የእስራኤል ፍልስጤሞች ግጭት | ዓለም | DW | 16.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የእስራኤል ፍልስጤሞች ግጭት

ትናንት የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር፤ ዛሬ ደግሞ የኢጣሊያዋ አቻቸዉ ፌደሪካ ሞግሔሪኒ እየሩሳሌም-እየደረሱ ተመልሰዋል።የፍልጤም ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ የግብፅና የቱርክ መሪዎችን ድጋፍ ለመጠየቅ ሁለቱን ሐገራት ይጎበኛሉ።ግድያዉ ቀጥሏል።

የእሥራኤል ጦር ጋዛ ሠርጥን መደብደቡን ዛሬም ለዘጠነኛ ቀን እንደቀጠለ ነዉ።የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ወደ ደቡባዊ እስራኤል ሮኬት ማወንጨፋቸዉን አላቋረጡም።ተፋላሚ ሐይላት የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲያደርጉ ግብፅ አቅርባዋለች የተባለዉ ሐሳብ ዉድቅ ከሆነ ወዲሕ መቶዎችን የገደለዉ ግጭት ይቆማል የሚለዉ ተስፋ ተሟጥጧል።ይሁንና የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ ለግጭቱ መፍትሔ ፍለጋ የግብፅና የቱርክ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ወደ ሁለቱ ሐገራት ለመሔድ ተዘጋጅተዋል።የጀርመንና የኢጣሊያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮችም አካባቢዉን ጎብኝተዋል።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

ጋዛ-ትንሽ ሠርጥናት።360 ስኩዬር ኪሎ ሜትር።በሥሟ የተሰየመችዉ ዋና ከተማዋ-ደግሞ ከትንሽም ትንሽ።ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ፍልስጤማዊ ተፋፍጎ-ይኖርባትል-ከተማይቱ።ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ደግሞ በተፋፈገዉ ፍልስጤማዊ ቤት፤መስሪያ ቤት፤ መስጊድ፤ ሕንፃ ላይ የእስራኤል ቦምብ-ሚሳዬሎች ይወርዱባቸዋል።

ትንሺቷ-ግዛት፤ ትንሺቱ ከተማ የዓለም ምርጥ ጦር እሳት አያወረደባት-እስከሬን ይለቀምባታል።ደም ታጎርፋለች።2008-እንዲያ ነበር።2009፤ 2012፤ ዘንድሮም።ትናንት ማታ ብቻ የእስራኤል የጦር አዉሮፕለኖች ትኒሺቱን ከተማ አርባ ሥፍራ ደብድበዋታል።ባለፉት ዘጠኝ ቀናት ሁለት መቶ አሥራ-ሁለት ፍልስጤማዉያንን ገድለዋል።1500 አቁስለዋል።

«ምን እናድርግ» ይላሉ ለጡረታ ሳምንት የቀራቸዉ ፕሬዝዳንት ሼሞን ፔሬዝ «ምርጫ አጥተን» ነዉ።«ምርጫ የለንም።ሐሳብ አይደለም።ያደረግ ነዉ ምርጫችን ሆኖ አይደለም፤ ምርጫ እጥተን ነዉ።በኛ ላይ ከተኮሱ፤ እናቶቻችንና ልጆቻችን ሙሉ ሌሊት መተኛት ካልቻሉ ምን ማድረግ እንችላለን»የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ወደ እስራኤል ሮኬት ያወነጭፋሉ።እስከ ትናንት አንድ ሺ ሁለት መቶ ተኩሰዋል።የገደሉት ግን-አንድ ሰዉ ነዉ።

ፔሬስ ዘጠና አንድ-አመታቸዉ ነዉ።ነብስ ካወቁበት ጀምሮ ከእስራኤል ፖለቲካ ተለይተዉ አያዉቅም።በዚሕ ሁሉ ዘመን- ከግጭት-ግድያ በስተቀር እሳቸዉ እንዳሉት«አማራጭ አላገኙም» ጠቅላይ ሚንስትር ቢንያሚን ኔታንያሁ ጦራቸዉ ጋዛ ላይ የሚፈፅመዉን ድብደባ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ትናንት ካስታወቀ ወዲሕ መቶ ሺሕ ፍልስጤማዉያን ቤታቸዉን ለቀዉ እንዲሰደዱ አዟል።ወዴት? እንዴት ምን መሔጃ አለን? ጠየቁ እሳቸዉ?«ወዴት እንሒድ፤ መሔድ አንችልም። እንዴትስ ነዉ የምንሔደዉ? አዉቶቡስ የለ።መኪና የለ?»

ጋዛ-ዙሪያ ገባዋ በእሥራኤል ጦር ተከርችሟል።መኪና-ቤንዚን አይደለም ምግብ መድሐኒትም የለም።የግብፅ መንግሥት እስራኤልና ሐማስን የተኩስ አቁም ዉል ለማዋዋል-ማቀዱ ተሰምቶ ነበር።ዕቅዱን የያዘዉ ደብዳቤ ለእስራኤል ተስጥቶ ሲመከር-ሲዘከርበት ሐማስ «አልደረሰኝም» አለ።በዚሕም ምክንያት እስራኤል በራሷ ጊዜ ለሰዓታት ተኩስ-አቁማ በራሷ ጊዜ ዳግም ተኩስ ከፈተች።

ትናንት የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር፤ ዛሬ ደግሞ የኢጣሊያዋ አቻቸዉ ፌደሪካ ሞግሔሪኒ እየሩሳሌም-እየደረሱ ተመልሰዋል።የፍልጤም ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ የግብፅና የቱርክ መሪዎችን ድጋፍ ለመጠየቅ ሁለቱን ሐገራት ይጎበኛሉ።ግድያዉ ቀጥሏል።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic