የኤ.ኤን.ሲ መሪ ምርጫ ውጤት | አፍሪቃ | DW | 19.12.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኤ.ኤን.ሲ መሪ ምርጫ ውጤት

የኤ.ኤን.ሲ መሪ ምርጫ በቀድሞው የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ አሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ አስቀድሞም ሲወሳ የቆየ ጉዳይ ነው ።

ታቦ ኢምቤኪና ጃኮብ ዙማ

ታቦ ኢምቤኪና ጃኮብ ዙማ

ከደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ታቦ ኢምቤኪ ጋር ለአንጋፋው የደቡብ አፍሪቃ የፖለቲካ ፓርቲ የአፍሪቃ ብሄራዊ ምክርቤት መሪነት የተወዳደሩት ጃኮብ ዙማ የፓርቲያቸውን አባላት አብላጫ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል ። እ.አ.አ በሁለት ሺህ ዘጠኝ የኤምቤኪ የስልጣን ዘመን ሲያበቃም ዙማ የፕሬዝዳንትነቱን መንበር መረከባቸው እንደማይቀር ከወዲሁ እየተነገረ ነው ። ዙማ የደቡብ አፍሪቃ መሪ ከሆኑም የምጣኔ ሀብት መርህ ለውጥ ያደርጋሉ የሚል ሰፊ ግምት አለ ። ሆኖም ዙማ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት ከዚህ ቀደም በቀረበቡባቸው ከሙስና ጋር በተያያዙ ልዩ ልዩ ክሶች ምክንያት ሊታሰሩ እንደሚችሉም የሚናገሩ አልጠፉም ። የአፍሪቃ ብሄራዊ ምክርቤት የኤ.ኤን.ሲ መሪ ምርጫ በቀድሞው የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ አሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ አስቀድሞም ሲወሳ የቆየ ጉዳይ ነው ። ከውጤቱ አዲስ ሊባል የሚችለው ለፓርቲ መሪነት ለተወዳደሩት ለደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ታቦ ኢምቤኪና ለቀድሞው ምክትላቸው ጃኮብ ዙማ የተሰጠው ድምፅ ብዛት ብቻ ነው ። በዚህ ምርጫ ዙማ ኢምቤኪን በሰፊ ልዩነት ነው ያሸነፉዋቸው። « ጓድ ታቦ ኢምቤኪ ያገኙት ድምፅ 1505 ፤ አመሰግናለሁ ! መቀጠል እችላለሁ ? እባካችሁ ጓዶች መቀጠል እችላለሁ ? ጃኮብ ዙማ ያገኙት ድምፅ 2329 »
ከዕሁድ አንስቶ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከተገኙት አራት ሺህ የአፍሪቃ ብሄራዊ ምክርቤት ተወካዮች አብዛኛዎቹ ዙማ ምርጫቸው መሆናቸውን ድምፅ ከመሰጠታቸው በፊት በስብሰባው ላይ ባስተጋቡዋቸው የድጋፍ መግለጫዎች በይፋ አሳውቀዋል ። የዙማ ደጋፊዎች ኢምቤኪ ባሉበት ዙማን ከማወደስ አልፈው የኢምቤኪን ንግግርም ከማወክ ወደ ኃላ አላሉም ። እነዚህ ምልክቶችም ታቦ ኢምቤኪ አለመፈለጋቸውንና በድጋሚ ለመሪነት እንደማይመረጡም በግልፅ አሳይተዋል ። ምንም እንኳን በኢምቤኪ የስልጣን ዘመን በደቡብ አፍሪቃ በድህነት ቅነሳው አቅጣጫ ለውጥ ቢታይም በሀብታሙና በድሀው ህብረተሰብ መካከል የኑሮው ልዩነት እጅግ እየሰፋ መሄዱ ኢምቢኬን ድጋፍ ያሳጣቸው አብይ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል ። ከዚሁ ጋርም በርሳቸው ፕሬዝዳንትነት ወጣቱ በከፍተኛ ደረጃ ስራ አጥ መሆኑ ሌላው ተወዳጅነት ያሳጣቸው ነጥብ ነው ። እነዚህን መሰል የሀገሪቱ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች አለመፈታታቸው ነው የፓርቲው አባላት ኢምቤኪን ፊት እንዲነሱዋቸው ምክንያት ሆነዋል ። በዚህ ማህበራዊ ቀውስ ሰበብም አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት አዲሱ የኤ ኤን ሲ መሪ ዙማ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ በሀገሪቱ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተሀድሶ የሚያመጡ መሲህ ሆነው ነው የሚታዩት ፤ ሌሎች ደግሞ ዙማን መደገፉ እርሳቸውን እንደ ለውጥ አምጭ አድርጎ ከማየት የመጣ አይደለም ። ይልቁንም በኢምቤኪና በተወሰነው የአመራር ዘይቤያቸው ላይ የሚካሄድ አመፅ ነው እንጂ ፤ ብለዋል ። ይህ ዓይነቱ ችግር በነርሱ አባባል በሀገሪቱ ላይ አደጋ ማስከተሉ አይቀርም ። በሁለቱ አንጋፋ የደቡብ አፍሪቃ የነፃነት ታጋዮች መካከል የተፈጠረው ይህ አለመግባባት በአጭር ካልተቀጨ በተለያየ አቅጣጫ አለመረጋጋትን ማስከተሉ አይቀርም ። በተለይ ከዚህ ቀደም በዙማ ላይ የተነሱት ከሙስና ጋር የተያያዙ ክሶች እንደገና ከተቀሰቀሱ የሀገሪቱን ደህንነት ሊያናጋ ይችላልም እየተባለ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት ብዙ ሚሊዮን ዶላር ከሚያወጣ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል ጋር የተያያዘ የሙስና ክስ ከቀረበባቸው በኃላ ነበር ዙማ ከምክትል ፕሬዝዳንትነት የወረዱት ። ከሁለት ዓመት በኃላ የኤ ኤን ሲ መሪነቱን ስልጣን የያዙት ዙማ የድጋፋቸው መሰረት ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍልና ጠንካራው የሀገሪቱ የሰራተኛ ማህበር በመሆኑ የምጣኔ ሀብት መርሀቸውን ወደ ግራ አቅጣጫ ያስተላክላሉ የሚል ሰፊ ግምት አለ ። በምህፃሩ ኮሳቱ የሚባለው ታዋቂው የሰራተኛ ማህበር ከአሁኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት የደቡብ አፍሪቃ ድሆችና ስራ አጦች በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ መንግስት የብድር ፖሊሲውን እንዲያላላ ጠይቋል ። እአአ በሁለት ሺህ ዘጠኝ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ ከወዲሁ የሚነገርላቸው ጃኮብ ዙማ አጠቃላዩን ምርጫ ለማፋጠን በታቦ ኢምቤኪ ላይ የመታመኛ ድምፅ እንዲሰጥ ጫና ያደርጋሉም እየተባለ ነው ። ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ደግሞ ዙማ ፓርላማ ውስጥ ከገቡት ሁለት መቶ ዘጠና አራት የኤ ኤን ሲ አባላት የሁለት መቶ አንዱን ድምፅ ማግኘት ይኖርባቸዋል ።