የኤነርጂ ፍጆት መጨመር ዓቢይ የኤኮኖሚ ዕድገት ፈተና? | ኤኮኖሚ | DW | 27.04.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኤነርጂ ፍጆት መጨመር ዓቢይ የኤኮኖሚ ዕድገት ፈተና?

የሩሢያና የአክራኒያ የጋዝ ውዝግብ፣ የኢራን የአቶም መርሃ-ግብር የቀሰቀሰው ውጥረትና የኢራቅ መልሶ-ግንባታ መጎተት፤ እንዲሁም የናይጄሪያ የነዳጅ ዘይት አካባቢ ሰላም ማጣትና የዓለምአቀፍ ፍጆቱም ማየል፤ እነዚህ ሁሉ በዓለም ላይ በኤነርጂው አቅርቦት በኩል ጎጂ ተጽዕኖ አላቸው።

ናሪው የቤንዚን ዋጋ

ናሪው የቤንዚን ዋጋ

የነዳጅ ዘይት ዋጋ ባለፉት ዓመታት ከመጠን በላይ እየናረ ነው የመጣው። እርግጥ ችግሩ ፖለቲካዊ መንስዔ ብቻ ያለው አይደለም። የወደፊቱን የኤነርጂ አቅርቦት ዕጣ ብቻውን ይወስናል ለማለትም አይቻልም። ግን በወቅቱ ይሄው የወደፊቱ ዕጣ ነው ከሁሉም በላይ ዓለምን ወደ ኋላ ታሪኩ እየመለሰው ያለው። ሰላሣ ዓመታት ሙሉ ሲሰነዘር የኖረው ማስጠንቀቂያ ሁሉ ሰሚ ጆሮ አላገኘም። የኤነርጂው አቅርቦት ችግር ሰሞኑን ከዋሺንግተን እስከ ጀርመን በዚህ በሃኖቨር ከተማ በሚካሄደው የኢንዱስትሪ ምርት ትዕይንት ጭምር ዓቢይ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነው የሰነበተው።

የነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሚል የሰባ ዶላርን ወሰን በማለፍ ከዚህ ቀደም ባለነበረ መጠን መናሩ በምዕራቡ ዓለም ከዓመታት ቀስው በኋላ መልሶ መንሰራራት የያዘው የኤኮኖሚ ዕድገት በአጭር እንዳይቀጭ ሥጋት ማሳደሩ አልቀረም። በዚሁ የተነሣም የሰባቱ ቀደምት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት የፊናንስ ሚኒስትሮች ባለፈው አርብ ዋሺንግተን ላይ ተገናኝተው ይሄው የዋጋ መናር በሚኖረው ሁል-አቀፍ ተጽዕኖ ላይ መክረዋል።
በዓለም ኤኮኖሚ የዕድገት አዝማሚያ አጠቃላይ እርካታ ቢኖርም የጀርመኑ የገንዘብ ሚኒስትር ፔር ስታይንብሩክ እንዳሉት የነዳጅ ዘይት ዋጋ የፈጠረው አደጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። “በዚህ በዋሺንግተን እስካሁን በአንድ ቀን ተኩል ጊዜ ውስጥ ተገናኝቼ ካነጋገርኳቸው ፖለቲከኞች መካከል አደጋውን ያልተገነዘበ አንድም አላጋጠመኝም” ነው ያሉት የጀርመኑ ባለሥልጣን!

በተለይ የመካከለኛው ምሥራቅ አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ስጋቱን ያጠነከረው። በኢራን ላይ ማንም የማይመኘው ወታደራዊ ጥቃት ከደረሰ ዕርምጃው በነዳጅ ዘይት አቅርቦቱ አኳያና በዋጋውም በኩል ሥር-ሰደስ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የብዙዎች ዕምነት ነው። ለማንኛውም የሰባቱ ሃያላን መንግሥታት የፊናንስ ተጠሪዎች የምርቱን ስፋት ከፍጆቱ አጣጥሞ ለማሳደግ በነዳጅ ዘይት በታደሉትና በገዢዎዎቹ አገሮች መካከል የተሻለ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ ሰንዝረዋል።


የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር፣ አቅርቦትና ፍጆቱ፤ በዚህ በጀርመን በሃኖቨር ከተማ ባለፈው ሰኞ በተከፈተው ዓለምአቀፍ የኢንዱስትሪ ትዕይንት ላይም ዓቢይ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ነው የሰነበተው። በዘንድሮው ትዕይንት ዋነኛዋ ምርት አቅራቢና የጀርመን ኢንዱስትሪዎች ሸሪክ በወቅቱ እስከ 9 በመቶ አስደናቂ ዓመታዊ ዕድገት በማድረግ ላይ የምትገኘው ሕንድ እንደመሆኗም መጠን ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሢንግ ሣይቀር ወደ ሃኖቨር ብቅ ማለታቸው አልቀረም።
ከ 66 አገሮች የመጡ 5,200 አምራቾች በሚሳተፉበት በዘንድሮው ትዕይንት በተፋጠነ ዕድገት ላይ የምትገኘው ሕንድ በ 340 ኩባንያዎቿ አማካይነት የተለያዩ ምርቶቿን እያስተዋወቀች ነው። ኤነርጂን በተመለከተ የወደፊት ፍላጎቷ በፍጥነት እየጨመረ እንደሚሄድ ጉልህ መሆኑም አልቀረም። የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርከል የጉዳዩን ክብደት ሲገልጹ “ሁሉም አገሮች እንዴት የረባ የኤነርጂ መሠረት ሊኖራቸው ይችላል? የሚለው ጥያቄ ከ 21ኛው ምዕተ-ዓመት ማዕከላዊ ጥያቄዎች መካከል አንዱ እንደሚሆን የሚሰማን ጉዳይ ነው” ብለዋል።

በሃኖቨሩ ውይይት ሕንድን ወክለው የተሳተፉት ምክትል የኤነርጂ ሚኒስትር R.V. Shani እንደሚሉት ሕንድ በሚቀጥሉት ሰላሣ ዓመታት በየአሥር ዓመቱ የኤነርጂ ብቃቷን በእጥፍ መጨመር ይኖርባታል። ሕንድ በእርግጥ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የምትገኘው ቻይናም ይበልጥ ኤነርጂ የሚፈጁ እየሆኑ ነው የመጡት። በመሆኑም የኤነርጂ አቅርቦት ችግር በዓለም ላይ የጋለ ክርክር እንዲካሄድበት እያደረገ ያለው አንዱም ምክንያት ይሄው ነው።

በዓለም ላይ ታላቁ በሆነው በሃኖቨሩ የኢንዱስትሪ ትዕይንት የጀርመንና የሩሢያ ተጠሪዎችም በኤኮኖሚ ግንኙነታቸው ላይ ዓቢይ በሆነው በኤነርጂው ጉዳይ ተነጋግረዋል። የሩሢያው መንግሥታዊ የጋዝ ሞኖፖል ጋዝፕሮም ወደ አውሮፓው የኤሌክትሪክ ሃይል ገበያ ሰርጎ ለመግባት የሚያደርገው ጥረት ታላቅ ተቃውሞ ገጥሞት እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው። በመሆኑም የኩባንያው አስተዳዳሪ ሚለር የጋዝ አቅርቦታቸውን በሌላ አቅጣጫ ሊያራምዱ እንደሚችሉ በማመልከት ግፊት እስከማድረግ ደርሰዋል።
የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭም በሃኖቨሩ ትዕይንት አኳያ የተናገሩት የጀርመንን ስጋት የሚያለዝብ አይደለም። “ጋዝን በተመለከተ በሚደረገው ትብብር ሁለት ዓላማዎች ወሣኝኝነት ሊኖራቸው ይገባል። አንደኛው ለነበረው፤ በተለይም ለአውሮፓ ቅድሚያ ሰጥቶ መቀጠል ነው። ግን የኤነርጂው ፍሰት በሌላ አቅጣጫም መስፋፋት ይኖርበታል።” ነው ያሉት። በሌላ አነጋገር ሩሢያ በጋዝ አቅርቦቷ ወደ ቻይናና ወደ ጃፓን ለማዘንበል እንደምትችል ማስጠንቀቋ ነው።
በኤነርጂ ችግር ላይ ይህን መሰሉ ጠንካራ ክርክር ሲደረግም ሆነ ስጋቱ ጠንክሮ ሲታይ ከሰባናዎቹ ዓመታት ወዲህ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ያኔ አረብ መንግሥታት ነዳጅ ዘይት ማቅረባቸውን በማቆማቸው የምርቱ ዋጋ በበርሚል በአንዴ ከሶሥት ወደ አምሥት ዶላር ማደጉ አይዘነጋም። ዛሬ የነዳጅ ዘይት ዋጋ እንዲያውም በበርሚል ከሰባ ዶላር በልጧል። በተጠቃሚዎቹም ሆነ በአምራቾቹ ላይ ያለው ግፊትም ከባድ ከመሆኑ የተነሣ አጠቃላይ ተጽዕኖው ከሰላሣ ዓመታት በፊት ከነበረው እጅግ የሚበልጥ ነው።

በተፋጠነው ፍጆት በዓለም ገበያ ላይ የተፈጠረውን ዕጥረት ለመሸፈን ምርቱን በሰፊው የማምረቱ ግፊት እየጨመረ መምጣቱን መረዳቱ ብዙም አያዳግትም። በነዳጅ ዘይት በታደሉት አካባቢዎች አለመረጋጋት መስፋፋቱ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ያከብደዋል። ከመጠን በል እየጨመረ የሚሄደውን የኤነርጂ ፍጆት ለመሸፈን የተያዘው ይህን መሰሉ ጥረት የተፈጥሮ ሚዛን የበለጠ ለአደጋ መጋለጡንም የሚጠቁም ነው። የሮማ ክበብ በመባል የሚታወቀው ስብስብ ገና በ 70 ኛዎቹ ዓመታት “ዕድገት በወሰን” በሚል መፈክር በዚህ አኳያ ጨለማ የለበሰ ትንበያ ነበር ያደረገው።

ለተፈጥሮ ጥበቃ ፖሊሲ ጠንካራ መሻሻል ካልተደረገ ዓለም ለተፈጥሮ ቀውስና ለረሃብ ነው የሚጋለጠው ሲል ነበር ያስጠነቀቀው። ዛሬ ከ 34 ዓመታት በኋላ ሊቀ-መንበሩ የዮርዳኖሱ ልዑል ሃሰን “ሰላሣ ዓመታት ሙሉ ማስጠንቀቂያው ችላ ተብሎ ነው የቆየው” ሲሉ የዓለም ሰሜንና ደቡባዊ ክፍላት በተቻለ ፍጥነት ተባብረው መሥራት እንደሚኖርባቸው ያሳስባሉ።

ብዙ የጸሃይ ብርሃንና የንፋስ ሃይል ባላቸውና በተጠቃሚዎቹ ወይም ፈጂዎቹ አካባቢዎች፤ ማለትም በሁለቱ የዓለም ክፍላት መካከል ያለውን ርቀት ማሸነፍ ከተቻለ አይገድም። ይህ እንዲሆን ደግሞ በዓለም ዙሪያ ሃይል አከማችና አመላላሽ ወይም አቀባባይ ዘዴዎችን ለማዳበር ብዙ ወጩ ጪ ማድረጉ ግድ ነው። ዛሬ ይህ ነው የሚጎለው ትልቁ ችግር። ዋናውም ምክንያት የዕውቀቱ መጓሰል ሣይሆን ውድነቱ ነው።

ለማንኛውም ወደፊት ሰፊ እየሆነ የሚሄደውን የኤነርጂ ፍጆት ለመሸፈን ታዳሽ የሆኑትን የጸሃይን፣ የንፋስንና መሰል የሃይል ምንጮች ቴክኖሎጂ ማስፋፋቱ፤ ገቢር ማድረጉም አማራጭ አይኖረውም። የነዳጅ ዘይት ሃብትንና የማዕድን ከሰልን የመሳሰሉት የሃይል ምንጮች እየሟጠጡ የሚሄዱ ናቸው። በሌላ በኩል በተለይ ታዳጊው ዓለም ተፈጥሮ የሰጠውን የጸሃይ ጸጋ ተጠቅሞ የአካባቢውን ደህንነት የጠበቀ ልማት ለማድረግ እንደሚችል አንድና ሁለት የለውም።

ምናልባት የወቅቱ የኤነርጂ ችግር ለታዳሹ የሃይል ምንጭ መስፋፋት የእመርታ ዕድል ይሆን? ቢሆን ምንኛ በበጀ! በአጠቃላይ ግን በበለጸገው ዓለም ይህን ከማራመድ ይልቅ በአቶም ሃይል ጣቢያዎች ችግሩን እንወጣ ሲል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መስፋፋት የተያዘው ውይይት ለዚህ የሚያበረታታ አይደለም። የአቶም ሃይል በነዳጅ ዘይት ላይ ያለውን ጥገኝነት የሚያለዝብ ቢሆንም አደገኛነቱ ከኤኮኖሚው ጥቅም ሲነጻጸር የከፋ መሆኑ የማይታበል ነው።