፣ በሁሉም መስክ የተቀራረቡ ናቸዉ።እስያዎች ባንፃሩ የምዕራቡን ዲሞክራሲ የሚከተሉ፣ በኮሚንስቱ መርሕ የሚገዙ፣ በምጣኔ ሐብቱ እድገት የተራራቁ አልፎ-ተርፎም ታሪካዊ ቅራኔያቸዉን ሙሉ በሙሉ ያላስወገዱ ሐገራት ቅይጦች ናቸዉ።የጋራዉ ማሕበር በተራራቀ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሐገራት ለማቀራረብ ብዙ መስራት፣ ሕንድና ፓኪስታንን ከስብስቡ መቀየጥ ይኖርበታል።ማሕበሩ እስካሁን የሚጠበቅበትን አላደረገም።መኖሩ ግን ካለመኖሩ ብዙ መሻሉ ሊያነጋግር አይገባም።