የእስራኤልና ሃማስ ተኩስ አቁም | ዓለም | DW | 22.11.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የእስራኤልና ሃማስ ተኩስ አቁም

ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ለማቆም የተስማሙት በግብፅና በአሜሪካን የሽምግልና ጥረት ነው ። ስምምነቱም በመነጋገር በቃል የፀና እንጂ በፊርማ የፀደቀ አይደለም ። ሁለቱም ወገኖች ለተኩስ አቁም የሚያስፈልጉትን ቅድመ ግዴታዎች ካሟሉ ከ 24 ሰዓትት በኋላ በነርሱ ጥያቄ በሃምስና በእስራኤል መካከል ድርድር ሊጀመር ይችላል ።

እስራኤልና ሃማስ የተስማሙበት ተኩስ አቁም እንዲከበር ተጠየቀ ። ጋዛን የሚያስተዳድሩት የሃማስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢስማኤል ሃንያ የተለያዩ የፍልስጤም አንጃዎች ለስምምነቱ ተገዥ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል ። ሃንያ መልዕክቱን ያስተላለፉት በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት ሃማስ በፍልስጤም ምድር የሚንቀሳቀሱ ሌሎች የሚሊሽያ ቡድኖች ተኩስ አቁሙን እንዲያከብሩ በተጣለበት ሃላፊነት መሠረት ነው ። ስምምነቱ ለፍልስጤማውያን እንደ ድል ተቆጥሯል ። አንዳንድ እስራኤላውያን ደግሞ በነታንያሁ ውሳኔ አልተደሰቱም ።
8 ቀናት ከዘለቀው የእስራኤል የጋዛ ድብደባና የፍልሴማውያን የሮኬት ተኩስ በኋላ እስራኤልና ሃማስ ተኩስ ለማቆም መስማማታቸው ትናንት ማምሻውን ይፋ የተደረገው ከእየሩሳሌም ወይም ከራማላህ ሳይሆን ከካይሮ ግብፅ ነበር ። የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረሱ እንደተገለፀም ፍልስጤማውያን ደስታ ፈንቅሏቸው በጋዛ ጎዳናዎች ሲጨፍሩ አምሽተዋል ። ደሰታቸውን ለመግለፅም ከ 1ሺህ ጊዜ በላይ ወደ ሰማይ መተኮሳቸውም ተዘግቧል ። ደሰታቸውን ለመግለፅም  እንደ ድል የቆጠሩት የተኩስ አቁም ስምምነት እፎይታን አስገኝቶላቸዋል ። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ መንግስታቸው ስምምነቱን መቀበሉን ሲገለፅ ትንኮሳው ከቀጠለ እስራኤል በዝምታ የምታልፈው አለመሆኑን ተናግረዋል  ።


የአሁኑ የስምምነቱ ፣እስራኤል ሰርጎ ገብ እንቅስቃሴን እንዲሁም ግለሰቦችን ለይቶ ማጥቃትን ጨምሮ ከምድር ከአየር ም ሆነ ከባህር ማንኛውንም ትንኮሳና ወደ ግጭት የሚያመራ እርምጃ እንዳትወስድ ይጠይቃል ። ፍልስጤማውያን አንጃዎችም የጓዳ ሰራሽ ሮኬቶች ጥቃትን እንዲያቆሙና ድንበር አካባቢም ከሚፈፅሙት ማናኛውም ጥቃት እንዲቆጠቡ ጥሪ ያደርጋል ። ሁለቱ ወገኖች ተኩስ ለማቆም የተስማሙት በግብፅና በአሜሪካን የሽምግልና ጥረት ነው ። ስምምነቱም በመነጋገር በቃል የፀና እንጂ በፊርማ የፀደቀ አይደለም ። ሁለቱም ወገኖች ለተኩስ አቁም የሚያስፈልጉትን ቅድመ ግዴታዎች ካሟሉ ከ 24 ሰዓትት በኋላ በነርሱ ጥያቄ በሃምስና በእስራኤል መካከል ድርድር ሊጀመር ይችላል ።  እስራኤል ለምሳሌ ያህል ከጋዛ በኩል ጥቃት መሰንዘሩ እንዲቆም ብቻ ሳይሆን በፍልስጤም ግዛት የመቆጣጠር ሥልጣን አሁንም ሊኖረኝ ይገባል ነው የምትለው ። ሃማስ ደግሞ  እስራኤልና ግብፅ በጋዛ ላይ የተደረገው ከበባ እንዲነሳ እንዲያደርጉ እንዲሁም ሰዎችና እቃዎች ያለ ገደብ እንዲጓጓዙ ነው የጠየቀው ። በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ድርድሩን አስመልክተው በሰጡት የመጀመሪያ አስተያየት እነርሱን ሊያረካቸው የሚችል ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል ።


« የእስራኤልን ጦር አንፈራም ። ሆኖም ለሞቱትና ለሚፈናቀሉት ልጆቻችን ስንል ነው የተኩስ አቁሙ እንዲደረግ የምንፈልገው ። ለልጆቻችን ስንል ብቻ»
እስራኤልና ፍልስጤማውያንን ለመሸምገል ትናንት እየሩሳሌም ራማላ ና ካይሮ የነበሩት የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂለሪ ክሊንተን በሽምግልናው ግብፅ አግዘዋል ። በስተመጨረሻ ከካይሮ ነበር ክሊንተን ወደ አገራቸው ያቀኑት ። እስራኤል እግረኛ ወታደሮቿን ወደ ጋዛ የመላክ እቅዷ እንዳለ ነው ። ይሁንና የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኤሁድ ባራክ ተጨማሪ ውጊያ ከእንግዲህ ማካሄዱ ምክንያት ያለው ሆኖ አይታያቸውም ።
«ግቦቻችንን ሙሉ በሙሉ መተናል ። ሃማስና ኢስላማዊ ጂሃድ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ። የሃማስ ወታደራዊ አዛዥ ድሃሽባሪና ሌሎችም ከፍተኛ አዛዦችና የሃማስ አስተሳሰብ አራማጆች እንዲሁም በርካታ አሸባሪዎች ተገድለዋል ።

በአጠቃላይ ከ130 በላይ ተገድለዋል ። ከ 900 በላይ ቆስለዋል»  
ምንም እንኳን የ 8 ቀኑ ጦርነት ብዙ የሰው ህይወትና ንብረት ቢያጠፋም የተኩስ አቁምን ስምምነቱን ፍልስጤማውያን እንደ ድል ነው የቆጠሩት ። ከፍልስጤም ምድር የሚተኮሱት ሮኬቶች ቴላቪቭና እየሩሳሌምን መድረስ መቻላቸው በፍልስጤማውያን ዘንድ ለእስራኤል መንበርከክ ምክንያት ተደርጎ ነው የተወሰደው ። አንዳንድ እስራኤላውያን ደግሞ ነታንያሁ የተኩስ አቁሙን መቀበላቸውን ከውርደት ቆጥረውታል ። አንዳንድ ወታደሮች ጭምር የነተንያሁ እርምጃ አላስደሰታቸውም ። 

 

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

 

Audios and videos on the topic