የኤቦላ ተሕዋሲ ሥርጭትና ሥጋቱ | ዓለም | DW | 05.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኤቦላ ተሕዋሲ ሥርጭትና ሥጋቱ

የኤቦላ ተሕዋሲ ሥርጭትን ለመግታትም ሆነ ለበሽታ የተጋለጡ ሠዎችን ለመርዳት መንግሥታት ተገቢዉን ጥረት አለማድረጋቸዉን ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች አጋለጡ።ድንበር የለሽ ሐኪሞች፤ የአለም ጤና ድርጅትና ሌሎች ድርጅቶች በየፊናቸዉ እንዳሉት የኤቦላን «አደጋ» ለማስወገድ ከተገባዉ ቃል አብዛኛዉ ገቢር አልሆነም።

በመንግሥታት ላይ ያነጣጠረዉ ወቀሳና ትችት ከተደጋጋመ በሕዋላ የቀፍሪቃ መሪዎች ሥለ ጉዳዩ ለመነጋገር ለመጪዉ ሰኞ ቀጠሮ ይዘዋል።ኤቦላ ካለፈዉ መጋቢት ወዲሕ ከአንድ ሺሕ ዘጠኝ መቶ በላይ ሰዎች ገድሏል።

ጀርመናዊዉ የሕፃናት ሐኪም ቬርነር ሽትራል «ካፕ አናሙር» የሚባለዉ ግብረ-ሠናይ ድርጅት በሚያስተዳድረዉ የሴራሊዮን ብቸኛ የሕጻናት ሆስፒታል መሥራት ከጀመሩ ገና ሁለት ሳምንታቸዉ ነዉ።ከ «እጥረት« ጋር ከተዋወቁም-እንዲሁ።ሥለ ኤቦላ ሲናገሩ ግን «እጥረት» የምትለዋን ቃል የወደዷት ያክል ይደጋግሟታል።

«ሆስፒታሉ በሀገሪቱ ዉስጥ ያለ ብቸኛ የሕጻናት ሐኪም ቤት ነዉ።ቤተ-ሙከራዉ ያለዉ ግን ከሆስፒታሉ በመኪና የሥድስት ሠዓት መንገድ እሚያጉዝ ሥፍራ ነዉ።በኤቦላ ተሕዋስ የሚጠረጠሩ በሽተኞች ደም ለምርመራ ተልኮ ዉጤቱ ለሐኪም ቤቱ እስኪደርስ ሰወስት ቀን ይፈጃል።»

አንዴ ይላሉ ሐኪሙ «ትኩሳቷ የናረ አንዲት ሕፃን ሆስፒታል ደረሰች።» እንደተለመደዉ የደም ናሙናዉ ቤተ-ሙከራ (ላቦላቶሪ) ተልኮ ዉጤቱ እስኪመጣ «ከሁለት ሐኪሞች በስተቀር የሚጠጋት አልነበረም።» ቀጠሉ ሐኪሙ፤ ምክንያቱም ለመላዉ «የሆስፒታሉ ሐኪሞችና ረዳቶቻቸዉ ያለዉ የመከላከያ ልብስ፤ጫማ፤መነፅርና ጓንት ሁለት ብቻ ነበርና።»

የቁሳቁሱ እጥረት ለሩቁ ታዛቢ ቀላል ይመስላል። ጀርመናዊዉ ሐኪም እንዳዩት ግን «ሕይወት እያስገበረ ነዉ።» ተሕዋሲዉ ሰዉ መልከፍ፤መግደል ከጀረበት ካለፈዉ መጋቢት ጀምሮ ብዙ ተወራ እንጂ የተደረገዉ ትንሽ ነዉ።

«ብዙ የተደረገ ነገር የለም።እኛ ብቻ ሳንሆን ድንበር የለሽ ሐኪሞች እና ሌሎች ድርጅቶችም ካለፈዉ ሚያዚያና ግንቦት ጀምሮ ድጋፍ እንዲደረግ በተደጋጋሚ እየጠየቁ ነዉ።የመከላከያ ቁሳቁሶች መዳረስ አለበት።ሕዝብን ማስረዳት አስፈላጊ ነዉ።»

ሥለ ኤቦላ ተሕዋሲ አደገኝነት መነገሩ፤ ሰዉ እንዲጠነቀቅ መመከር፤መታወጁ አልቀረም።ይሁንና ምክር፤ አዋጅ መገለጫዉ ሰዉን ከማስፈራራት በስተቀር የርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት የሥርጭቱ ሥፋት፤ የሟች በሽተኛዉ ቁጥርም አልቀነሰም።

ጀርመናዊዉi ሐኪም ዛሬም «እጥረት» የሚሉት ቁሳቁስና መድሐኒትን ለመስጠት ከወራት በፊት ቃል የገቡ በርካታ መንግሥታት ነበሩ። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ቃል አቀባይ ታሪክ ጃሳሬቪች እንደሚሉት ቃሉ ግን እስካሁን ሙሉ በሙሉ ገቢር አልሆነም።

«አሁንም መጠየቃችንን እንቀጥላለን።አሁንም የሚገቡ የርዳታ ቃሎች አሉ።ይሁንና ቃሉ ገቢር መሆን አለበት።የበሽታዉን ሥርጭት ለመከላከል ቁሳቁሶችና ለጤና ሠራተኞች ክፍያ የሚዉለዉ ርዳታ መቀጠል አለበት።»

የአፍሪቃ መሪዎች በሽታዉ አምስት የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራትን ካዳረሰ፤ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክም በበሽታዉ ከሠላሳ በላይ ዜጎችዋን መቅበሯ ከተረጋገጠ በኋላ ገና ስለበሽታዉ ሊነጋገሩ ለሰኞ ቀጠሮ ይዘዋል።የሕብረቱ ሥራ-አስፈፃሚ እንዳስታወቀዉ አዲስ አበባ የሚሰየመዉ ጉባኤ ኤቦላን በክፍለ-ዓለሚቱ ደረጃ በጋራ መከላከል የሚችልበትን ሥልት ይቀይሳል።

በድርንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ሐላፊ በዡዋን ሊዩ እገላለፅ ግን «እሳቱን ለማጥፋት ወደሚነደዉ ሕንፃ ጠጋ ብሎ ዉሐ መርጨት እንጂ ስብሰባ፤ዉይይት፤መግለጫዉ ያሁኑን አደጋ ለማስወገድ የሚፈይደዉ የለም።

«መግለጫ ማዉጣት፤የጉዞ ካርታ መንደፍ፤ክትባትና መድሐኒት መፈለግ ጥሩ ነዉ።ዛሬ ግን እነዚሕ ሁሉ የበሽታዉን ሥርጭት አያቆሙትም።ሥርጭቱን ለመግታት መንግሥታት የሲቢልና የጦር እሴቶቻቸዉንና ባለሙያዎቻቸዉን ባስቸኳይ በመከላከሉ ላይ ሊያዉሏቸዉ ይገባል።ይሕን እሳት ለማጥፋት ወደሚጋየዉ ሕንፃ መሮጥ አለብን።»

ኤቦላ እስካሁን ከ1900 በላይ ሰዎች ገድሏል።ከሰወስት ሺሕ በላይ ለክፏል።የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራትን ማሕበረ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እያሽመደመደ ነዉ።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic