የ«እርሻ መሬት ቅርምት» ና ሳዑዲ አረቢያ | ዓለም | DW | 11.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የ«እርሻ መሬት ቅርምት» ና ሳዑዲ አረቢያ

በቅርቡ ግን የሳዑዲ አረቢያ ገበሬዎች ለንጉስ አብዱላሕ «ብሔራዊ» ያሉትን የሰብል ምርት አበረከቱ።የተመረተዉ ግን ሳዑዲ አልነበረም።ኢትዮጵያ እንጂ

default

110110

ሳዑዲ አረቢያ ከአለም ሐብታም ሐገራት አንዷ ናት።በነዳጅ ዘይት ሐብት የበለፀገችዉ ሐገር በድሆቹ ሐገራት የእርሻ መሬት ለማግኘት በሚደረገዉ አለም አቀፍ ዉድድርም ከግባር ቀደሞቹ ሐገራት አንዷ ሆናለች።«የመሬት ቅርምት» በሚባለዉና አንዳዶች «አዲሱ ቅኝ አገዛዝ» እያሉ የሚተቹት ሥልትም በሳዑዲ አረቢያ እይታ ለወደፊት ኑሮ አስተማማ መሠረት መጣል ነዉ።በነዳጅ ዘይት ሐብት ከአለም የመጀመሪያዉን ሥፍራ የያዘችዉ ሐገር የሌሎች ሐገራትን መሬት በመግዛት በራሷ ግዛት ማድረግ የማትችለዉን ኢንዱስትሪ እያስፋፋች ነዉ።ኻሊድ ኤል ካኦዉቲት የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የ«አረብ-ሳዑዲ የእርሻ ባንክ» እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ1962 ሲመሠረት ለሳዑዲ ታሪካዊ ክስተት ነበር።የዉሐ እጥረት ያለበት በረሐይቱ ሐገር በዚሕ ተቋም አማካይነት አብዛኛዉን የምግብ አቅርቦት የሚሸፍን የራሷን የእርሻ መስክ ለመገንባት ነበር-አለማዉ።ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ የሚደረግለት ሰብል ከራስ ምድር፥በራስ ጥረት የተገኘ ምርት ተብሎም አስፈንድቆም ነበር።ወዲያዉ ግን ዘላቂ እንደማይሆን ተረጋገጠ።
«የግብርናዉ መስክ አዳዲሶቹን ብሔራዊና አለም አቀፋዊ ፈተናዎች መቋቋም አለበት።በመጀመሪያ እየሰፋ የመጣዉ የአለም አቀፍ ንግድ ሥርዓት ነፃነት፥እና ሁለተኛ ደግሞ እተባባሰ ያለዉ የከርሰ ምድር ዉሐ እጥረት»

ይላሉ-የሳዑዲ አረቢያዉ የግብርና ሚንስትር ደ ኤታ አብደላሕ አል-ቁባይድ።ገበያዉ አለም ንግድ ይበልጥ መክፈቱና የከርሰ ምድር ዉሐ እጥረት ከፍተኛ ድጎማ የሚደረግለትን የሐገር ዉስጡን ምርት ዋጋ አስወድዶ፥በስምት አመቱ አስቆመዉ።

በቅርቡ ግን የሳዑዲ አረቢያ ገበሬዎች ለንጉስ አብዱላሕ «ብሔራዊ» ያሉትን የሰብል ምርት አበረከቱ።የተመረተዉ ግን ሳዑዲ አልነበረም።ኢትዮጵያ እንጂ።ስጦታዉ ዘገቢዉ ኤል ካኦዉቲት እንደሚለዉ የዉጪ ሐገር መሬት በመያዙ ሒደት የመንግሥት ተሳትፎ መኖሩን ጠቋሚ ነዉ።ሚንስትር ደ ኤታዉም የሚሉት አለ።

«በእኛ እምነት በዉጪ ሐገር ለግብርናዉ መስክ የሚዉለዉ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት የምግብ አቅርቦታችን ማረጋገጪያ ነዉ።እንደ ብዙዎቹ የአለም ሐገራት ሁሉ ሳዑዲ አረቢያ አስተማማኝ የምግብ አቅርቦት እንዲኖራት ትፈልጋለች።»

ሚንስትር ደኤታ አል-ቁባይድ በእርሻዉ መስክ በዉጪ ሐገራት የሚወርቱ ባለሐብቶችን የሚያማክር፥ የሚረዳና የሚያበረታታና ፍቃድ የሚሰጠዉ የሚንስትሮች ኮሚቴ አባልም ናቸዉ።ኮሚቴዉ ስምንት መቶ ሚሊዮን ዶላር ተመድቦለታል።ስዑዲ አረቢያዊዉ የምጣኔ ሐብት አዋቂ መሐመድ አልቁናይቢ ግን የመንግሥታቸዉን አቋም አይቀበሉትም።

«በዉጪ ሐገር የሚደረግ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በዚያ (በታላሚዉን) ሐገር የአስመጪ ሕግ የሚመራ ነዉ።እዚያ ምግብ ፍላጎት ካለ እሕሉ በተመረተበት ሐገር መቅረት አለበት።ከዚሕ በተጨማሪ (ሥራዉ) የዚያ ሐገር ፖለቲካዊ ሁኔታ ጥገኛ ነዉ።»

እንደ ኢትዮጵያ፥ ሱዳን የመሳሰሉት በግብርናዉ መስክ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስባቸዉ ሐገራት ተደጋጋሚ የምግብ እጥረት ያለባቸዉ ናቸዉ።በነዚሕ ሐገራት እሕል አምርቶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መዉሰድ ኢኮኖሚስት አል ቁናይቢ እንደሚሉት የሳዑዲ አረቢያን መልካም ስም የሚጣፋ ነዉ።እንዲሕ አይነቱ የመከራከሪያ ሐሳብ በሚንስትር ደ ኤታ አል-ቁባይድ ዘንድ ተቀባይነት የለዉም።

«ይሕ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት አለም አቀፍ ምርታማነትን የማሳደግ አለማም አለዉ።ለግብራናዉ መስክ ሥራ በሚደረገዉ የጋራ ስምምነትም በርግጥም ታላሚዎቹ (የባለመሬቶቹ) ሐገራት ብሔራዊ ምርታቸዉን እንዲያሳድጉ እድል የሚፈጥር ነዉ።ሳዑዲ አረቢያ በነዚሕ ሐገራት ከምታመርተዉ እሕል የተወሰነዉ እዚያዉ ነዉ የሚሸጠዉ።»

የኢራቁ የምጣኔ ሐብት አዋቂ መሐመድ አል ዶኦላይሚ የዉጪ ሐገራት የእርሻ መሬትን በመኮናተር የሚደረገዉን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በጥቅሉ ይተቻሉ።በተናጥል ግን ከቻይና የሳዑዲ ይሻላል ባይ ናቸዉ።
«ቻይና መሬቱን ብቻ አይደለም የምትገዛዉ።ለማምረት የሚያስፈልገዉን የሰዉ ሐይልም ይዛ ነዉ የምትገባዉ።የሳዑዲ አረቢያ የተለየ ነዉ።በባለ መሬቶቹ ሐገራት የእስራ እድል ይፈጥራል።ይሕ አንድ ጥሩ ጥቅም ሊሆን እችላል።ከዚሕ በተጨማሪ የሐገራቱ ብሔራዊ የምግብ ምርት ይጨምራል።»

Khlid El Kaoutit
Negash Mohammed
Aryam Abraha


Audios and videos on the topic