የኤርትራ መንግሥትና የፕረስ ነፃነት | የጋዜጦች አምድ | DW | 19.09.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የኤርትራ መንግሥትና የፕረስ ነፃነት

የጋዜጠኞቹ መብት ተሟጋች ድርጅት መግለጫ ያን ሳምንት በአፍሪቃ የፕረስ ነፃነት ታሪክ ጨለማዉ ሳምንት ብሎታል።ቫንሴት ከዚያም በላይ ነዉ-ይላሉ።

ቀይ ባሕር ጥግ----

ቀይ ባሕር ጥግ----


የኤርትራ መንግሥት ከአምስት አመት በፊት ያሰራቸዉ የግል ወይም የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ያሉበት ሥፍራና ሁኔታ በዉል እንደማይታወቅ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የተሰኘዉ የጋዜጠኞች መብት ተማጋች ድርጅት አስታወቀ።ድርጅቱ የኤርትራ መንግሥት የግል ጋዜጦችን የዘጋበትንና ጋዜጠኞችን ያሰረበትን አምስተኛ አመት ምክንያት በማድረግ ባወጣዉ መግለጫዉ እንዳለዉ ከበርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር የታሰሩት ጋዜጠኞች ጤንነት አሳሳቢ ነዉ ፣በሕወት መኖር አለመኖራቸዉም በዉል አይታወቅም። የድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የአፍሪቃ ጉዳይ ሐላፊ ሊዮናርድ ቫንሴንትን ነጋሽ መሐመድ በስልክ አነጋግሯቸዋል።

መሥከረም ስምንት-1994 ምን ምን እያደረጉ ነበር---በጥያቄ ይጀምራል የድንበር የለሽ ዘጋቢዎች መግለጫ።ምናልባት ከሳምንት በፊት ከኒዮርኩ የአለም ንግድ ማዕከል ሕንፃዎች እና ከዋሽንግተኑ የፔንታጎን ሕንፃ ጋር የተላተሙት የመንገደኞች አዉሮፕላኖች ሥላደረሱት ጉዳትና መዘዙ ከዘመድ ወዳጅዎ ጋር ገና እየተወያዩ ይሆናል---እያለ መላምታዊ መልሱን ቀጠለ።-መግለጫዉ።ከሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ ጥግ-ከቀይ ባሕሪቱ ዳርቻ ትንሽ ሐገር የሆነዉን ፖለቲካዊ ድራማ ግን አያዉቁት ይሆናል----አከለ።

በዚያች እለት የኤርትራዉ ፕሬዝዳት ኢሳያስ አፈወርቂ-የድንበር የለሽ ዘጋቢዎች መግለጫ እንዳብራራዉ በሐገሪቱ የነበሩ የግል ጋዜጠኞች በሙሉ እንዲዘጉ አዘዙ።በአምሰተኛ ቀኑ የግል ወይም ነፃ ጋዜጠኞችም እየተለቀሙ ታሰሩ።ዘንድሮ አምስት አመቱ።የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት የአፍሪቃ ክፍል ሐላፊ ሊዮናርዶ ቫንሴት እንደሚሉት በመቶ ከሚቆጠሩ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር የታሰሩት አስራ-ሰወስት ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታና ሥፍራ በትክክል አይታወቅም።

«ምንም ማረጋገጪያ የለንም።የታሰሩበትን ሥፍራ በትክክል አናዉቅም።ከታወቁት የኤርትራ ጋዜጠኞች አንዱ ዳቪድ ኢሳቅ የታሰረዉ አስመራ በሚገኘዉ ካሊቲ እስር ቤት ሳይሆን አይቀርም።መስከረም 1994 ከታሰሩት ከተቀሩት ባልደረቦቹ ገሚሶቹ ምናልባት ሰሜን ምሥራቅ ኤርትራ-ኤሪ ኤሮ በሚባለዉ እስር ቤት ሳይሆኑ አይቀሩም።»

ባንሴንት እንደሚሉት እስረኞቹ ከጠበቆች፣ ከቤተሰቦቻቸዉ ወይም ከዉጪዉ አለም ጋር መገናኘት አይፈቀድላቸዉም።በዚሕም ምክንያት ድርጅቱ ከአስመራ በተዘዋዋሪ መንገድ ከሚያገኘዉ መረጃ ዉጪ እስረኞቹ በትክክል ያሉበትን ሥፍራና የአካል ጤናቸዉን ሁኔታ ማረጋገጥ አይችልም።

«ይሕ በጣም ነዉ-ያሚያሳስበን።መስከረም 1994 የታሰሩት ጋዜጠኞች የጤና ሁኔታ አሳሳቢ ነዉ።ምናልባት የተወሰኑት ሞተዉ ይሆናል የሚል ሥጋትም አለን።ከጠበቆች፣ ከቤተሰቦቻቸዉም ሆነ ከዉጪዉ አለም ጋር እንዲገኛኙ አይፈቀድላቸዉም።»

በድንበር የሌሽ ዘጋቢዎች መግለጫ መሠረት የኤርትራ መንግሥት የግል ጋዜጦችን ዘግቶ ጋዜጠኞቹን ያሰረዉ ከመስከረም ስምንት እስከ አስራ-ሰወስት 1994 ባለዉ ጊዜ ነበር።የጋዜጠኞቹ መብት ተሟጋች ድርጅት መግለጫ ያን ሳምንት በአፍሪቃ የፕረስ ነፃነት ታሪክ ጨለማዉ ሳምንት ብሎታል።ቫንሴት ከዚያም በላይ ነዉ-ይላሉ።


«ለአፍሪቃ ብቻ አይደለም።ለመላዉ አለምም ጨለማ ሳምንት ነዉ።ኤርትራ ዉስጥ በተፈፀመዉ ምክንያት ሁኔታዉ በርግጥ ለአሐጉሪቱ የተለየ ነዉ።እንደ አለመታደል ሆኖ ለመላዉ አለም ልዩ አይደለም።ግን በአለም የመረጃ የጨለማ ጉርጓድ የምንለዉ አካል ነዉ።በሰሜን ኮሪያ ወይም በቱርክሜንስታን እንደሚታየዉ አይነት ነዉ።»

የኤርትራ መንግሥት ጋዜጠኞችን እንዲፈታ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ በተለይም ምዕራቡ አለም ግፊት እያደረገ መሆኑን ቫንሴት ጠቅሰዋል።በተለይ ሲዊድን ሲዊድናዊ ዜግነት ያለዉ ጋዜጠኛ ዳቪድ ኢሳቅን ለማስለቀቅ ብዙ መጣሩን አስታዉቀዋል።የአዉሮጳ ሕብረትም በኤርትራ መንግሥት ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳረፍ እየሞከረ መሆኑን ገልጠዋል።ይሁንና የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግፊት እንዲጠናከርና የኤርትራ መንግሥት ለሚደረግበት ግፊት እንዲንበረከክ ለነፃነትና መብት የቆመዉ ሕዝብ በሙሉ ድምፁን ማሰማት አለበት።