የኤቦላ ስጋትና የጥንቃቄዉ ዘመቻ | ጤና እና አካባቢ | DW | 01.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የኤቦላ ስጋትና የጥንቃቄዉ ዘመቻ

ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ የኤቦላ ተሕዋሲ የገደላቸዉ ሰዎች ቁጥር ከሰባት መቶ ልቋል። በተጠቀሰዉ አካባቢ በተሕዋሲዉ ክፉኛ የተጎዱት ሃገራት የኤቦላ ወረርሽኝን ለመቋቋም ጠንካራና አዲስ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል።

የጊኒ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን እና አይቮሪኮስት መሪዎች ዛሬ በጊኒ ዋና ከተማ ኮናክሪ ላይ ከዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ኃላፊ ማርግሬት ቻን ጋ በመሆን ተሕዋሲዉን ለመዋጋት የሚያስችል የጋራ እቅድ ይፋ ያደርጋሉ። የዓለም የጤና ድርጅት እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ 100 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

ባለፈዉ የካቲት ወር ነዉ በጊኒ ገጠራማ ቀበሌዎች የመጀመሪያዉ የኤቦላ ተሕዋሲ ምልክት የታየዉ። ወራት ቆይቶ ደግሞ እንደሰደድ እሳት ወደሌላ ከተሞች ብቻ ሳይሆን ወደጎረቤት ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን፤ ከራርሞ ወደናይጄሪያ ተዛመተ። እስከትናንት በተጠቀሱት ሃገራት በኤቦላ ሕይወታቸዉን ያጡት 729 መድረሳቸዉን የዓለም የጤና ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ WHO አረጋግጧል። 1,323 ደግሞ በተሕዋሲዉ መያዛቸዉ ይገመታል። ኤቦላ በታሪኩ እንዲህ በአጭር ጊዜ በርካታ አካባቢዎችን ሲያዳርስ እና ከፍተኛ ጉዳትንም ሲያደርስ የመጀመሪያዉ ነዉ ተብሏል። የሰዎች ከቦታ ወደቦታ የመንቀሳቀስ ልማድና ምክንያት እያደር በመጨመሩም የተሕዋሲዉ ስጋት ወረርሽኙ በተቀሰቀሰበት አካባቢ ብቻ የሚገታ አልሆነም።

ረሃብ፣ ጦርነት እንዲሁም ሌሎች በሽታዎች የሚቀጥፉት ሰዉ ሳያንስ አሁን ስሙ የገነነዉ ይህ ተሕዋሲ ደግሞ የሚጥለዉ ግዳይ እንዳይበረክት ርብርቦሹ በአፍሪቃ ብቻ አልተገደበም። ፊት አዉራሪዉ WHO ቢሆንም የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ፣ ECOWAS፣ የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እንዲሁም የአዉሮጳ ኮሚሽን የገንዘብና የባለሙያዎች ድጋፍ እያደረጉ ነዉ። በምዕራብ አፍሪቃ በኤቦላ ክፉኛ ከተጎዱት የጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን እንዲሁም አይቮሪኮስት መሪዎች ጋር በመሆን የተሕዋሲዉን ወረርሽኝ ለመግታት የተዘጋጀዉን እቅድ ይፋ የሚያደርገዉ የዓለም የጤና ድርጅት ለዚሁ ተግባር የሚያስፈልገዉን የገንዘብ መጠን ከወዲሁ አሳዉቋል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ፓዉል ጋርዉድ፤

«ለወረርሽኙ ምላሽ ለመስጠት ለተዘጋጀዉ እቅድ ወደ100 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። እቅዱ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገዉን ዘመቻ የሚያግዙ የህክምና ባለሙያዎችን ዓይነትና ብዛትም ለይቷል። ይህም ዶክተሮችን፣ ነርሶችን፣ አገልግሎት አቅራቢዎችን፣ ወረርሽኝ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች፣ የመረጃ ልዉዉጥ ባለሙያዎች እንዲሁም ከማኅበረሰቡ አባላት ጋ እንዲነጋገሩ እና ስለጤና አገልግሎቱ መልዕክቶችን በማዳረስ በተቻለ መጠን ህክምናዉን አስቀድመዉ ማግኘታቸዉን ማረጋገጥ እንዲቻል ኅብረተሰቡን በማነቃቃት የተካኑ ባለሙያዎችን ሁሉ ያካትታል።»

እስካሁን በርካታ ሰዎችን ኤቦላ የፈጀዉ ጊኒ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን ነዉ። ናይጀሪያ ዉስጥ ህይወቱ ያለፈዉ አንድ ሰዉ ሲሆን እሱም የላይቤሪያ ዜጋ ነዉ። ናይጀሪያ ይህን ሰዉ በቅርበት ያስታመሙ ሁለት ዜጎቿን ገለል አድርጋ በተሕዋሲዉ መያዝ አለመያዛቸዉን በማጥናት ላይ ናት። ሌሎች 69 በተመሳሳይ የተጠረጠሩ ሰዎችም ተገልለዉ ክትትል እየተደረገ ነዉ። አሜሪካም ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ ይሠራ የነበረ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ የነበረና በገዳዩ ኤቦላ ተሕዋሲ የተያዘ ዜጋዋ ወደአትላንታ ኢሞሪ ዩኒቨርሲቲ ሃኪም ቤት ተወስዶ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲታከም እንደምታደርግ አመልክታለች። ሴራሊዮን በተሕዋሲዉ ከተጎዱት ሃገራት አንዷ በመሆኗ በአሁኑ ወቅት ኤቦላ እንዳይዛመት የበኩሏን ጥንቃቄ እያደረገች ሲሆን በተሕዋሲዉ የተያዙ ወገኖችን ሲያክሙ የነበሩ በዚሁ ሰበብ ህይወታቸዉ ዶክተሯንም ሃዘን እያስተናገደች ነዉ። በስፍራዉ የዶቼ ቬለዉ አቡበከር ጃሎ የዶክተሩ ሞት ያስከተለዉን ስሜት እንዲህ ያስረዳል፤

«ይህ ማለት በርካታ ሰዎች ፍርሃት ገብቷቸዋል፤ በዚያ ላይ ተሕዋሲዉ ወደተስፋፋበት የሴራሊዮን ግዛት ደፍሮ ለመሄድ ፈቃደኛ የሆነ ዶክተር እንዳይኖር አድርጓል፤ አሁን ተህዋሲዉን የመዋጋቱ ኃላፊነት እንደድንበር የለሽ ሃኪሞች፤ የዓለም የጤና ድርጅትና ቀይ መስቀል ባሉ የዓለም ዓቀፍ የጤና እና የእርዳታ ድርጅቶች ትከሻ ላይ ወድቋል።»

ላይቤሪያ የዛሬዉን ቀን የኤቦላን ተሕዋሲ ከአንዱ ወደሌላዉ እንዳይዛመት መከላከል የሚያስችል የመድሃኒት መርጫ ቀን እንዲሆን በብሄራዊ ደረጃ ኣዉጃለች። እጅግ ተፈላጊ ያልሆኑ የመንግስት ሠራተኞችም ቢያንስ ለ30 ቀናት ከስራ ገበታዉ በእረፍት ስም እንዲገለሉ የማድረግ ርምጃ ወስዳለች። ተገልጿል። የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ AMISOM ከሴራሊዮን ሊካሄድ የነበረዉን የወታደሮች ለዉጥ ለጊዜዉ መሰረዙን አስታዉቋል። የAMISOM ቃል አቀባይ ኮሎኔል አሊ አደን ሁመድ ለዘጋቢዎች እንደገለጹት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮዉ የኤቦላ ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል ከሴራሊዮን ሊመጡለት የነበሩት ወታደሮች ለጊዜዉ እንዳይመጡ ማድረጉን አመልክተዋል።

ኤቦላ ከባድ የሆነ የጡንቻ ህመም፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ የራስ ምታትና እጅግ ከጠናም የማይቋረጥ የደም መፍሰስ የሚያስከትል ተሕዋሲ ነዉ። በኤቦላ ተሕዋሲ ከተያዘ ሰዉ አካል የሚወጡ ማንኛዉም ዓይነት ፈሳሾችን በመንካት እንጂ በአየር የማይተላለፍ ቢሆንም በሚገባ በሳሙናና ሙቅ ዉሃ መታጠብ ተሕዋሲዉን ሊገድለዉ እንደሚችል ይነገራል። በተሕዋሲዉ ከተያዘ ግለሰብ ጋ የቅርብ ግንኙነትና መነካካት ለበሽታዉ የመጋለጥ አጋጣሚን ከፍ እንደሚያደርገዉየጤና ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic