1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የእስራኤልና የሒዝቡላሕ ተኩስ አቁም፣ ለሠላም ወይስ ጊዜ መግዢያ

ረቡዕ፣ ኅዳር 18 2017

በ14ት ወራቱ ጦርነት እስራኤል የሒዝቡላሕ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ፣ ከ3700 በላይ የሊባኖስ ዜጎችን ገድላለች።ብዙ ሺዎችን አቁስላለችል።ሚሊዮኖችን አፈናቅላለች።የሊባኖስ ምጣኔ ሐብት ዳሽቋል።የርዕሰ ከተማ ቤይሩት ሕንፃ-የመሰረተ ልማት አዉታሮች ትናንት ጭምር ሲወድሙ ነበር

https://p.dw.com/p/4nUfp
እስራኤልና ሒዝቡላሕ የገጠሙትን ዉጊያ በመሸሽ በሚሊዮን የሚቆጠር የደቡባዊ ሊባኖስ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል
በእስራኤልና በሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን መካከል የተደረገዉ ተኩስ አቁም ገቢር መሆን እንደጀመረ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለዉ የሊባኖስ ሕዝብ ወዲ,ቀዬዉ ሲመለሰምስል Mohammed Zaatari/AP/picture alliance

የእስራኤልና የሒዝቡላሕ ተኩስ አቁም፣ ለሠላም ወይስ ጊዜ መግዢያ

እስራኤልና የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕ ያደረጉት የተኩስ አቁም ሥምምነት ዛሬ ፀንቶ ዉሏል።በዩናይትድ ስቴትስ የተረቀቀዉን የተኩስ አቁም ዉል ሙሉ በሙሉ ገቢር ለማድረግ የእስራኤልና የሊባኖስ ባለሥልጣናት በየፊናቸዉ ቃል ገብተዋል።የሥምምነቱ አርቃቂ ዩናይትድ ስቴትስና ሥምምነቱ ተቀባይነት እንዲኖረዉ ከፍተኛ ግፊት ሥታደርግ የነበረችዉ ፈረንሳይ ለስምምነቱ መከበር ድጋፋቸዉን እንደሚሰጡ አስታዉቀዋል።ሥምምነቱን የተለያዩ መንግሥታት ቢደግፉትም  ተቃዉሞና ጥርጣሬ አልተለየዉም።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አጠናቅሯል።
ያን ጥንታዊ፣ የሥልጣኔ መገኛ፣ የኃይማኖት መፍለቂያ፣ የኃያል-ደካሞች መፈራረቂያ ቁራሽ ግዛትን በቦምብ፣ሚሳዬል፣ በድሮን፣ በታንክ መድፍ፣በተንቀሳቃሽ መገናኛ ዘዴዎች ፈንጂ ሳይቀር አጋይተዉ፣ አንድደዉ፣ፈርክሰዉ፣ ፈረካክሰዉ፣ በሰዉ ደም አጥንት አጉድፈዉ ሲደክማቸዉ ወይም ሲበቃቸዉ «በቃን» አሉ።ተኩስ እናቁም።

አዉዳሚ ጦርነት፣ አስደሳች ስምምነት

ባለፉት 14 ወራትለእስራኤል በሳቸዉ ቋንቋ «ከብረት የፀና» ድጋፋቸዉን ደጋግመዉ የገለጡት የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጦርነቱን «አዉዳሚ»፣ ተኩስ አቁምን «መልካም ዜና» አሉት።
«ዛሬ ሥለመካከለኛዉ ምሥራቅ የምዘግበዉ ጥሩ ዜና አለኝ።ከጥቂት ጊዜ በፊት ከእስራኤልና ከሊባኖስ ጠቅላይ ሚንስትሮች ጋር ተነጋግሬያለሁ።በእስራኤልና በሒዝቡላሕ መካከል ሲደረግ የነበረዉን አዉዳሚ ግጭት ለማቆም ዩናይትድ ስቴትስ ያረቀቀችዉን ዕቅድ ሁለቱም መንግሥታት መቀበላቸዉን ሳስታዉቅ ደስታ ይሰማኛል።»
እስራኤልን በመደገፍና ሊባኖስን ከለየለት ዉድመት በመከላከል ተቃርኖ ተቃርጣ ለቆየችዉ ለቀድሞዋ የሊባኖስ ቅኝ ገዢ ለፈረንሳይም፣ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ እንዳሉት በርግጥ ደስታ ነዉ።
«በእስራኤልና በሊባኖስ መካከል ዛሬ የተኩስ አቁም ሥምምነት በመደረጉ ደስታዬን መግለፅ እፈልጋለሁ።(ስምምነቱ) በፕሬዝደንት ጆ ባደን መሪነት በዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ትብብር ከእስራኤልና ከሊባኖስ ባለሥልጣናት ጋር ለበርካታ ወራት የተደረገዉ ጥረት ዉጤት ነዉ።»

የእስራኤል ጦር የተኩስ አቁም ስምምነቱ ገቢራዊ ከመሆኑ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ቤይሩት ላይ ካደረሰዉ ዉድመት አንዱ
የተኩስ አቁም ስምምነቱ በይፋ እስከሚፀናበት ሰዓት ድረስ የእስራኤል የጦር ጄቶች የሊባኖስ ርዕሰ ከተማ ቤይሩትን ሲያጋዩ ነበርምስል AFP/Getty Images

የጦርነቱ ጥፋትና የስምምነቱ ይዘት


በ14ት ወራቱ ጦርነት እስራኤል የሒዝቡላሕ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ፣ ከ3700 በላይ የሊባኖስ ዜጎችን ገድላለች።ብዙ ሺዎችን አቁስላለችል።ሚሊዮኖችን አፈናቅላለች።የሊባኖስ ምጣኔ ሐብት ዳሽቋል።የርዕሰ ከተማ ቤይሩት ሕንፃ-የመሰረተ ልማት አዉታሮች ትናንት ጭምር ሲወድሙ ነበር።ከእልቂት፣ ጥፋቱ የተረፈዉ ሊባኖሳዊ ያፍታ-ፋታ ሲያገኝ ቢደስት በርግጥ አይበዛበትም።
ሒዝቡላሕ በትንሹ 45 ሰላማዊ እስራኤላዊያንንና 73 ወታደሮችን ገድሏል።ወገኖቹን ላጣዉ በተለይ ከየቤት ንብረቱ ለተፈናቃለዉ 60 ሺሕ የሰሜን እስራኤል ነዋሪ፣ ተኩስ መቆሙ በርግጥ አስደሳች ነዉ።ይሁንና ትናንት ማታ ቴል አቪቭ አደባባይ የወጡ መገናኛ ዘዴዎች «ቀኝ ክንፈኛ» ያሏቸዉ ወገኖች ተኩስ አቁሙን ተቃዉመዉታል።
በስምምነቱ መሠረት የእስራኤል ጦር ከደቡባዊ ሊባኖስ ለቅቆ ይወጣል።የሒዝቡላሕ ታጣቂዎች ሊታኒ ከተባለዉ ወንዝ ወደ ሰሜን ያፈገፍጋሉ።በድንበሩ ላይ የሊባኖስ ጦር ኃይል በ60 ቀናት ዉስጥ ይሰፍራል።በነባር የፖለቲካ ሽኩቻ፣ በምጣኔ ሐብት ድቀት፣ በቃጠሎና ሙስና ቁልቁል የምትሮጠዉን ሊባኖስን ከዉድቀት ለማዳን ለሚፍጨረጨሩት ለቤይሩት ፖለቲከኞች ተኩስ አቁም ከከፋ ጥፋት ማምለጫ «በር» ብጤ ነዉ።

ደቡባዊ ሊባኖስ።የሊታኒያ ወንዝና አካባቢዉ።በስምምነቱ መሠረት የእስራኤል ጦር ከደቡባዊ ሊባኖስ ለቅቆ ይወጣል።የሒዝቡላሕ ታጣቂዎችም ከሊታንያ ወንዝ በስተደቡብ የሚገኘዉን አካባቢ ይለቃሉ።በአዋሳኙ ድንበር የሊባኖስ መንግሥት ጦር ይሰፍራል
ደቡባዊ ሊባኖስ።የሊታኒያ ወንዝና አካባቢዉ።በስምምነቱ መሠረት የእስራኤል ጦር ከደቡባዊ ሊባኖስ ለቅቆ ይወጣል።የሒዝቡላሕ ታጣቂዎችም ከሊታንያ ወንዝ በስተደቡብ የሚገኘዉን አካባቢ ይለቃሉ።በአዋሳኙ ድንበር የሊባኖስ መንግሥት ጦር ይሰፍራልምስል JOSEPH EID/AFP/Getty Images

ተኩስ አቁሙና የኔታንያሁ ዕቅድ 

ስምምነቱን የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር፣ የቡድን ሰባት አባል ሐገራትና ሌሎችም መንግስታት ደግፈዉታል።ለዘላቂ ሰላም የመጀመሪያዉ ርምጃ በማለት አድንቀዉታልም።የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢንያምን ኔታንያሁ እንደሚሉት ግን መንግሥታቸዉ ስምምነቱን የተቀበለዉ በኢራን ላይ ለማነጣጠር፣ የጦር ሐይሉን ዳግም ለማጠናከርና  ሐማስን ለመነጠል ነዉ።

«ተኩስ አቁም ያስፈለገን ለምንድ ነዉ።በ3 ዋና ዋና ምክንያት ነዉ።የመጀመሪያዉ ከኢራን በሚሰነዘረዉ ሥጋት ላይ ለማተኮር።ዝርዝሩን አላብራራም።ሁለተኛዉ ለጦር ኃይላችን ፋታ ለማግኘትና የጎደለዉን ለማሟላት።በግልፅ እናገራለሁ።የጦር መሳሪያና ጥይት አቅርቦቱ በጣም መዘግየቱ ሚስጢር አይደለም።ይሕ አሁን መፍትሔ ያገኛል።ተልዕኮአችንን ከግብ ለማድረስ ተጨማሪ አቅም የሚሰጡን፣ወታደሮቻችንን ለጥቃት እንዳይጋለጡ የሚረዱ በጣም የተሻሻሉ መሳሪያዎች ይደርሱናል።ሶስተኛዉ ምክንያት የጦር ግንባሮቹን ለማጥበብና ሐማስን ለመነጠል።»
ይላሉ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት የእስራት ዋራንት የቆረጠባቸዉ ኔታንያሁ።ጥያቄዉ ዓለም የደከመ፣ የተደሰተበት ተኩስ አቁም ለሰላም ያለመ ነዉ ወይስ ጊዜ መግዢያ?

ነጋሽ መሐመድ 

ፀሀይ ጫኔ