የኤልኒኞ ጉዳት በደቡባዊ አፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 19.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኤልኒኞ ጉዳት በደቡባዊ አፍሪቃ

ኤልኒኞ የተባለው የአየር ጠባይ ለውጥ በጎርጎሮሳዊው 2016 በዓለም ዙሪያ 60 ሚሊዮን ሰዎችን ለችግር ዳርጓል ። ሲፈጥን በየሁለት ዓመቱ ሲዘገይ ደግሞ በየሰባት ዓመቱ የሚከሰተው ኤል ኒኞ በመላው ዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ያስከትላል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:29
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:29 ደቂቃ

ኤልኒኞ በደቡባዊ አፍሪቃ

 በመገባደድ ላይ ባለው በጎርጎሮሳዊው 2016 ደቡባዊ አፍሪቃ በኤልኒኞ ሰብብ በ30 ዓመት ታሪኳ አይታ የማታውቀው ከባድ ድርቅ መቷታል ።ዓመቱን በሙሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የረሀብ ስጋት ላይ ነበሩ ።ችግሩ በማንኛውም ሰው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ የሚከሰትም ነበር ።

የደቡብ አፍሪቃ ትልቅዋ ከተማ የጆሀንስበርግ ሀብታም ነዋሪዎች በ2016 ደቡብ አፍሪቃን በመታው ድርቅ ምክንያት የጓሮ አትክልቶቻቸውን ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ውሐ ማጠጣት አልቻሉም ። መታጠቢያ ውሐም አያገኙም ። ከዚህ በባሰ ግን ኤልኒኞ በደቡባዊ አፍሪቃ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ አደጋ አጋልጧል ። ለረሀብ ። ኤልኒኞ በተለይ ማዳጋስካር ሞዛምቢክ ዚምባብዌ  እና ማላዊን በመሳሰሉ ሀገራት ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል ።  ፋኒ ካሉምፓ ማላዊ ናማባዞ በሚባለው መንደር የምትኖር ባለትዳር እና የአምስት ልጆች እናት ናት ። ከድርቁ ሰላባዎች አንዷ ናት ። 
«በእርሻችን ላይ በቆሎ ተክዮ ነበር ። ሆኖም በድርቁ ምክንያት በቆሎው በትክክል አልበቀለም ። ምንም ምርት አላገኘንም ። ምርት ስላጣን የሚበላ ቅጠላ ቅጠል  ፍለጋ ወደ ጫካ እንሄዳለን ። ይሁን እና ብዙውን ጊዜ ሳንበላ ነው የምንተኛው  ።»
ፋኒ በደቡባዊ አፍሪቃ ድርቅ ያስከተለው ጉዳት አንዷ ምሳሌ ናት ። በአካባቢው ብዙዎች ራሳቸውን ችለው መተዳደር አልቻሉም ።  ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ነው የሚገፉት ። የተመድ ባልደረባ ቲሞ ፓካላ እንደሚሉት አሁን የዝናብ ወቅት ቢሆንም ፣ ድርቁ ብዙዎቹን አዳክሟል ። 

«አሁን በደቡባዊ አፍሪቃ ከፍተኛ ዝናብ የሚጥልበት ወቅት ላይ ነው ያለነው ። በብዙ ሀገራት በመጋቢት ወይም በሚያዚያ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል ። ምርት ከመሰብሰቡ በፊት ግን በድርቁ የተጎዱ ሰዎች የመቋቋሚያ ዘዴዎቻቸውን በሙሉ አሟጠው ተጠቅመዋል ።»
የተመድ እንደሚለው በደቡባዊ አፍሪቃ ሀገራት የሚኖሩ ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ረሀብ የሚያሰጋቸው ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ።ከመካከላቸው ግማሽ ሚሊዮኑ አሳሳቢ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል ፤ 3 ሚሊዮኑ ደግሞ ንጹህ የመጠጥ ውሐ አያገኙም ። በርካታ የእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በድቅ በተመቱ ሀገራት ሰዎች ለመርዳት ይንቀሳቀሳሉ ። ማላዊ የሚገኙት የበጎ አድራጊው ድርጅት ዎርልድ ቪዥን ባልደረባ አንድሪው ቺማራ ይህ ለማድረግም የተለያዩ ስልቶች አሉ ይላሉ ።
«ችግር ውስጥ ለወደቁ ሰዎች ምግብ እናቀርባለን ። በአንዳንድ አካባቢዎች ለመዘገብናቸው ሰዎች ገንዘብ ይሰጣል ።  ገበያ ላይ ምግብ ለሚገኝባቸው አካባቢዎች ነው ገንዘብ የምንሰጠው ምግብ በማይገኝባቸው ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ምግብ እንሰጣለን ። » 
የእርዳታ ድርጅቶች በደቡባዊ አፍሪቃ ለብዙሀኑ ተጎጂ መድረስ መቻላቸው ጥሩ ዜና ነው ። ይሁንና መጥፎ ነገር የሚፈለገው ገንዘብ አለመገኘቱ ነው እንደ ፓካላ ።
«ወደ 1.3ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋል ። ምናልባትም ወደ 550 ሚሊዮን ዶላር ያህል ያጥረናል ። ለድርጊት መርሃ ግብራችን የጠየቅናቸውን እርዳታዎች ካላገኘን እስከሚቀጥለው የእህል መሰብሰቢያ ጊዜ ድረስ ለአደጋ ለተጋለጡት ሰዎች ምግብ ማቅረብ አንችልም ።ይህንንም እርዳታ ካላገኘን ተጽእኖው ከፍተኛ ነው የሚሆነው ። »

ያን ፊሊፕ ሹልተር/ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ 
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች