1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእርሻና የግጦሽ መሬትን ያካለለው ተክልና የግለሰቡ መፍትሄ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2016

መጤ አረሞች በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሀገር ይገባሉ። ጣናን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ የውኃ አካላትን የወረረው እንቦጭ በቅርብ ጊዜ ብዙ ከተባለላቸው መጤ አረሞች አንዱ ነው። ለማደግ ብዙም ውኃ የማይፈልገው ደረቅ አካባቢ ተንሰፋርቶ የሚባዛው ፕሮሶፒስ በአፋር ክልል ሰፊ መሬትን መያዙ አርብቶ አደሩን ኅብረተሰብ የግጦሽ መሬት እንዳሳጣው ይነገራል።

https://p.dw.com/p/4i4dT
አፋር ክልል ፕሮሶፒስ ዛፍ
የአፋርን መልክአ ምድር ያካለለ መጤው ፕሮሶፒስ ዛፍ። ምስል DW

የእርሻና የግጦሽ መሬትን ያካለለው ተክልና የግለሰቡ መፍትሄ

ፕሮሶፒስ ስያሜና አመጣጥ

በሳይንሳዊ ስያሜው ፕሮሶፒስ ይባላል፤ በአፋር ክልል በብዛት የተንሰራፋው ይህ ዛፍ በአፋሮች አንድም ደርጊ ሃራ አንድም ወያኔ በሚል መጠሪያው ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በረሃማነትን ለመከላከል በሚል ከባሕር ማዶ የመጣው ይህ ዛፍ በአሁኑ ጊዜ በተለይ ምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት ኢትዮጵያ፤ ኬንያ እና ሶማሊያ በብዛት ይገኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ወደ ድሬደዋ የገባው በ1960ዎቹ እንደሆነ በኢትዮጵያ የእርሻ ምርምር ድርጅት የተዘጋጀ አንድ ጥናት ያመለክታል። ድርቅን መቋቋሙን በመመልከት ሰዎች ለእርሻ ቦታዎችም ሆነ ለየመኖሪያ አካባቢያቸው እንደ አጥር እንዲያገለግል በአንድ ወቅት በብዛት ይተከሉት እንደነበር የተገለጸው ይህ ዛፍ አንዴ ከተተከለ አካባቢውን ሁሉ እንደሚሸፍን ነው ሁኔታን በቅርበት የተከታሉ ይናገራሉ። ምናልባትም ከሕንድ ወደ ኢትዮጵያ ሳይገባ እንዳልቀረ የሚነገርለት ፕሮሶፒስ የተሰኘው ዛፍ በመጀመሪያ ወደ ድሬደዋ ከዚያም ወደ አፋር ክልል እንደተስፋፋ የእርሻ ምርምር ድርጅት ጥናት ይጠቁማል።

የመጤው ዛፍ ተጽዕኖ

ይህ ዛፍ በብዛት ባለባቸው አካባቢዎች ሙቀቱ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የዝናብ መጠኑም አነስተኛ እንደሆነና ሌሎች ተክሎችም የመብቀል ዕድላቸው የመነመነ እንደሆነ ነው ጥናቱ ያመለከተው። በዚህም ምክንያት ዛፉ ተቀናቃኝ እንደሌለበት የሚጎዳው ተባይም ሆነ ሌላ ጸር እንዳላጋጠመው ታይቷል። ወደ ኢትዮጵያ የገባው ፕሮሶፒስ ጥቅጥቅ ያለ ደን የሚፈጥር፣ እሾሃማና በፍጥነት የሚራባ ዓይነትም መሆኑ ተገልጿል።

አፋርና ሶማሌ ክልል ውስጥ በብዛት የተስፋፋው ይህ ዛፉ በባህሪው ለማደግ እጅግም ውኃ የማይፈልግ፤ በአጭር ጊዜ የሚያድግና አካባቢን በፍጥነት የሚወር፤ ለእንስሳት መኖነት የማይውል ነገር ግን እሾሁ ከወጋ አደገኛ እንደሆነም ይነገራል።

ይህ ዛፍ ሰፋ ያለ አካባቢን በመውረር የእርሻም ሆነ የግጦሽ ቦታዎችን እያጣበበ በመምጣቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲጠፋ የሚለው ሃሳብ ከመጣ ቆይቷል። ለዚህም የተለያዩ አካላት የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ሊያስወግዱት ቢሞክሩም በቀላሉ የሚገላገሉት ዓይነት አልሆነም። አፋር ላይ የአርብቶአደሮቹን አካባቢ የግጦሽ መሬት በማሳጣት የሚወገዘው ፕሮሶፒስ ዛፍ እንዲሁ ይጥፋ መባሉ ውጤት አለማምጣቱን ያስተዋሉ ወገኖች ለአካባቢው ነዋሪ የኤኮኖሚ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችልበትን ስልት መቀየስ እንደሚሻል ሲመክሩ ቆይተዋል።

የአፋር መልክአ ምድር በከፊል
የአፋር መልክአ ምድር በከፊልምስል picture-alliance/dpa

ለማጥፋትም ሆነ እንዳይስፋፋ የተደረጉ ጥረቶች

በአካባቢው በርካቶች ይህን ወራሪ መጤ ተክልለማስወገድ በሚል በባህላዊ መንገድ ከሰል እያከሰሉ  ለተጠቃሚዎች ማገዶ ለማቅረብ ለብዙ ዓመታት ሞክረዋል። ሆኖም አፋር አካባቢ የሚዘጋጀውን ከሰል በብዛት ተጠቃሚዎች ወደሚገኙበት ለማድረስ ባለው ውጣ ውረድ ምክንያት ዋጋው ከፍተኛ መሆኑ ኑሯቸው ዝቅተኛ የሆነ ወገኖችን ለችግር መዳረጉ ነው የሚነገረው።

ይህን ዛፍ ፈጽሞ ለማጥፋት አለመቻሉን ካስተዋሉት አንዱ የአፋር ወጣት በግል ተነሳሽነት ወደ ጠቃሚ ከብክለት ነጻ የሆነ አማራጭ የኃይል ምንጭ እና ማገዶ አድርጎ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ነው። አፋር ክልል የአዋሽ ከተማ ነዋሪ የሆነው አሊ አህመድ በሽር የተባለው ዛፍ በአካባቢው አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ኑሮ ላይ ያስከተለውን ጫና በቅርብ ተመልክቷል።

ፕሮሶፒስ የተሰኘው መጤ አረም አካባቢውን እንዴትና መቼ ወረሰው የሚለውን በተመለከተ አሊ አህመድ እራሱ ያስተዋለውንና ያጋጠመውን ሲገልጽ እሱ ከመወለዱ አስቀድሞ ወደ አፋር ክልል መግባቱን እንደሰማ ነው የሚናገረው። በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ ይህን መሰሉን ጉዳት የሚያስከትለውን ወራሪ አረም ለማጥፋት በሚል የተለያዩ ጥረቶች እንደተደረጉ መሆኑን መረጃዎች ያሳሉ። የኅብረተሰቡን ኑሮ አብሮ እየኖረ ችግሩን በቅርበት መመልከት የቻለው አሊ አረሙን በማጥፋት ስም በባህላዊ መንገድ በገፍ በአካባቢው የሚከናወነው  ከሰል የማምረት ሂደት የሚያስከትለውን አሉታዊ አስተዋጽኦም ያነሳል።

አሊ አህመድ
አሊ አህመድ የአሊፍ ኢነርጂ መስራችና የሃሳብ አመንጪ ምስል DW

ጭስ የሌለው ከሰል

የአሊፍ ኢነርጂ መስራችና የሃሳብ አመንጪ የሆነው አሊ አህመድ በሽር ከችግሩ በመነሳት በመፍትሄነት በእራሱን የግል የፈጠራ ከካርቦን ነጻ የሆነ ከሰል ለየት ባለ መንገድ በማዘጋጀት ለቤት ውስጥ አገልግሎትም ሆነ ለኢንዱስትሪ የኃይል ምንጭ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ያስረዳል። ወጣት አሊ አህመድ በሽር ከካርቦን የጸዳ ከሰልን ይህን እንዲጠፋ የሚፈለግ ዛፍን እንዲሁም የእርሻ ተረፈ ምርቶችና የሚጣሉ ቆሻሻዎችን ተጠቅሞ ዘላቂነት ያለው የኃይል ምንጭ ለማዘጋጀት ያቀረበው ንድፈ ሃሳብ የበርካታ ተቋማትን ቀልብ እንደገዛ ያገኛቸው ሽልማቶች ያመለክታሉ።

አዋሽ ከተማ ውስጥ ከጅቡቲ አዲስ አበባ መስመር ላይ ማደጉት የሚናገረው አሊ አህመድ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች ጉዳይ ትኩረቱን እንደሳቡት ይናገራል። እዚያው ሀገር ውስጥ ለየቤቱ የሚቀርብ የኃይል ምንጭ እንዲጠፋ ከሚፈለግ አረም እና መሰል ተረፈ ምርቶች አዘጋጅቶ የማቅረብ እቅዱ የገንዘብ ድጋፍ ቢያገኝ ለኅብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያምናል።

እሱ ባሰበው መንገድ የሚያከናውነው ተግባር አንድም የአካባቢውን ለም መሬት ለእርሻ ከወራሪው አረም ነጻ የሚያደርግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ የመቀነስ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተስፋ ያደርጋል።

አሊ አህመድ ምንም እንኳን የገንዘብ አቅም ቢገድበውም የአፋር አርብቶ አደሮችን የግጦሽ መሬት ያሳጣውን መጤ አረም ወደ ጠቃሚ የኃይል ምንጭነት ለመለወጥ ተዘጋጅቷል።

 ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ