የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ጠፉ | ኢትዮጵያ | DW | 15.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ጠፉ

"---ሌሎቹ ቅዳሜ ማታ ወደ ሐገራቸዉ ሲመለሱ ተጨዋቾቹ ለመቅረት መወሰናቸዉ ለሴካፋ-በጣም አሳዛኝ ነዉ።ለኤርትራ እግር ኳስ ለኤርትራ መንግሥትም ጭምር በጣም አሳዛኝ ነዉ።»

default

15 12 09

አስራ ሁለት የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ናይሮቢ-ኬንያ ዉስጥ ጠፉ።ተጨዋቾቹ እዚያዉ ናይሮቢ ኬንያ ዉስጥ በተደረገዉ በምሥራቅና የማዕከላዊ አፍሪቃ ሐገራት የእግር ኳስ ማሕበር (CECAF) ባዘጋጀዉ ግጥሚያ ላይ ሐገራቸዉን ወክለዉ የተጫወቱ ነበር።ተጨዋቾቹ ናይሮቢ መቅረታቸዉ እንጂ ያሉበት ትክክለኛ ሥፍራ እስካሁን አልታወቀም።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝሩን አጠናቅሮታል።

አስራ-አንድ አባል ሐገራትን የሚያስተናብረዉ የምሥራቅና የማዕከላዊ አፍሪቃ የእግር ኳስ ማሕበር ምክር ቤት-CECAFA በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ አፍሪቃ አካባቢያዊ የእግር ኳስ ማሕበራት ሁሉ አንጋፋዉ ነዉ።ዘንድሮ ናይሮቢ ኬንያ ላይ ያዘጋጀዉ ግጥሚያ ደግሞ የማሕበሩ ዋና ፀሐፊ ኒኮላስ ሙሶንዬ እንደሚሉት በብዙ መስኩ በጣም የተዋጣለት-የኤርትራ ቡድንም በጣም ጥሩ ከሚባሉት ቡድናት አንዱ ነበር።

የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ለአስራ-አንደኛ ጊዜ የዘንድሮዉን ዋንጫ ይዘዉ ካምፓላ ከመግባታቸዉ ጥቂት ቀደም ብሎ-ኤርትራዎቹ የገቡበት ጠፋ።ጠፉ።ዋና ፀሐፊ ኒኮላስ ሙሶንዬ ማታዉኑ ነበር-የሰሙት።

«አስራ-ሁለቱ የኤርትራ እግር ኳስ ተጫዋቾች ወደ አስመራ አለመሔዳቸዉን ቅዳሜ ማታ ነዉ-የሰማሁት።አሁን በምንነጋገርበት መሐል የፖሊስ መግለጫ ደርሶኛል።ሥለዚሕ ከእንግዲሕ ጉዳዩ የፖሊስ ነዉ።»

የዜና ወኪሎች እንደዘገቡት አስራ-ሁለቱን ተጫዋቾች አስከትለዉ ናይሮቢ ገብተዉ የነበሩት አሰልጣኝና ጥቂት የኤርትራ እግር ኳስ ፌደሬሽን አባላት-ብቻቸዉ ወደ ሐገራቸዉ መመለስ ግድ ነዉ-የሆነባቸዉ።ዛሬ ሥለ ጉዳዩ የብሔራዊ ቡድኑን አሰልጣኝ ለማነጋገር ሞክረን ግን ከናይሮቢ አልተመልሱም ነዉ የተባልነዉ።

የኤርትራ ኤምባሲና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነዉም ሙከራ አልተሳካልንም።የCECAFA ዋና ፀሐፊ የተጨዋቾቹን መጥፋት ለሁሉም አሳዛኝ ይሉታል።

«በጣም አሳዛኝ ነዉ።እኔና የኤርትራ እግር ኳስ ፌደሬሽን በቅርብ ተባብረን እየሰራን ነበር። እንዲያዉም የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ኬንያ ላይ በተደረገዉ የCECAFA ግጥሚያ እንዲካፈል የፌደሬሽኑን ፕሬዝዳት ያግባባኋቸዉ እኔ ነበርኩ።ተጫዋቾቹን ናይሮቢ ለማምጣት የተቻላቸዉን ሁሉ አድርገዋል።በጣም የሚያስመሰግን ጥረት ነበር።ሌሎቹ ቅዳሜ ማታ ወደ ሐገራቸዉ ሲመለሱ ተጨዋቾቹ ለመቅረት መወሰናቸዉ ለሴካፋ-በጣም አሳዛኝ ነዉ።ለኤርትራ እግር ኳስ ለኤርትራ መንግሥትም ጭምር በጣም አሳዛኝ ነዉ።»

የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በወጡበት ሲቀሩ ግን ያሁኑ የመጀመሪያዉ አይደለም።ከዚሕ ቀደምም ብዙ ተጨዋቾች በተለያዩ ሐገራት ቀርተዋል።እዚያዉ ኬንያ እንኳን እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጣር በሁለት ሺሕ ስድስት አራት የቀይ ባሕር ክለብ ተጫዋያ ጠፍተዋል።

አሁን የጠፉትን ተጨዋቾች ለማግኘት የኬንያ ፖሊስ እያሰሰ ነዉ።በናይሮቢ የኪሲዋሒል ክፍል ባልደረባችን አልፍሬድ-ኪቲ እንደሚለዉ ተጫዋቾቹ ዘመድ-አዝማድ ቤት ሳይሸሽጉ አልቀሩም።

«ሥማቸዉ እንዲጠቀስ የማይፈልጉ ምንጮች እንደነገሩን የጠፉት ተጫዋቾች በየተመዶቻቸዉ ቤት ተደብቀዋል።ናይሮቢ ዉስጥ ናቸዉ ተብሎ ይታመናል።ምክንያቱም ከመጥፋታቸዉ ጥቂት ቀደም ብሎ እዚያዉ ናይሮቢ ሆቴላቸዉ ዉስጥ ነበሩ።»

ፖሊስ ሥለ ጠፉት ተጫዋጮች እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለም።አልፍሬድ ኪቲ እንደሚለዉ ተጫዋቾቹን ፖሊስ ካገኛቸዉ ግን ወደ ሐገራቸዉ ይመልሳቸዋል።
«ፖሊስ እነዚሕን የጠፉትን ተጫዋቾች ለመያዝ አሁን እያሰሰ ነዉ።ከተገኙ ወደ ሐገራቸዉ ነዉ-የሚላኩት።በርግጥ ወደ ሐገራቸዉ መላካቸዉ አይቀርም።»

ኤርትራ በተለያየ አቅጣጫ በርካታ ሕዝብ የሚሰደድባት ሐገር ናት።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደዘገበዉ ባለፈዉ የአዉሮጳዉያን አመት ብቻ 62 ሺሕ ኤርትራዉያን ዉጪ ሐገር ጥገኝነት አግኝተዋል።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ


Audios and videos on the topic