የኤኳቶርያል ጊኒ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 23.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኤኳቶርያል ጊኒ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ

ፕሬዚደንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ ካለፉት 37 ዓመታት ወዲህ በስልጣን ላይ ይገኛሉ። ከአፍሪቃ መሪዎች ሁሉ ለረጅም ዓመታት ስልጣን የጨበጡት የ73 ዓመቱ ኦቢያንግ ንጌማ የስልጣን ዘመናቸውን ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ለማራዘም በነገው ዕለት በሀገሪቱ በሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫም ላይ እንደገና በተወዳዳሪነት ይቀርባሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:03 ደቂቃ

ኤኳቶርያል ጊኒ

በኤኳቶርያል ጊኒ ካሉት ትልቆቹ የነዳጅ ዘይት ንጣፎች መካከል አንዱ ፑንቶ ኦይሮፓ ሲሆን፣ በዚሁ ከመሀል ሀገር 200 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የቢዮኮ ደሴት ባለው ስፍራ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ማውጣት ሂደት ተጧጡፎ ይካሄዳል፤ በዚሁ ሂደት ውስጥም በየሌሊቱ የእሳት ነበልባል ከሩቁ ይታያል። የተፈጥሮ ሀብቷ ነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ለኤኳቶርያል ጊኒ ብልፅግና ያስገኘላት ሲሆን፣ በዓለም ባንክ ዘገባ መሰረት፣ በሀገሪቱ አማካዩ የነፍስ ወከፍ ገቢ 23,000 ዩኤስ ዶላር ነው። ይህ ታንዛንያ ወይም ሴኔጋልን ከመሳሳሉ አፍሪቃውያት ወይም ሀንጋሪን ከመሳሰሉ አውሮጳውያት ሀገራት ጋር ሲነፃፀር በአስር እጥፍ በልጦ ነው የተገኘው።

ከነዳጅ ዘይቱ እና ከጋዙ ሀብት ሽያጭ ይገኛል የሚባለው ገቢ ግን ለብዙዎቹ የኤኳቶርያል ጊኒ ዜጎች በፑንቶ ኦይሮፓ በየሌሊቱ ከሩቅ እንደሚታየው የእሳት ነበልባል ርቋቸዋል፣ በሌላ አነጋጋር ለሕዝቡ አንዳችም ጥቅም አላስገኘም ሲሉ ቱቱ አሊካንቴ ተችተዋል። መንበሩን ዩኤስ አሜሪካ ያደረገውን እና «ኢ ጂ ጃስቲስ» በመባል የሚታወቀውን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያቋቋሙት ጠበቃው ቱቱ አሊካንቴ ካለፉት ብዙ ዓመታት ወዲህ ለትውልድ ሀገራቸው ኤኳቶርያል ጊኒ ሰብዓዊ መብት ይዞታ በመታገል ላይ ይገኛሉ።

«በኤኳቶርያል ጊኒ ሀኪም ቤቶች እና ክሊኒኮች የሉም፣ የትምህርቱም ስርዓት በጣም ደካማ ነው። ንፁሕ ውኃ እና ኮሬንቲ ማግኘት ለብዙዉ የሀገሪቱ ሕዝብ ዛሬም ሕልም ብቻ ሆኖ ነው የቀረው።»

በአፍሪቃ የኤኳቶርያል ጊኒ ፕሬዚደንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማን ያህል በስልጣን የቆየ መሪ የለም። ኦቢያንግ እጎአ ነሀሴ ሶስት፣ 1979 ዓም ነበር ስልጣኑን የጨበጡት። ቴዎዶሮ ኦቢያንግ በዚሁ ዕለት ባካሄዱት መፈንቅለ መንግሥት አጎታቸው ፍራንሲስኮ ማቺያስ ንጌማ ን አስገድለው አቋቁመውት የነበረውን አሸባሪ መንግሥት አስወግደዋል። ይሁን እንጂ፣ ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በኤኳቶርያል ጊኒ ስርዓተ ዴሞክራሲ ይተክላሉ ብሎ የጠበቀ ከነበረ ይኸው ምኞቱ ገሀድ አልሆነለትም። እርግጥ፣ ፕሬዚደንት ኦቢያንግ፣ በአጎታቸው አንፃር ዜጎች ይገደሉ የነበሩበትን አሰራር እንዳስቀሩ በይፋ ቢናገሩም፣ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅትን የመሰሉ ቡድኖች ካለፉት ብዙ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ በተቃዋሚዎች እና ለመንግሥቱ በማይመቹ ወገኖች ላይ ቁም ስቅል የማሳየቱ እና በዘፈቀደ የማሰሩ ተግባር እንደቀጠለ ነው ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል።

ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጌማ እጎአ በ2009 ዓም በተካሄደው ምርጫ ላይ 97% የመራጩን ድምፅ በማግኘት የስልጣን ዘመናቸውን በሰባት ዓመታት አራዝመዋል። ገዢው የኤኳቶርያል ጊኒ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲያቸውም በሀገሪቱ በተካሄዱት ምክር ቤታዊ ምርጫዎች ሁሌ ተመሳሳዩን አብላጫ ድምፅ ነው የሚያገኘው። በአሁኑ ጊዜ በኤኳቶርያል ጊኒ የተቃዋሚው ቡድን በሕግ መምሪያ እና በሕግ መወሰኛው ምክር ቤቶች ውስጥ በሁለት እንደራሴዎች ብቻ መወከላቸውን «ቲያክ» በመባል የሚታወቀው መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ባልደረባ ዦአኦ ፓውሎ ባታልሀ በማስታወቅ፣ የኤኳቶርያል ጊኒ ምርጫዎች ሁሉ ለይስሙላ የሚደረጉ ናቸው በማለት ተችተዋል።

« በኤኳቶርያል ጊኒ ታሪክ እንደታየው፣ በሀገሪቱ ብዙ የተጭበረበሩ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በነገው ዕለት በሚደረገው ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ዝግጅትም ላይ የምናየው ኤኳቶርያል ጊኒን ስርዓተ ዴሞክራሲን የምትከተል ሀገር አድርጎ ለማቅረብ የተያዘውን ሙከራ ነው። ይሁን እንጂ፣ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ሁሉ እንዳረጋገጡት፣ ኤኳቶርያል ጊኒ ዴሞክራሲያዊ አሰራር የሌላት ሀገር ናት። »

በነገው ዕለት በኤኳቶርያል ጊኒ የሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫም ነፃ እና ትክክለኛ ይሆናል ብለው እንደማይገምቱ የፖለቲካ ተንታኞች እና ታዛቢዎች ገልጸዋል።

አስመራጩ ኮሚሽን ለፕሬዚደንት ኦቢያንግ ንጌማ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉትን የታወቁትን የተቃዋሚ «የማሻሻያ ሕዝባዊ ፓርቲ » ፖለቲከኛ ጋብርየል ንሴ ኦቢያንግ ኦቦኖንን፣ ከምርጫው በፊት በነበሩት አምስት ዓመታት ውስጥ ሳይቋርጡ በሀገሪቱ መኖር አለባቸው የሚለውን በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሰውን ትዕዛዝ አላሟሉም በሚል ምክንያት፣በምርጫው በተወዳዳሪነት እንዳይቀርቡ ከልክሎዋል። በዚህም የተነሳ የተቃዋሚ «የማሻሻያ ሕዝባዊ ፓርቲ » ፖለቲከኛ ጋብርየል ንሴ ኦቢያንግ ኦቦኖንን፣ የጋብርየል ንሴ ኦቢያንግ ኦቦኖ «የማሻሻያ ሕዝባዊ ፓርቲ » ከነገው ምርጫ ለመራቅ ወስኖዋል። በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጠቃለሉበት ቡድንም አባላቱ በምርጫው ሂደት ውስጥ እንዳይሳተፉ ባለፈው መጋቢት ወር ጥሪ አስተላልፎዋል። መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት «ቲያክ» ባልደረባ ዦአኦ ፓውሎ ባታልሀ የምርጫው ምህዳር ለተቃዋሚው ወገን እጅግ የጠበበ መሆኑን ነው የገለጹት።

« የተቃዋሚ ወገኖች ሕዝቡ ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ እንዲርቅ ጥሪ አቅርበዋል። ምክንያቱም፣ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት የምርጫውን ዝግጅት፣ የመንግሥቱን ተቋማት እና የመገናኛ ብዙኃኑን በጠቅላላ በመቆጣጠራቸው፣ እርሳቸው የሚያስተላልፉት መልዕክት ብቻ ነው ለሕዝብ የሚደርሰው። የተቃዋሚው ወገን ቦታ አላገኘም። የኤኳቶርያል ጊኒ መንግሥት በጣም ጨቋኝ መንግሥት ነው።»

የምርጫው ዘመቻ በተጀመረበት ጊዜ ፕሬዚደንት ኦቢያንግ ንጌማ ለመጨረሻ ጊዜ በእጩ ተወዳዳሪነት መቅረባቸውን አስታውቀዋል። ይሁንና፣ የኤኳቶርያል ጊኒ ስልጣን ወደፊትም በኦቢያንግ ንጌማ ቤተሰብ እጅ ሊቆይ ይችላል በሚል በሕዝቡ ዘንድ ስጋት መኖሩን መንግሥታዊ ያልሆነው የ«ኢ ጂ ጃስቲስ» ድርጅት የመብት ተሟጋቹ ጠበቃው ቱቱ አሊካንቴ ገልጸዋል።

« ከምርጫው ከራቅን ኦቢያንግ ያሸንፋሉ። ከምርጫው ባንርቅም ፕሬዚደንቱ ማሸነፋቸው አይቀርም። ስለዚህ ከምርጫ መራቅ አለመራቅ በምርጫው ውጤት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ያም ቢሆንም ግን፣ ሕዝቡ ድምፅ ከመስጠቱ ሂደት የሚርቅበት ርምጃው ፕሬዚደንቱ ሕጋዊ እውቅና አለማግኘታቸውን መልዕክት ያስተላልፋል። ኦቢያንግ ስልጣናቸውን እጎአ በ2020 እንደሚያበቁ አስታውቀዋል። ይሁንና፣ ስጋታችን ፕሬዚደንቱ በዚያን ጊዜ አሁን የምክትል ፕሬዚደንትነቱን ስልጣን የያዙትን ልጃቸውን ቴዎዶሪን ኦቢያንግን ተተኪያቸው አድርገው የስልጣን ኮርቻ ላይ እንዳያስቀምጡ ነው። »
ኤኳቶርያል ጊኒ ከስጳኝ ቅኝ አገዛዝ ከተላቀቀች እጎአ ከ 1968 ዓም ወዲህ የሀገሪቱን ስልጣን የያዙት የኦቢያንግ ቤተሰብ አባላት ብቻ ሲሆኑ፣ ሂደቶች በዚሁ ሁኔታ ከቀጠሉ ሶስተኛውም ፕሬዚደንት ኦቢያንግ የሚባል ሊሆን ይችላል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic