የእስራኤልና አፍሪቃዉያን ስደተኞች | አፍሪቃ | DW | 02.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የእስራኤልና አፍሪቃዉያን ስደተኞች

እስራኤል በሕገ ወጥ መንገድ ወደግዛቷ የገቡ አፍሪቃዉያን ስደተኞችን «አስተማማኝ» ወዳለቻቸዉ ሶስተኛ ሃገራት ለማሻገር መወሰኗን አመለከተች። የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ መሠረትም ይህን አማራጭ የማይቀበሉ እስራት ይጠብቃቸዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ርምጃዉን ተቃዉመዋል። ተሰዳጆቹ የሚሄዱበትን ሀገር የእስራኤል መንግሥት ይፋ ባያደርግም መገናኛ ብዙሃንና የመብት ተሟጋቾች ግን ወደሩዋንዳና ዩጋንዳ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ። ይህ ርምጃ ከሚመለከታቸዉ አብዛኞቹ ከሱዳንና ኤርትራ ወደእስራኤል በሕገ ወጥ መንገድ ገብተዋል የሚባሉ ሲሆኑ ወደተጠቀሱት ሃገራት እንዲሄዱ መደረጉ ሕይወታቸዉን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ እየገለጹ ነዉ።

እስራኤል ዉስጥ ሕገ ወጥ የምትላቸው ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የገቡት ስደተኞች 42 ሺህና ከዚያም በላይ ይገመታሉ። ሆሎት በተባለችዉ ስፍራ የሚገኙት ብቻም ወደ2,000 ገደማ ናቸዉ። ዘገባዎች እንደሚሉትም ከዚህ አብዛኞቹም ወደየመጡበት ሀገራቸዉ ቢመለሱ የከፋ አደጋ እንደሚጠብቃቸዉ የሚናገሩ የሱዳንና የኤርትራ ዜጎች ናቸዉ። የእስራኤል መንግሥት «አስተማማኝ» ወዳላቸዉ ሶስተኛ ወገን የአፍሪቃ ሃገራት የሚሻገሩትን ስደተኞች በመለየትም አንድም ወደተባለዉ ስፍራ እንዲሄዱ አለያም እስከመቼ መሆኑ ያልተገለፀ እስር እንደሚጠብቃቸዉ ነግሯቸዋል።

Flüchtlingslager Holot für afrikanische Asylsuchende in Israel

ሆሎት ኔጌቭ በረሀ

ለጉዟቸዉም የመሳፈሪያና የሆቴል እንደሚከፍል ጭምርም አሳዉቋል። እንዲያም ሆኖ ርምጃዉን የሀገር ዉስጥና የዉጭ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም ተቃዉመዋል።እስራኤል ዉስጥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ሙታሲም አሊ ይህ አዲስ መመሪያ አለመሆኑን ቢያስታዉሱም ተግባራዊነቱ ግን የእስራኤልን ዴሞክራሲ ፈተና መሆኑን ያመለክታሉ።

«ሰዎችን ወደሶስተኛ ሀገር ማሻገሩ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ከሆነ ወደሁለት ዓመት ገደማ ይሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ ለየት ያለዉ ነገር ሆሎት ኔጌቭ በረሃ ዉስጥ እስር ላይ የቆዩት ስደተኞች ወደሶስተኛ ሃገር እንዲሄዱ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ በዝግ ወህኒ ቤት እንዲታሠሩ መባሉ ነዉ። ይህ በእርግጥ ተግባራዊ መደረጉም የእስራኤልን ዴሞክራሲ የሚፈታተን ነዉ የሚሆነዉ።»

እንደዘገባዉ የአብዛኞቹ አፍሪቃዉን ስደተኞች በተጎሳቆሉ የደቡብ ቴሌአቪቭ አካባቢዎች በርከት ብለዉ መገኘት ከነባር ኗሪዎች ዘንድ ተቃዉሞን አስከትሏል። የፈረንሳይ የዜና ወኪል የጠቀሳቸዉ የእስራኤል የሀገር ዉስጥ ሚኒስትር ጊላድ ኢርዳን፤ ሕገ ወጥ የሚባሉትን ስደተኞች በዚህ መልኩ ወደሌላ ሀገር ማሻገሩ፤ ለእነሱ አስተማማኝና ክብር ያለዉ መንገድ ነዉ ባይ ናቸዉ።

Wüste Sinai Ägypten

ስደተኞቹ የሚያቋርጡት የሲና በረሀ

ከምንም በላይ ግን እነሱን ማስወጣቱ የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ ሕይወት ወደቀድሞዉ ጤናማ አኗኗር ይመልሰዋል ማለታቸዉም ተገልጿል። እስራኤል በተለይ የሱዳንና ኤርትራን ስደተኞች ይገጥመናል የሚሉትን አስቸጋሪ ሁኔታ በማሰብ ወደየሀገራቸዉ እንደማትመልስ መግለጿ ተጠቅሷል። ያም ቢሆን ግን «አስተማማኝ» ወደምትላቸዉ ሶስተኛ ሃገር በማሻገር እቅዷ፤ የተዋዋለችዉ ስምምነት ግልፅ ባለመሆኑ አስቸጋሪ እንደሆነ ነዉ ሙታሲም አሊ የሚያስረዱት።

«ነገሩ እንዴት ነዉ፤ ጥቂት የደቡብ ሱዳን ዜጎች ካለፈዉ ዓመት አንስቶ ወደዩጋንዳና ሩዋንዳ እንዲሻገሩ ተደርጓል። እዚያ በሄዱበትም የመኖሪያ ሁኔታቸዉ ሳይስተካከል በመቆየቱ ምንም አስተማማኝ ነገር አላገኙም። ወደዩጋንዳም ሆነ ሩዋንዳ ከገቡ ከሶስት ወይም አራት ቀናት በኋላ እዚያም ሕገ ወጥ ተብለዉ ይፈረጃሉ። ከዚያም ወደተባሉት ሃገራት የስደተኞች ጉዳይ ፅህፈት ቤትም ሆነ UNHCR ለመሄድ ይገደዳሉ። ያ ግን እጣ ፈንታቸዉን ምንነት እንዲያዉቁት ምንም አይረዳም። ስለዚህ ጉዳይ ደግሞ ከእስራኤል መንግሥት ምላሽ የለም። ምክንያቱም በእስራኤልና በሃገራቱ መካከል የተደረገዉ ስምምነት ግልፅ አይደለም።»

እሳቸዉ እንደሚሉትም ባለፈዉ ወደሩዋንዳም ሆነ ዩጋንዳ የተሻገሩት ተሰዳጆች በገጠማቸዉ ችግር ምክንያት ወደ የትዉልድ ሀገራቸዉ ማለትም ኤርትራና ሱዳን ለመመለስ የተገደዱበት ሁኔታ አለ።

Israel Samuel Akue Flüchtling Sudan Tel Aviv Abschiebung Religion Fanatismus

ከተመለሱት የደቡብ ሱዳን ዜጎች ጥቂቱ

የእስራኤል የሀገር ዉስጥ ሚኒስቴር እንደሚለዉ ከጀመረበት ካለፈዉ ዓመት አንስቶ 1,500 ሕገ ወጥ ስደተኞች ወደሶስተኛ ሀገር በፈቃደኝነት ተሻግረዋል። 7,000 የሚሆኑት ደግሞ ወደየሀገራቸዉ ተመልሰዋል። ሙታሲም አሊ እንደሚገልፁት ተሰዳጆቹ ይህን ዉሳኔ ለመቀበል የሚገደዱበት እስራኤል ዉስጥ ካለዉ የአኗኗር ሁኔታቸዉ ይመስላል።

«እጅግ አዳጋች ነዉ። ከ2007ዓ,ም አንስቶ እስከ አሁን ግልጽ መመሪያ የለም። መንግስትም ሆነ የተለያዩ ባለስልጣናት አፍሪቃዉያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን ያገልላሉ። በወንጀለኝነት ይፈርጇቸዋል። ይህም ሕይወታቸዉን በተቻለ መጠን የከፋ ለማድረግ ነዉ። ዓላማዉም ጥገኝነት ጠያቂዎቹ እዚያ የመኖር ተስፋ እንደማይኖራቸዉ ማመላከት ነዉ። ለዚህም ነዉ ፖሊሲዎቹም ሆኑ ቅድመ ሁኔታዎቹ አስከፊ የሆኑት። ስደተኞቹ ህክምናን ጨምሮ ምንም ዓይነት ማህበራዊ አገልግሎት አያገኙም፤ እስራኤል ዉስጥም የመሥራት መብት የላቸዉም።»

ያም ሆነ ይህ በእስራኤል ዋና አቃቤ ሕግ የተወሰነዉ ይህ ዉሳኔ በቀጣይ ቀናት ዉስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን የሀገር ዉስጥ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ አመልክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic