የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይና ጠቅላይ ሚንሥትሩ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 26.03.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይና ጠቅላይ ሚንሥትሩ

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የኤርትራ ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ መገኘታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መናገራቸው እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ስለ ትግራይ ሰብአዊ ኹኔታ ያወጣው ቀዳሚ ዘገባ ዋነኛ መነጋገያ ሆኖ ቆይቷል። የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር የትግራይ ክልልን በተመለከተ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውም አነጋግሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:15

ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማማች

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትግራይ ክልል ውስጥ ደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በሲቪሎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ያቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርት የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኗል። ኢሰመኮ፦ «ትግራይ ክልል፤ በአክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በአጠቃላይ በክልሉ የተሟላ ምርመራ የማድረግን አስፈላጊነት ያመለክታል» ብሏል። 

ራስ መኳንንት የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ «ኢሰመኮ አሁን ኢሰመኮ መሰለ» ሲሉ ፌስቡክ ላይ በአጭሩ ጽፈዋል። የኢሰመኮ ቀዳሚ ዘገባ የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ክልል ውስጥ አደረሷቸው የተባሉትን «መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት» ሆን ተብለው የተደረጉ ናቸው ብሏል። በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና መርኆች የተቀመጡ ደንቦችን የሚጥስ ተግባር መሆኑንም ጠቅሷል። 

በ13 ገጾች የተካተተው የኢሰመኮ የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ዘገባ «ጾታዊ ጥቃትን እና ሁሉንም አይነት ጉዳቶች የማያጠቃልል» መሆኑም ተገልጧል። በዚህ የኢሰመኮ ቀዳሚ ዘገባ በርካታ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። ኢሰመኮ በድፍረት መረጃዎችን ማውጣቱን የሚያወድሱ፣ የለም ዋናውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመሸፈን ሲባል ነው የሚሉ እንዲሁም እስከዛሬ የት ነበራችሁ ሲሉ የሚወቅሱ አስተያየት ሰጪዎችም ነበሩ። 

ፍሬው ዳምጠው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «በጣም በጣም አሳዛኝ ድርጊት ነው። ንጹሁ ሕዝብ ምን አደረገ ተብሎ ነው የሚግደለው? ሴቶቹስ ምን ባደረጉ ይደፈራሉ?» ሲሉ ወደ ፈጣሪ አማረው ጽፈዋል።  

 ፋይሰል ፋይሰል የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፦ «ከጦርነት ምን ትርፍ ይገኛል የዚህን ድህነት የተጫነውን ህዝብ ስቃይ ከማስረዘም በስተቀር» ብለው ጽፈዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈጸሙ የተባሉ የመብት ጥሰቶችን ከአፍሪቃ የሕዝቦች እና የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ACHPR)ጋር በመተባበር ለመመርመር ዝግጁነቱን ገልጧል።  ይህን በመደገፍም በመቃወምም የተለያዩ ሰዎች ጽፈዋል።  

የትግራይ ችግርን በተመለከተ፦ «አፍሪቃዊ መፍትኄ የለም» ሲሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትዊተር ገጻቸው ላይ የጻፉት ማርቲን ፕላውት የተባሉ ሰው ናቸው። እኚህ ሰው በተለይ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መንግሥትን በከፍተኛ ኹኔታ በመቃወም ይታወቃሉ። ትዊተር ገጻቸው ላይ ያያዙት የድረ ገጽ ማገናኛ ሲከፈት እውስጡ ዊሊያም ዳቪሰን በሚባሉ ሰው በሚዘጋጅ ድረ ገጽ ላይ በዮናስ አረጋዊ የተጻፈ ጽሑፍ ሰፍሮበታል።  

በርካቶች ዊሊያም ዳቪሰን ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት መልካም አመለካከት የላቸውም ቀውስ እንዲከሰትም ደጋግመው ይጽፋሉ ሲሉ ይተቻሉ።  በእንግሊዛዊው ዊሊያም ዳቪሰን በተቋቋመው ድረ ገጽ የወጣው ጽሑፍ፦«ለኢትዮጵያ ትግራይ ችግር አፍሪቃዊ መፍትኄ የለም» ይላል ርእሱ። ማርቲን ፕላውት የትዊተር ጽሑፋቸውን ከዚህ የድረ ገጽ ጽሑፍ ቆንጥረው ነው ያሰፈሩት። በርካቶች እንግሊዛዊው ማርቲን ፕላውት በኢትዮጵያ እና አፍሪቃ ጉዳይ ረዥም እጃቸውን መዘርጋታቸውን ያቁሙ ሲሉ ኮንነዋል። ጽሑፋቸውንም ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ጋር አያይዘውታል። 

«ይኽ አይነት አመለካከት የመጣው ዘረኛ ከሆነው አምእምሮህ ነው። እኛ አፍሪቃውያን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቀርቶ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ የአፍሪቃ ችግሮችን አፍሪቃዊ መፍትኄዎችን ስናቀርብ ቆይተናል» ሲሉ ትዊተር ገጻቸው ላይ የጻፉት ወንድይራድ የተባሉ ሰው ናቸው። «የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ሠርቶ ዐያውቅም» ሲሉም የዛሬ 125 ዓመት ለመላው አፍሪቃውያን ኩራት እና መነቃቃት የሆነውን የአድዋ ድል ማርቲን ፕላውትን አስታውሰዋል። 

ዘ ፒስ ሜከር በሚል የትዊተር ስም የጻፉ ግለሰብ ደግሞ፦ «አሁን የነጭ እና ጥቁር ሕዝቦች ካርድ መጫወት ጀመርክ» ሲሉ ማርቲን ፕላውት ትዊተር ገጻቸው ላይ ያያዙት የኤርትራ ስም ያለበት ድረገጽ የራሳቸው የማርቲን መሆኑን ጽፈዋል። «ያ የራስህ ድረገጽ ነው። የአስተሳሰብ ልካችንን አትዝለፍ» ሲሉም ተችተዋል። ሚካኤል አብደታ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ ቀጣዩን ጽፈዋል። «ሕወሓት ከአፍሪቃውያን ይልቅ ከአሜሪካውያን እና አውሮጳውያን ጋር ጠንካራ ትብብር ስለነበረው ነው ከእነሱ መፍትኄ እንዲመጣ የምትጠብቀው።» ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፦ «እና ምን ይጠበስ?» ሲሉ ይንደረደራሉ። «ጣልቃ ለመግባት አንዳች ቀዳዳ አስፈለገህ?» ሲሉ ጠይቀው ራሳቸው በአጭሩ ይመልሳሉ፦ «በፍጹም!» ሲሉ። ቀጠል አድርገውም፦ «ጠቅላይ ሚንሥትሩ እጆቻችንን ማንም አይጠመዝዘንም ሲሉ ነግረውኻል» የሚል ጽሑፍ አስፍረዋል። ጸሐፊውሞ ሞሼ ዳያን ይባላሉ፤ መልእክቱ ትዊተር ገጻቸው ላይ ይገኛል። 

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በጋራ ሊሠሩ ነው። ሁለቱ ተቋማት ትግራይ ውስጥ ተፈጽሟል የሚባለውን የመብት ጥሰትና እንግልት በጋራ ለመመርመር መስማማታቸውን ትናንት ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል። 

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ባደረጉት ንግግር፦ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያ ድንበርን አልፈው መግባታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ አረጋግጠዋል። በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን ገልጠውም እንደሚጣራ ዐሳውቀዋል።

«አይዞህ በርታ ፅና የኢትዮጵያ አምላክም እኛም ኢትዮጵያውያንም ከአንተ ጋር ነን» የሚል አስተያየት ለጠቅላይ ሚንስትሩ የላኩት ግርማ ኪንግ ግርማ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ናቸው። ረዘነ ገብረመስቀል የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «እንደዚህ ሰውዬ ውሸት የምደወ ሰወ የለም» ሲሉ ጽፈዋል። በአጭሩ፦ «ቻዎ ሉዓላዊነት» ያሉት ብርኃኑ ዓለሙ ናቸው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ትናንት ከቀትር በኋላ አስመራ መግባታቸው ተገልጧል። የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ባሰራጩት መልእክት የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርዊ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና አብሯቸው ለተጓዘው የልዑካን ቡድን አስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ደማቅ አቀባበል አድርገዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፦ «ኤርትራ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነች» ያሉት ደግሞ ሱሌይማን ብሩ ፈይሳ ናቸው። ሉዋም የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «እግዚአብሔር ለንፁሃን ደም ይፍረድ» ሲሉ ሐና ሰዒድ ደግሞ፦ «በርቱ እና እዚያ አካባቢ ሰላም አስፍኑ» በሚል ፌስቡክ ላይ ጽፈዋል። 

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኤርትራ መንግሥት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት መስማማቱን ዐስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ ዛሬ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳሉት ኤርትራ ጦሯን ለማስወጣት የተስማማችው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አስመራ ውስጥ መጋቢት 17ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት ውይይት ነው። 

የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር ክሪስ ኩንስ የትግራይ ክልልን በተመለከተ ኢትዮጵያን በመጎብኘታቸው በርካታ አስተያየቶችን ተሰጥተዋል። ሴናተሩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የቅርብ ሰው ከመሆናቸው አንጻር ወደ ኢትዮጵያ ሊጓዙ ሲነሱ በርካቶች የየራሳቸውን መላምት እና ግምት አኑረዋል። በኢትዮፕያ እና ኤርትራ መንግሥታት ላይ ጫና በማሳደር ማዕቀብ ሊጥሉ ነው፤ ከሕወሃት ጋር መንግሥት እንዲደራደር ሊያደርጉ ነው፣ የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል። 

አቤል አቤል ፌስቡክ ላይ በሰጠው አስተያየት፦ «መጀመሪያ ያፈራረሳቹኋቸውን ሀገሮች አስተካክሉ መዥገሮች» ብለዋል።  «እነዚህ ሰዎች ግን ማያሳስባቸው ነገር ምንድን ነው?» ሲሉ የጠየቁት ደግሞ ከድሮ ማን ናቸው ፌስቡክ ላይ። ደስታ ሁሪሶ ደግሞ፦ «ህወሃት መሞቱን አልሰማንም እያላችሁ እንዳይሆን» ሲሉ ተሳልቀዋል። 

ሌላው በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በርካቶች አስተያየት የሰጡበት ጉዳይ በሰሜን ሸዋ የንጹሃን ሰዎች መገደላቸው ነው። አስተያየቶቹ ግን አብዛኞቹ ያልተረጋገጡ፤ ጽንፍ የረገጡ የፖለቲካ አመለካከቶች እና ቅራኔዎች በማስተጋባታቸው ለሳምንታዊ ዝግጅታችን ለማካተት አልቻልንም።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic