የእርስ በርስ ጦርነት ቡሩንዲን ያሠጋ ይሆን? | አፍሪቃ | DW | 06.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የእርስ በርስ ጦርነት ቡሩንዲን ያሠጋ ይሆን?

ከሳምንታት አመፅና ተቃዉሞ በኋላ የቡሩንዲ ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ ጊዜ ለምርጫ መወዳደር እንደሚችሉ ተወስኗል። የሀገሪቱ ሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት ትናንት በይፋ የፕሬዝደንቱ እጩነት ሕገ-መንግሥታዊ ነዉ ሲል አሳዉቋል።

በመሠረቱ የቡሩንዲ ሕገ-መንግሥት ለሀገር መሪ የሰጠዉ ሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ ነዉ። የፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ፕሬዝደንት ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለሚያደርጉት ዝግጅት አረንጓዴ መብራት አሳይቷል። ታዛቢዎች ዉሳኔዉ ነፃና ገለልተኛ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ።

ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2005ዓ,ም ወደስልጣን የወጡት በሕዝቡ ቀጥተኛ ድምፅና ምርጫ ሳይሆን በሀገሪቱ ምክር ቤት አማካኝነት ነዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1993ዓ,ም የጦሩ አንድ ክፍል በሕዝብ የመረጡትን ከሁቱ ጎሳ የወጡትን ፕሬዝደንት ሜልኮር ንዳዳዬን ገደለ። ይህም በሀገሪቱ ለሰባት ዓመታት በሁቱና ቱትሲ መካከል የእርስበርሱ ጦርነት እንዲካሄድ ምክንያት ሆነ። በዚህ ግጭት ፣ ጦርነትም፣ ከ300 ሺህ የሚበልጥ ሕዝብ አልቋል። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2000ዓ,ም አሩሻ ታንዛኒያ ላይ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥት የቀረጹት አባቶች የመጀመሪያዉ ፕሬዝደንት በምክር ቤት ዉስጥ በተገኘ የድምፅ ብልጫ እንዲወሰን አደረጉ።

Burundi Präsident Pierre Nkurunziza bewirbt sich um eine dritte Amtszeit

ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ

ንኩሩንዚዛ አሁን የሚሟገቱት መጀመሪያ የተመረጡት በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት ባለመሆኑ አሁን ሕገ ደንቡ እንደሚያዘዉ በይፋ ሶስተኛ እድል አለን በሚል ነዉ። ሕገመንግሥታዊዉ ፍርድ ቤትም ይህንን አተረጓጎም የተከተለ ይመስላል። ዉሳኔዉ የተሰማዉ ከመነሻዉ የንኩሩንዚዛን ለሶስተኛ ጊዜ ለምርጫ እጩነት መቅረብ ከሕገመንግስቱ እንደሚፃረር ሲገልፁ የቆዩት የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝደንቱ ሲልቪየር ኒምፓጋሪቲ ከሀገር ከተሰደዱ በኋላ ነዉ። መንግሥት ተፅኖ ያደርግ እንደነበር ያመለከቱት ኒምፓጋሪቲ የግድያ ዛቻ እንደደረሰባቸዉም አመልክተዋል። የበርሊን የዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ክላዉዲያ ዚሞንስ ፍርድ ቤቱ ነፃ ዉሳኔ አሳለፈ ማለት አይቻልም ይላሉ።

«ዉሳኔዉ ነፃ ነበር ማለት አይቻልም። ሕገመንግሥቱ እንዲከበርም ከመነሻዉ ሶስት ሲደግፉ አራት ተቃዉመዉ እንደነበር ተሰምቷል።። በተደረገዉ ግፊት ሳቢያም ቀሪዎቹ ዳኞች አቋማቸዉን መለወጥ ግድ ሆነባቸዉ።»

ክላዉዲያ ዚሞንስ የቡሩንዲን ይዞታ በገመገመዉ ጥናታቸዉ እንዳመለከቱትም ለጊዜዉ ፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ይሰጣል የተባለበት ዕለት ተላልፎ ነበር። በመካከሉ ግን ቀሪዎቹ ዳኞች ሌሎቹ ላይ ጫና ሳያደርጉ እንዳልቀሩም ያስረዳሉ። የቡሩንዲ ሕገ-መንግሥት አዋቂዎችም የዉሳኔዉን ሕጋዊነት አላረጋጡም። የቀድሞዉ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ዶሚቲየን ናዳይዚም ዉሳኔዉ ከሕግ አኳያ አጠራጣሪነቱን ይናገራሉ።

«ዛሬ ላይ ቆሞ መጀመሪያ ላይ ፕሬዝደንቱ በቀጥተኛ መንገድ አልተመረጡም ነበር ማለቱ የተሳሳተ አካሄድ ነዉ። የአሩሻዉን ስምምነት ብንመለከት፤ የትኛዉም ፕሬዝደንት ከሁለት ጊዜ የስልጣን ዘመን በላይ ሀገሪቱን ማስተዳደር አይችልም ሲል፤ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። እናም ይህ እዉነትና የማያወላዳ ነዉ።»

በዚህ ምክንያትም ቡሩንዲ አሁን ባለችበት ሁኔታ የፕሬዝደንቱ የስልጣን ዘመናቸዉን ለሶስተኛ ጊዜ ለማራዘም መወጠን የሀገሪቱን ፀጥታ እንደሚያናጋ ታዛቢዎች እየገለጹ ነዉ። ፕሬዝደንት ንኩሩንዚዛ ባለፈዉ ሚያዝያ 17 ቀን ይህን ዉጥን ይፋ ካደረጉ አንስቶም የዋና ከተማ ቡጁሙቡራ ጎዳናዎች በተቃዋሚዎች አመፅ እንደተናጠች ነዉ። ተቃዋሚዎችና ፖሊሶችም መጋጨታቸዉ ሕይወት መጥፋቱ ንብረት መዉደሙም እየተነገረ ነዉ። አብዛኞቹ ቡሩንዲያዉያን ንኩሩንዚዛ በገቡት ቃልና በሰጧቸዉ ተስፋ መሠረት ኑሯቸዉ ባለመለወጡና ባለመሻሻሉ ደስተኞች አይደሉም። በሀገሪቱ ከፍተኛ ግሽበት ከመታየቱ በተጨማሪ፤ የምግብ ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ በየዕለቱ እየናረ ሄዷል። የነዳጅ እጥረት አለ፤ አብዛኞቹ ወጣት የሀገሪቱ ዜጎች ሥራ አጦች ናቸዉ። ይህም አለመረጋጋቱን እንደሚያባብሰዉ ይገመታል። አሁን ሁሉም ዐይኖች የሀገሪቱ ጦር ሠራዊት ላይ አተኩረዋል። የእሱ አቋም ነዉ የሀገሪቱን መፃኤ ዕድል የሚወስነዉ። ችግሩ ግን ጦሩ ራሱ ለፕሬዝደንቱ በመወገንና በመቃወም አቋም የተከፈለ ነዉ።

Domitien Ndayizeye

የቀድሞዉ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ዶሚቲየን ናዳይዚም

ቅዳሜ ዕለት የመከላከያ ሚኒስትሩ ፖንታይን ጋሲዩቡዌብጌ ጦሩ ገለልተኝነቱን እንዲጠብቅ በማሳሰብ የቡሩንዲያዉያን ሕገመንግሥታዊ መብት እንዲጠበቅ አሳስበዋል። በፖሊስና የተቃዉሞ ሰልፈኞች መካከል ግጭት እንዳይባባስም ወታደሮች በፖሊስና በሰልፈኞቹ መካከል ገብተዉ ታይተዋል። ቆየት አሉና የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ በበኩላቸዉ የሠራዊቱን ለፕሬዝደንቱ ታማኝነት በይፋ ተናገሩ። ካለፈዉ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ የተገነባዉ የቡሩንዲ ጦር በአማፅያንና መደበኛ ሠራዊት ተዋፅኦ የተገነባና ለሌሎችም ማሳያ የሚሆን ነዉ። የሰሞኑ ዉጥረት ግን ምናልባት ይህ እንዲቀጥል ላይፈቅድ ይችል ይሆናል የሚል ስጋት አለ። አሳሳቢ ደወሎችና የማስጠንቀቂያ መብራቶች እየታዩ ሳለ የእሳት አጥፊዉ ብርጌድ የት አለ? በማለትም የቀድሞዉ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ባልደረባ ያን ኢግላንድ ዛሬ ጄኔቫ ላይ ይህን አስመልክቶ ለተካሄደዉ ጉባኤ ጥያቄ አቅርበዋል። እንደመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባም በሰሞኑ አመፅና ተቃዉሞ ስጋት ከ40 ሺ የሚበልዙ የቡሩንዲ ዜጎች ወደጎረቤት ሃገራት ለመሰደድ ተገደዋል፤ ያለፈዉን የእርስ በርስ እልቂት በማስታወስ።

ካትሪን ማታይ/ ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic