የኤርትራውያኑ የተራዘመ ጥበቃ በጀርመን | አፍሪቃ | DW | 20.06.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የኤርትራውያኑ የተራዘመ ጥበቃ በጀርመን

ምንም ያኽል የለውጥ ተስፋ ቢደረግም ኤርትራ አኹንም አምባገነን ተደርጋ ነው የምትወሰደው። እንዲያም ኾኖ ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን ወደ ጀርመን ማምጣት ሲፈልጉ ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት መፍጠር አለባቸው። ለብዙዎች ታዲያ ይኽ እጅግ አስቸጋሪ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:23

ትኩረት በአፍሪቃ

መጀመሪያ አካባቢ ተስፋ ያጭራል መጨረሻው ግን ብዙውን ጊዜ አያምርም። ለነገሩ ጀርመን ውስጥ እውቅና የተሰጣቸው ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን የማስመጣት መብት አላቸው። ከኤርትራ ለመጡ ስደተኞች ግን በተግባር ሲታይ ይኽ አዳጋች ነው። ቤተሰቦቻቸውን ወደ ጀርመን ለማስመጣት 1645 ስደተኞች ማመልከቻዎቻቸውን ኢትዮጵያ፤ ሱዳን እና ኬንያ በሚገኙ የጀርመን ኤምባሲዎች ባለፈው ዓመት አመልክተዋል። ቪዛ ማግኘት ቢገባቸውም ቅሉ ካመልካቾቹ መካከል ቪዛ የተሰጣቸው ለ48 ከመቶው ብቻ  መኾኑን በግራዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ ተጠንቶ ለጀርመን ቡንደስታግ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የቀረበ አንድ ጥናት ይጠቊማል። 

በእርግጥ ይኽ ቊጥር ከኹለት ዓመት በፊት ከነበረው አንጻር ሲታይ የተሻለ ነው። ያኔ ቤተሰባቸውን ለማምጣት አመልክተው ቪዛ የተሰጣቸው ሰዎች ብዛት 38 ከመቶ ነበር። ቪዛውን ያለማግኘታቸው ሰበቡ ግን የአመልካቾቹ አይደለም ይላሉ በጀርመን ቡንደስታግ የግራዎቹ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ኡላ የልፕከ።

«ዋናው ችግር ምንድን ነው፤ በአብያተ ክርስቲያናት ለሚከወኑ ጋብቻዎች እዚህ ጀርመን ውስጥ ማስረጃዎቹ የተጭበረበሩ ሊኾኑ ይችላሉ የሚል ስልታዊ ጥርጣሬ መኖሩ ነው። ዕውቅና የተሰጣቸው ስደተኞች ክትትል በሚደረግባት ኤርትራ ግንኙነት ፈጥረው ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስመዘገቡ መገደዳቸው ነው። ያ በእኔ እይታ ከመጠን ያለፈ ጥያቄ ነው።»

ኤምባሲዎቹ ግን የሚያደርጉት ነገር ትክክል እንደኾነ ነው የሚታያቸው። «ለጀርመን የውጭ  ሃገራት ዲፕሎማቶች የምስክር ወረቀቶቹ ዘርፈ ብዙ በመኾናቸው የተነሳ የኤርትራ የሃይማኖት ምስክር ወረቀቶች ይዘት እና ቅርጻቸው ትክክለኛ ስለመኾናቸው የማረጋገጫ መንገዶች የላቸውም» ይላል የጀርመን ቡንደስታግ ለግራዎቹ ፖለቲከኞች በሰጠው ምላሽ ላይ የሚነበበው። 

ይኽ ማለት፦ ስደተኞችም ኾኑ የትዳር አጋሮቻቸው ጋብቻቸው አጠራጣሪ በሚኾንበት ወቅት ኤርትራ ውስጥ በሚገኙ ባለሥልጣናት ስለጋብቻቸው ትክክለኛነት ማረጋገጫ ማግኘት ይኖርባቸዋል ማለት ነው። በሌላ አንጻር ደግሞ የጀርመን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኤርትራ ውስጥ ያለውን ኹኔታ የሚመለከተው በጎሪጥ ነው። «ዴሞክራሲ እና መሠረተ-ሕግ የመከበሩ ጉዳይ አልተረጋገጠም። የፖለቲካ ስርዓቱ ጨቋኝ ነው። ነጻ ፕሬስ የሚባል ነገር የለም። የሲቪል ማኅበረሰብ ተገልለዋል። የሰብአዊ መብቶች በብርቱ ተደፍልቀዋል» ሲል መልስ ሰጥቷል ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ከዶይቸ ቬለ ለቀረበለት ጥያቄ።

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት የለውጥ ተስፋን አጭሯል

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት የለውጥ ተስፋን አጭሯል

ኤርትራ ከኢትዮጵያ በኩል ሊደርስብኝ የሚችለውን ወታደራዊ ስጋት ለመከላከል በሚል ዜጎቿን ገደብ አልባ በኾነ ወታደራዊ ግዳጅ ስልጠና ማጥመዷ አኹንም እንደቀጠለ መኾኑን ስደተኞቹ በምሬት ይናገራሉ። ወታደራዊ አገልግሎቱ ለበርካታ ዓመታት ከመዝለቊም ባሻገር አገልግሎት ሰጪዎች የግዳጅ ሥራዎች ላይ እንዲጠመዱ እና አካላዊ ጉዳቶችንም እንዲያስተናግዱ ይገደዳሉ ሲሉም ያክላሉ። ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ በሚገኘው ጊጋ በተሰኘው ተቋም (GIGA-Institut) የኤርትራ ጉዳይ ጠበብቷ ኒኮል ሒርት ኹሉም የኤርትራ ተወላጆች በአኹኑ ወቅትም ያለገደብ ወታደራዊ አገልግሎት በግዳጅ እየሰጡ ነው ይላሉ።

«በአኹኑ ወቅት ከኢትዮጵያ በኩል ወታደራዊ ስጋት ስለሌለ ገደብ አልባ ብሔራዊ ግዳጅ ለውጥ እንዲደረግበት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። ያግ ግን ተግባራዊ አልኾነም። ኹሉም የኤርትራ ተወላጆች አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ ያለገደብ ይኽን አገልግሎት መስጠት አለባቸው። የፖለቲካ ለውጥ አልተከናወነም። የፖለቲካ እስረኞችም አልተፈቱም።»

የኤርትራ ባለሥልጣናት መሰል ገለጣዎችን በጥብቅ ነው ውድቅ የሚያደርጉት። ቊጥሮች ግን በራሳቸው የሚገልጡት ነገር አለ። ሰዎች በገፍ መፍለሳቸው አልተቋረጠም። ባለፈው የጎርጎሪዮስ ዓመት በየወሩ 6000 ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረዋል። በውጭ ሃገራትም ቢኾን ኤርትርራውያን በሀገራቸው ባለሥልጣናት ጫና እንደሚያርፍባቸው ስለኤርትራ የሚያውቊ ተንታኞች ይናገራሉ። የኤርትራ ጉዳይ ጠበብቷ ኒኮል ሒርት በዚህም ጉዳይ ላይ የሚሉት አላቸው። 

«ጀርመን ውስጥ አንድ ሰው አንድ የኾነ ወረቀት ለመውሰድ ወደ ኤንባሲ ቢኼድ ያ ሰው አካላዊ ጥቃት አይደርስበትም።  ግን ደግሞ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ዘመዶቹ ላይ ጫናው ሊያርፍ ይችላል፤ ወይንም ያ ሰው የጀርመን ባለስልጣናት የጠየቊትን አገልግሎት ለማግኘት ለኤምባሲ ባለስልጣናቱ ያለፍላጎቱ የውጭ ሀገር ነዋሪዎች የሚከፍሉትን ግብር መክፈል ይኖርበታል።»

ከኤርትራ የመጡ በርካታ ስደተኞች ጀርመን ውስጥ ይኖራሉ

ከኤርትራ የመጡ በርካታ ስደተኞች ጀርመን ውስጥ ይኖራሉ

እንደ ኤርትራ መንግስት ከኾነ በውጭ ሃገራት ነዋሪ የኾኑ ኤርትራውያን በአጠቃላይ ከገቢያቸው ኹለት ከመቶ መክፈል ይኖርባቸዋል።  ከዶይቸ ቬለ ጥያቄ የቀረበለት የኤርትራ ኤምባሲ ክፍያው «አለኝታነት የማሳያ ግብር» እንደኾነ ገልጧል።  ኾኖም ግን ኤርትራውያን ግብሩን ካልከፈሉ አንዳንድ የመንግሥት አገልግሎቶችን አያገኙም ሲል አክሏል። 
«ኤርትራ ግብሩን የምትሰበስብበት መንገድ የጀርመንን ሕግ የሚጥስ አይደለም፤ በመሠረቱም ኢ-ምክንያታዊ ኾኖ የሚታይም አይደለም» ሲል የጀርመንን ቡንደስታግ ግራዎቹ ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። 

ጀርመን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ስደተኞችን «ስለመጸጸታቸው» የሚገልጥ ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ ያስገድዳል ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚያውቊ የጠቀሱ ባለሞያዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። ስደተኞች እንዲፈርሙበት የሚቀርብላቸው ሰነድ ላይ ስደታቸው ሕገወጥ እንደኾነ እና ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱም ለመቀጣት ፍቃደኛ መኾናቸውን እንዲገልጡ ይገደዳሉ ሲሉም አክለዋል። 

ይኽንንም ቢኾን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንደ ችግር አይመለከተውም። «የመጸጸት ማብራሪያ ሰነዱ ላይ የሚፈርሙ በመሰረቱ ሕጋዊ መብታቸው ተበላሽቶ አለያም የፈራሚዎቹ ኤርትራ የሚገኙ ቤተሰቦች ለጭቆና ተዳርገው እንደኾን የጀርመን መንግስት የቀረበለት የሚታወቅ ነገር የለውም» ብሏል።  ይኽን ሰነድ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበለት ቤርሊን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ማመልከቻው የኢምግሬሽን ክፍሉ ሕገወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠር ያዘጋጀው መኾኑን ጠቅሷል። በራሱ መፈረሙ በቀጥታ ለቅጣት ይዳርጋል ማለትም እንዳልኾነ ተገልጧል።

የጀርመን ኤምባሲዎች በአካባቢው ሃገራት ቪዛ ለመስጠት የሚሰጡት ቀጠሮ የተራዘመ ነው

የጀርመን ኤምባሲዎች በአካባቢው ሃገራት ቪዛ ለመስጠት የሚሰጡት ቀጠሮ የተራዘመ ነው

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀድሞ የኤርትራ የሰብአዊ መብቶች ልዑክ ሼይላ ኪዛሩት ግን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2016 ይኽን አባባል ተቃውመው ነበር። ይልቁንም ሰነዱ ባለሥልጣናት ወደ ሀገር ተመላሾችን ለመጉዳት የሚያስችላቸው «ደረቅ ቼክ» እንደኾነም ተከራክረዋል። 

ስደተኞቹ ቤተሰቦቻቸውን ወደ ጀርመን አስመጥተው በአንድነት ለመኖር እንዳይችሉ ሌላኛው ብርቱ ተግዳሮት ለረዥም ጊዜ የቪዛ ቀጠሮ የመጠበቃቸው ነገርም እንደኾነ ይነገራል። የጀርመን ኤምባሲዎች በምሥራቅ አፍሪቃ ቪዛ ለመስጠት የሚሰጡት ቀጠሮ የተራዘመ ነው።  ኤርትራ ውስጥ የሚገኘው ጀርመን ኤምባሲ የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከት የቪዛ ክፍል የለውም። 

በጎረቤት ሃገራት በሚገኙ ኤምባሲዎች በውክልና የሚሰጡ የቪዛ ቀጠሮዎች በአብዛኛው ከዓመት በላይ ናቸው። ትንሹ የቪዛ ቀጠሮ ጊዜ ሱዳን በሚገኘው ኤምባሲ የሚሰጠው ሲኾን፤ አንድ ስደተኛ ቤተሰቡን ወደ ጀርመን ለማስመጣት ለቀጠሮ የዐሥር ወራት ጊዜ መጠበቅ ይኖርበታል። ተመሳሳይ ቀጠሮ ለማግኘት ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የጀርመን ኤምባሲ 13 ወራትን መጠበቅ ያስፈልጋል። ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ ደግሞ የቪዛ ቀጠሮው 14 ወራትን ይፈጃል።
በጀርመን የግራዎቹ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ኡላ የልፕከ ይኽ ረዥም ቀጠሮ በአስቸኳይ ማጠር እንደሚገባው ይናገራሉ።

«በዚህም አለ በዚያ ተጨባጩ ነገር ቪዛ መስጠትን በተመለከተ በጀርመን ኤምባሲዎች ከመጠን ያለፈ የጥበቃ ጊዜ አለ። የኤምባሲ ሠራተኞች ተቀባይነት ያለው የቪዛ ጥበቃ ጊዜን ለማረጋገጥ በአስቸኳይ መጠናከር ያስፈልጋቸዋል።»
የረዥም ጊዜ ጥበቃው ለመጀመሪያ ጊዜ ትንሽም ቢኾን በመሰረተ ሐሳቡ ለውጥ ታይቶበታል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በቪዛ አሰጣጥ የቀጠሮ ጊዜ ላይ ቀጣዩን ብሏል። «የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የጥበቃ ጊዜውን በንቃት እየተከታተለው ነው።  ለሚታየው መዘግየትም  በተቻለ ፍጥነት በተደራጀ ርምጃ እና ሠራተኞችን በማጠናከር ምላሽ ይሰጣል» ይላል የመሥሪያ ቤቱ ጽሑፍ።

በጀርመን የግራዎቹ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ኡላ የልፕከ

በጀርመን የግራዎቹ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ኡላ የልፕከ

ኾኖም ግን በውጭ ሃገራት የሚገኙ ለየት ያሉ ጉዳዮችም ነገሮችን ሊያጓትቱ እንደሚችሉ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጠቊሟል። በየሃገራቱ ቤቶችን ለመገንባት፤ ለመከራየት አለያም ለመግዛትም አስቸጋሪ ወይንም የተንቀራፈፈ እንደኾነ በመጠቆም በተለይ በጉዳዩ ላይ የሰለጠኑ ባለሞያዎችን ወደየሀገሩ ለመላክ፤ ብሎም ባለሞያዎቹን ለማሰልጠን ረዥም ጊዜ እንደሚፈጅ አስምሮበታል።

እናም ታዲያ ለኤርትራ ስደተኞች እና ለቤተሰቦቻቸው በርካታ ነገሮች የሚያመለክቱት አኹንም በተስፋ ተሞልተው በድጋሚ መጠበቃቸው እንደማይቀር ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ዳንኤል ፔልስ 

Audios and videos on the topic