1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእህል ዘሮችን ምርታማነት የሚያሻሽለዉ ምርምር

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16 2009

የተለያዩ የእህል ዘሮችን በምርምር አማካኝነት የጥራቅ አደረጃቸዉን ማሻሻል እንደሚቻል የግብርና ምርምር ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ዋና አላማዉም የእህል ዘሩን የድርቅና ተባይ የመቋቋም አቅም አሻሽሎ ምርታማነቱን ለማድረግና አርሶ አደሩም ሆነ የሚኖርበት አካባቢ ዘላቂ የምግብ ዋስትና እንዲኖረዉ ለማስቻል ነዉ።

https://p.dw.com/p/2ib7R
Äthiopien - Äthiopisches landwirtschaftliches Forschungsinstitut - Verbesserte Samen auf dem Feld
ምስል S. Yemaneh

የተሻሻሉት ዘሮች ድርቅን በመቋቋም ምርታማነትን ያሻሽላሉ፤

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ተቋም ሦስት ተልዕኮዎች ያሉት በሀገሪቱ በፌደራል ደረጃ የሚገኝ የምርምር ተቋም ነዉ። የተቋሙ ግንባር ቀደም ሥራ ምርምር ሲሆን የተገኘዉን ዉጤት በማስተዋወቅ በዚያ ላይ የሚታየዉን ፍላጎት መሠረት አድርጎ የተገኘዉን ዘር ለሚያባዙ አካላት ለመነሻ የሚሆነዉን ያቀርባል።  የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት እና አዕምሮዊ ንብረት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፤  አቶ ፍሰሐ ዘገየ እንደገለፁልን ከዚህ አልፎም አርሶ አደሩ በቀጥታ እነዚህን ዘሮች እና የአሠራር መረጃዎችን እንዲያገኝ ያደርጋል።

«ከአርሶ አደሩም ጋር ቀጥታ በመሥራት አርሶ አደሩ እነዚህን ቴክኒዎሎጂዎች እንዲያገኝ መነሻ ዘር ለአርሶ አደሩ በመስጠት፤ ስልጠና በመስጠት አርሶ አደሩ ያንን እያባዛ ሌላዉም አርሶ አደር እርስ በራሱ እንዲጠቃቀም የምናደርግበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ተልዕኳችን ይኼ ነዉ። አሁን በየዓመቱ እንሠራለን ፤ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች ይጀመራሉ። እንግዲህ እስከ ዛሬ በተሠራዉ በ2009 ብቻ ወደ 48 የሚሆኑ የሰብል ዝርያዎች አቅርበዋል።»

በአፍሪቃ አሉ ከሚባሉት የምርምር ተቋማት  የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ተቋም አንጋፋዉ ነዉ።  ከተመሠረተ 50ኛ ዓመቱን ያከበረዉ ይህ ተቋም በእነዚህ ጊዜያት ዉስጥም ወደ1,280 የሚበልጡ ዝርያዎችን ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ማቅረቡን አቶ ፍሰሐ ገልጸዉልናል።  ችግር ብልሃትን ይፈጥራል እንዲሉ ለእንዲህ አይነቱ ምርምር ዋናዉ መንስኤ እሱዉ ነዉ ይላሉ።

Äthiopien - Äthiopisches landwirtschaftliches Forschungsinstitut - Verbesserte Samen auf dem Feld
ምስል S. Yemaneh

«ይህ እንግዲህ መነሻዉ ችግር ነዉ፣ የምርታማነት ችግር ሊሆን ይችላል፣ ከበሽታ ጋር የተገኛኙ ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ድርቁን ተከትሎ የሚፈጠረዉን የዝናብ እጥረትተቋቁመዉ  በአጭር ጊዜ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ፤ እና እንደየሁኔታዉ እነዚህ ቴክኒዎሎጂዎች በየዓመቱ ነዉ እንግዲህ የምናቀርበዉ ይኼ አሁን ለምሳሌ ስንዴን ስንመለከት በየጊዜዉ እያሻሻልነዉ ፣ ዋግ የሚቋቋምበትን፤ የምርቱ ሁኔታ የጥራቱ፤ እያሻሻልነዉ እስካሁን ደርሰናል። ሌላዉም የሰብል አይነት ስንመጣ ዝርያዎቹ እየተሻሻሉ ከነበረዉ ከ10 እስከ 20 በመቶ ምርታማነታቸዉ እየጨመረ መጥቷል ማለት ነዉ።»

እናም ይላሉ አቶ ፍሰሐ ይህንን የምርምር ዉጤት እና ግብዓት የሚሆን መረጃ ነዉ ለአርሶ አደሩ እና ለአርብቶ አደሩ ለማቅረብ  የሚሠሩት። በያዝነዉ 2009 የበጀት ዓመት ተቋሙ 586 የምርምር ዉጤቶች እና ለእሱ የሚጠቅሙ መረጃዎችን ለማቅረብ ነበር ያቀደዉ። እስካሁን 564ቱን ማቅረብ መቻሉንም ዘርዝረዋል።

«እንግዲህ ይሄ ቴክኒዎሎጂ እና መረጃ ማለት አንዳንዱ ምክረ ሃሳብ ነዉ። ተጨባጭ አይደለም። አሁን ዝርያ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ነዉ፤ አንዳንዱ ደግሞ ዝርያዉን እንዴት መትከል፤ እንዴት ማምረት ፤ የበሽታም ጥበቃ ከሆነ የመሳሰሉትን  እንደ ምክረ ሃሳብ ደረጃ የሚወጡ ናቸዉ ማለት ነዉ። »

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰዉ ዘንድሮ ተቋሙ ያቀረባቸዉ የምርምር ዉጤት ከ500 ይበልጣሉ፤ ከእነዚህ መካከል ታዲያ ተጨባጭ የሆኑት የሰብል ዝርያዎች 48 ናቸዉ። የትኞቹ ይሆኑ? አቶ ፍሰሐ፤

«የሞኮሮኒ ስንዴ አለ፤ የዳቦ ስንዴ አለ፤ ገብስ፤ አጃ እና የመሳሰሉት፤ ለምሳሌ ሩዝ ላይ፤ ማሽላ ላይ፤ ዘንጋዳ፤ በቆሎ ላይ፤ እንደዚሁም ደግሞ ጥራ ጥሬ ላይ ፣ የተለያዩ የጥራጥሬ አይነቶች አሉ፤ እንደ ቦሎቄ እና ሽንብራ፣ ሰሊጥ፤ አትክልቶችም አሉ፤ እና እነዚህን የሚይዝ ነዉ አጠቃላይ ዝርያ ብለን ያወጣነዉ። ስለዚህ ዝርያዎቹ አንደኛ ምርታማነትን ይጨምራሉ ብለናል፤ ለአግሮ ኢንዱስትሪዉ ግብዓት የሚሆኑ አሉ፤ ለምሳሌ እንደቢራ ገብስ ያሉ፤ ለዉች ኤክስፖርት እንደቦሎቄ ያሉ አሉ፤ እነዚህ አሁን ተሻሽለዉ የሚወጡ ናቸዉ፤ በምርምር የሚገኙ ናቸዉ።»

Äthiopien - Äthiopisches landwirtschaftliches Forschungsinstitut - Verbesserte Samen auf dem Feld
ምስል S. Yemaneh

በምርምር የተሻሻሉትን የተለያዩ የእህል ዝርያዎች ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበርም ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ለማድረግ ተቋሙ እየሠራ መሆኑንም አብራርተዋል። በሚካሄደዉ ምርምር ከተገኙ የተሻሉ ዘሮች መካከልም ከፍተኛ የዝናብ መጠን ለሚያገኘዉም  ሆነ ለበረሃማ አካባቢ የሚሆኑት ለየቦታዉ እንደተዳረሱም ይዘረዝራሉ።

«ከማሽላ ዉጪ የቦቆሎ ዝርያዎችም አሉ። ለምሳሌ ከፍተኛ ዝናብ ላለበት አካባቢ ተስማሚ የሚሆን ለከፍታ ቦታዊ የሚሆን መካከለኛ ሆነዉ ዝናብ ያለባቸዉ ቦታዎች የሚሆኑ ዝርያዎች ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ዝቅተኛ ሆነዉ ዝናብ ያላቸዉም አሉ። ለእነዛ የሚሆኑ ዝርያዎች፤ ከዚያም ባለፈ ድርቅ ለሚያጠቃዉ አካባቢ በአነስተኛ ርጥበት ምርት ሊሰጡ የሚችሉ ዝርያዎች አሉ። በመቆሎም ደረጃ የወጡ። ከዚያ በተጨማሪ የቆላ ስንዴ ዝርያዎችም አዉጥተናል። አሁን አፋር ዉስጥ በሰፊዉ እየተመረተ ያለ የቆላ ስንዴ ዝርያዎች ናቸዉ እነዚህ የስንዴ ዝርያዎች አርብቶ አደሩ እነዚህን በመዝራት ዉጤት ያገኘበት እና በዚያ አካባቢ ተስማሚ መሆናቸዉን ያረጋገጥነዉ እነዚህ ዝርያዎች አሁን በስፋት ወደአርብቶ አደሩ እየገቡ ስንዴ እያመረተ የሚገኝበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ። ይኼ ባለፈዉም ዓመት ሰርተን የተለያዩ አካላት እንዲጎበኙ አድርገናል። አፋር ላይ ወረር ግብርና ምርምር አለን መልካ ወረር የሚባል፣ እሱ በስፋት ይሄንን አካባቢ ይዞ እየሠራ ይገኛል»

በዚህ ብቻ አያበቃም ለድርቅ አካባቢ የሚሆኑ የተቋሙ የምርምር ዉጤቶች፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጠናበት ድርቅ ከብቶችን ክፉኛ መጎዳቱ በሚነገርለት የሶማሌ ክልል አካባቢም ለእንስሳቱ መኖ የሚሆን በቶሎ ሊደርስ የሚችል ዘር አቅርቧል። ለማሳያነትም በ250 ሄክታር ላይ በአጭር ጊዜ የደረሰዉን የእንስሳት መኖም መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የተለያዩ አካላት እንደጎበኙትም ዘርዝረዋል።

Äthiopien - Äthiopisches landwirtschaftliches Forschungsinstitut - Verbesserte Samen auf dem Feld
ምስል S. Yemaneh

«ይኼ በዘላቂነት በዚያ ክልል ድርቅን ተከትሎ ለሚፈጠሩ ችግሮች በመኖ ዘር አቅርቦት ደረጃ በስፋት ችግሩን እንዲፈታ ነዉ የሚሰራዉ። አሁን 250 ሄክታር ላይ የተጀመረዉ ሥራ ወደ 1,000 ሄክታር በማሳደግ ሌሎች የዉኃ አቅርቦት ያለባቸዉ ቦታዎች ላይ እያባዛን የመኖ ክምችት እንዲፈጠር ፤ ዘሩም እዚያ እንዲኖር አርብቶ አደሩም ያንን በመጠቀም ከብቶቹን የሚመግብበት ሁኔታ እሱ ላይ ሰርተን ዉጤት አግኝተናል።»

እሳቸዉ እንደሚሉትም ለእንስሳት መኖ ብቻ ሳይሆን ን ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸዉ አካባቢዎች   ለሰዎች ጥቅም የሚዉሉ እንደ ሩዝ እና ስንዴ የመሳሰሉ የተሻሻሉ የእህል ዘሮች ተሞክረዉ ዝግጁ ናቸዉ። አቶ ፍሰሐ እንደሚሉት ከ1993ዓ,ም ወዲህ አርሶ አደሩ ኅብረተሰብ እንዲህ ያለዉ የምርምር ዉጤት እገዛ ምርታማነትን ማሻሻል እንደማይቻል ተገንዝቧል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ