የኤች አይቪ ስርጭት በመላዉ ዓለም | ጤና እና አካባቢ | DW | 05.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የኤች አይቪ ስርጭት በመላዉ ዓለም

በዓለም ኤች አይቪ በደሙ ዉስጥ የሚገኘዉ ሕዝብ 37 ሚሊየን ማለትም ከካናዳ የሕዝብ ብዛት ጋር እንደሚቀራረብ ነዉ ባለፈዉ ሳምንት ይፋ የተደረገዉ። ቁጥርሩ ካለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2016 ሰኔ ወዲህ ያለዉን ሲያመለክት፤ ከኤድስ ጋር በተያያዘም የ1 ሚሊየን ሰዉ ሕይወት አልፏል። 21 ሚሊየን ታማሚዎችም የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት ማግኘት ችለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:41

በአዉሮጳ እና እስያ ሃገራት የተሐዋሲዉ ስርጭት አስግቷል፤

በየዓመቱ በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር ዲሴምበር 1 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ታኅሳስ 22 ቀን የዓለም የኤድስ ቀን ይታሰባል። በዚህ ዕለት የሚወጡት ዘገባዎች ያለፈዉን ዓመት የበሽታዉን ስርጭት፣ ያደረሰዉን የጉዳት መጠን እንዲሁም ለታማሚዎች የሚሰጠዉን የህክምና አገልግሎት የሚያስቃኙ ናቸዉ። ከተመድ ኤይድስ ላይ የሚያተኩረዉ ተቋም UNAIDS ዘንድሮዉ ያወጣዉ መረጃ በዓለም ደረጃ ወንዶች የኤች አይቪ ህክምናን የመዉሰድና መከታተላቸዉ ነገር አሳሳቢ መሆኑን ያመለክታል። በዚህም ምክንያት ድርጅቱ ወንዶች ፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት የመጠቀማቸዉ ሁኔታ ዝቅተኛ በመሆኑ ከኤድስ ጋር በሚያያዙ በሽታዎች የመሞታቸዉ ዕድልም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አሳስቧል። ይህን አስመልክተዉ ባለፈዉ ዓርብ ዕለት ከጄኔቫ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የUNAIDS የስልት ዘርፍ ኃላፊ ፒተር ጊይስ በተለይ አፍሪቃ ዉስጥ ወንዶች HIV በደማቸዉ ዉስጥ እንደሚገኝ የመመርመር ፍላጎት እንደሌላቸዉ፤ በተሐዋሲዉ መያዛያቸዉን ካወቁ በኋላም ህክምናዉን የመከታተል ግንዛቤያቸዉ ከሴቶች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

«ከሴቶች ጋር ሲነፃፀር ያሉትን አገልግሎቶች በመጠቀም ረገድ የወንዶች ቁጥር አነስተኛ ነዉ፤ የHIV ምርመራ የሚያደርጉትም ሆነ ተሐዋሲዉ በደማቸዉ ዉስጥ እያለ በበሽታዉ መያዛቸዉን የሚያዉቁት ወንዶች ቁጥር ከሴቶች አኳያ ሲታይ ትንሽ ነዉ። ከሴቶች ጋር ሲወዳደር 20 በመቶ የሚሆኑት የጤና ይዞታቸዉን እንደማያዉቁ ይገመታል።»  

እንዲህም ሆኖ ህክምናዉን የሚጀምሩ ወንዶች ቢኖሩም እንኳ ክትትልም እና ትኩረት እንደማይሰጡት ኃላፊዉ ሳይጠቅሱ አላለፉም። እንዲህ አይነቱን መዘናጋት ለመቀስቀስ እና ለበሽታዉ ትኩረት እንዲሰጡ የሚረዳ ቴክኒዎሎጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተዘጋጅቷልም ይላሉ።

«ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስማትፎን ላይ በሚጫኑ አፕሊኬሽኖች አማካኝነት ቴክኒዎሎጂዉ ሰዎች የHIV ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ስልት አቅርቧል። ይህ ብቻ ሳይሆን መመርመሪያ ቦታዉ በአቅራቢያዉ የቱ ጋር እንደሚገኝ ሁሉ ይጠቁማል።»

ይህ ምንአልባት ቸልታ ለሚያሳዩ ወገኖች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ዋናዉ ግን ሰዎች የጤናቸዉን ይዞታ በማወቅ የራሳቸዉንም ሆነ የተጓዳኞቻቸዉን ሕይወት ለአደጋ አሳልፈዉ እንዳይሰጡ ሊያደርጉ የሚገባዉን ጥንቃቄ ልብ ማለቱ ነዉ።

በሌላ በኩል የዓለም የኤድስ ቀን ሲታሰብ ይፋ የሆነዉ ሌላዉ መረጃ ደግሞ የተሐዋሲዉ ስርጭት አፍሪቃ ዉስጥ 29 በመቶ መቀነሱን በተቃራኒዉ ደግሞ ምሥራቅ አዉሮጳ ሃገራት እና በማዕከላዊ እስያ በ60 በመቶ መጨመሩን ያመለክታል። በዚሁ ዓመት አዉሮጳ ዉስጥ የተካሄደዉ የኤች አይቪ ምርመራ በተሐዋሲዉ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ ከፍ ማለቱን አሳይቷል። የአዉሮጳ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ያወጡት መረጃ፤ በተጠቀሰዉ ጊዜ በ53 የአዉሮጳ ሃገራት 160 ሺህ ሰዎች አዲስ በተሐዋሲዉ መያዛቸዉን ያሳይቷል። ከተጠቀሰዉ ቁጥር 80 በመቶዉ የምሥራቅ አዉሮጳ ነዉ።

በኢትዮጵያ የፌደራል ኤችአይቪ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት የዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስተባበር ዳይሬክተር ለአቶ ክፍሌ ምትኩ የኤች አይቪ ተሐዋሲ ከአፍሪቃ ይልቅ በኤኮኖሚ አቅማቸዉ የተሻሉ በሚባሉት የአዉሮጳ ሃገራት ተባብሷል የሚለዉ መረጃ ጥያቄ የሚያስነሳ አይነት ነዉ።  እሳቸዉ የሚሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኤች አይቪን ለመከላከል የነበረዉ ትኩረት መቀዛቀዙ በተለይ አቅም የሌላት አፍሪቃን ይበልጥ ተጎጂ ማድረጉ አይቀርም ነዉ።  

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሕዝቡን የጤና ይዞታ የሚያሳየዉ ቅኝት ዉጤት ያለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመትን የሚመለከተዉ ማለት በቅርቡ ይፋ ቢደረግም የኤች አይቪ ምርመራ ዉጤትን የሚመለከተዉ ግን ገና እንዳልወጣ ነዉ ከአቶ ክፍሌ ለመረዳት የቻልነዉ። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ የኤችአይቪ ተሐዋሲ ስርጭት እየቀነሰ መታየቱ እዉነት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ክፍሌ፤ ከመዘናጋት ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች ዛሬም ስጋቱ መኖሩን ግን አፅንኦት ይሰጣሉ። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኤች አይቪ ተሐዋሲ በደማቸዉ ዉስጥ የሚገኝ ወገኖች ቁጥር አንድ ሚሊየን እንደማይሞላ ነዉ የሚነገረዉ። እንዲያም ሆኖ ወጣቶች ለተሐዋሲዉ የተጋለጡ እንደሆኑ ተመልክቷል።

በነገራችን ላይ UNAIDS የዓለም የኤድስ ቀን መታሰቢ ኅዳር 22 ከመድረሱ አስቀድሞ «ጤና፤ መብቴ» የሚል መሪ ቃል የያዘ ዘመቻ ጀምሯል። ዘመቻዉ ሰዎች ጤናቸዉን ለመጠበቅ የሚያስችሏቸዉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸዉንም ሆነ ያንን ለማሳካት የሚገጥሟቸዉን እንቅፋቶች በቅርበት ይቃኛል። የተመድ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2030ዓ,ም አሳካዋለሁ ብሎ ያቀዳቸዉ ግቦች ሁሉ የሚያያዙት ከጤና ጋር መሆኑን በማስታወስም፤ ሰዎች ጤናቸዉ እንዲጠበቅ የሚያስፈልጓቸዉ ሁሉ የሚመቻችበት አጋጣሚ ሁሉ በተቻለ መጠን መሟላት እንደሚገባቸዉም ኅብረተሰቡ እንዲያዉቅ ማድረግም እንደሚሻ ነዉ ያመለከተዉ።  

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic