የኤሌክትሪክ ኃይል ከቆሻሻ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 22.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የኤሌክትሪክ ኃይል ከቆሻሻ

የምስራቅ አፍሪካዋ ኢትዮጵያ በመዲናዋ በሚገኝ የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ የተከመረ ቆሻሻ ተደርምሶ ሀዘን ላይ በከረመችበት በዚህ ሰሞን የስካንድኒቪያዋ ስዊዲን ከቆሻሻ ጋር በተያያዘ መነጋገሪያ ሆናለች፡፡ ስዊዲን የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ የሳበችው በቆሻሻ ብዛት ተቸግራ ሳይሆን ቆሻሻ አጥሯት ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:42

የረጲ ኃይል ማመንጫ ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው

ስዊዲን ቆሻሻ ከሌሎች ሀገሮች ማስገባት ሁሉ ጀምራለች፡፡ ሊያውም በዓመት 700 ሺህ ቶን የሚጠጋ፡፡ ስዊዲን 10 ሚሊዮን ከሚጠጋው ህዝቧ የሚሰበሰበውን 99 በመቶ ቆሻሻ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መልሳ ጥቅም ላይ ማዋሏ ነው “የቆሻሻ ያለህ?” ያስባላት፡፡ የሀገሪቱ ይፋዊ ድረ-ገጽ እንደሚጠቁመው ከየቤቱ ከሚሰበሰበው ቆሻሻ ውስጥ 50 በመቶው ለኃይል ማመንጫነት ይውላል፡፡ በስዊዲን ቆሻሻን በማንደድ ሙቀት እና የኤሌክትሪክ ኃይልን የሚያመነጩ 32 ተቋማት አሉ፡፡ አውሮፓዊቷ ሀገር የመጀመሪያውን እንዲህ አይነት ተቋም በዋና ከተማይቱ ስቶኮሆልም ያቋቋመችው እንደጎርጎሮሳዊው በ1904 ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከስዊዲን አንድ ምዕት አመት ዘግይታም ቢሆን መንገዱን ተያይዛዋለች፡፡ ከቆሻሻ ኃይል የሚያመነጭ ተቋም ለመገንባት ግንባታ ከጀመረች ሶስት ዓመት አለፋት፡፡ ቦታው ደግሞ የመጋቢት ሁለቱ አስደንጋጩ አደጋ ከደረሰበት አቅራቢያ ነው፡፡ በዚያ አዲስ አበባ በ1957 ዓ.ም ለደረቅ ቆሻሻ መጣያነት ስራ ያስጀመረችው የቆሻሻ መድፊያ ከእነ ክምር ቆሻሻው አለ፡፡

 “ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ማመንጫ” የተሰኘው አዲሱ ፕሮጀክት ግንባታው ወደ መገባደዱ ቢቃረብም ይህን ለዓመታት የተከማቸ ቆሻሻ ወደ ኃይል የሚለወጥ አይደለም፡፡ ይልቅስ ከአዲስ አበባ በየቀኑ ከሚሰበሰበው ወደ ሁለት ሚሊዮን ኪሎግራም ቆሻሻ ውስጥ 85 በመቶውን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የመቀየር እቅድ ያለው ነው፡፡ አቶ ሳሙኤል አለማየሁ የኃይል ማመንጫውን በመገንባት ላይ ያለው የካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የኃይል ማመንጫው ክምር ቆሻሻውን የማይጠቀምበትን ምክንያት እንዲህ  ያስረዳሉ፡፡

“እስከዛሬ የተከማቹት ቆሻሻዎች ከአፈር ጋር እየተደባለቁ ነው የሚደመደሙት፡፡ [ቆሻሻው] በጣም ብዙ የሆነ የአፈር ክምችት አለው፡፡ አፈሩ መንደድ የማይችሉ ንጥረ ነገር በብዛት ስላለው በእንደዚህ አይነት ተቋሞች ውስጥ አስገብቶ ለመጠቀም አዲስ ለእነዚያ ብቻ የሚሰራ ተቋም መስራት ያስፈልጋል” ይላሉ አቶ ሳሙኤል፡፡

በዚህ ዓመት መገባደጃ ላይ አገልግሎት መስጠት የሚጀምረው የረጲው የኃይል ማመንጫ ተቋም አዳዲስ ቆሻሻዎችን ነው የሚቀበለው ከተባለ ቀጣዩ ጥያቄ “እሱንስ እንዴት አድርጎ ነው ወደ ኃይል የሚቀይረው?” የሚለው ይሆናል፡፡ አቶ ሳሙኤል ማብራሪያ አላቸው፡፡

“የአምስት ቀን ቆሻሻን ማከማቸት የምንችልበት ማከማቻ ቤት ሰርተንለታል፡፡ ሁሉም የቆሻሻ መኪኖች ሲመጡ የራሳቸው ቤት አላቸው፡፡ ልክ መኪናው ሲመጣ በራሳቸው አውቀው የሚከፍቱ በሮች አሉ፡፡ በሮቹ ሲከፈቱ መኪኖቹ ቆሻሻዎቹን ይደፋሉ፡፡ ቆሻሻዎቹን በደንብ አድርገን ውሃቸው ጠልሎ እንዲወጣ ካደረግን በኋላ ወደ ማንደጃ ውስጥ እንከታቸዋለን፡፡ ቆሻሻው እነዚህ ማንደጃዎች ውስጥ በ1600 ዲግሪ ሴንትግሬድ ላይ ነው የሚነደው፡፡ ከ1000 እስከ 1600 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሲነድ ውሃውን ወደ እንፋሎት ይቀይረዋል፡፡ እንፋሎቱ ደግሞ ቲን ተርባይን የሚባሉ ማሽኖችን በማንቀሳቀስ ጀነሬተሩ በየቀኑ ኃይል እንዲያመነጭ እናደርጋለን ማለት ነው” ሲሉ ሂደቱን ይዘረዝራሉ፡፡

በመንግስታዊው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለቤትነት እየተገነባ ከሚገኘው ከዚህ ተቋም የሚመነጨው ኃይል በየቀኑ ስድስት ሚሊዮን አምፖሎችን ለስምንት ሰዓታት የማብራት አቅም እንዳለው አቶ ሳሙኤል ይገልጻሉ፡፡ የዚህ ተቋም ዋናው አበርክቶት የሚሆነው በየቀኑ ከአዲስ አበባ የሚሰበሰበው ቆሻሻ ወደ መጣያ ቦታዎች ሄዶ እንዳይቀበር ማድረጉ ነው፡፡

የመዲናይቱ ቆሻሻዎቿን እየተቀበለ ሲከምር የቆየው የረጲ የደረቅ ቆሻሻ መጣያ እንደሚዘጋ በይፋ የተነገረው በህዳር 2005 ዓ.ም ነበር፡፡ አዲስና ዘመናዊ የቆሻሻ መጣያ በሰንዳፋ ቢገነባም የአካባቢው ነዋሪዎች ባስነሱት ተቃውሞ አገልግሎት መስጠት ማቋረጡ ይታወሳል፡፡ በዚህ ምክንያት የረጲየደረቅ ቆሻሻ መጣያ የተወሰነው ክፍል የቆሻሻ መደርመስ አደጋው እስከደረሰ ድረስ አገልግሎት መስጠት ቀጥሎ ነበር፡፡ በቦታው የተከማቸው ቆሻሻ የሚፈጥረው ብክለት የአካባቢ ባለሙያዎችን ሲያስብ ቆይቷል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ በርካታ ጥናቶችም ተደርገዋል፡፡

አቶ ይስሐቅ ደምሴ በቦታው ጥናት ካደረጉ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው፡፡ የታዳሽ ኃይልና የቆሻሻ አያያዝ ባለሙያው አቶ ይስሐቅ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ የዓለም ሙቀት መጨመርን ለማስተካከል ከሚወሰዱ እርምጃዎች አንዱ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በረጲ የተከማቸውን ቆሻሻ አያያዝ ማሻሻል የሚቻለው በሁለት መንገዶች መሆኑንም በቀደምት ጥናታቸውን ጠቁመው ነበር፡፡

“ቆሻሻው በተፈጥሮ ሊነድ የሚችል ጋዝ ያመነጫል፡፡ ይህንን ቆሻሻ አንደኛ ነገር ወደ ኃይል መቀየር ይቻላል፡፡ ቀጥታ በማንደድ ወይም የሙቀት ኃይል እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ ወይም በጋዝ ተርባይን ወደ ኤሌክትሪክ ቀይሮ መጠቀም የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡ ሁለተኛ የማስወገጃ ዘዴ ምንድነው? ሙቀት ማመቅ የሚችሉ የጋዝ አይነቶች (ግሪን ሀውስ ጋዝ) የበካይነት ወይም ሙቀት የመያዝ አቅሙን ለማሳጣት በማቃጠል፤ ወደ ካርቦን ዳይኦክሳይድ በመቀየር፤ አቅሙን ማሳነስ ይቻላል” ይላሉ ባለሙያው፡፡

ከቆሻሻ የሚመነጨውን ሜቴንን መቆጣጠር የአየር ንብረት ለውጥን ለማገት እንደሚያግዝ አቶ ይስሐቅ ይናገራሉ፡፡ ሚቴንም ሆነ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ለዓለም ሙቀት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የጋዝ አይነቶች ናቸው፡፡ ሙቀት በማመቅ ረገድ ግን ሚቴን ከካርቦን ዳይኦክሳይድ የላቀ ኃይል አለው፡፡ አቶ ይስሐቅ ብርድ ልብስን በምሳሌነት በመጠቀም የሁለቱን ጋዞች የማመቅ አቅም ያነጻጽራሉ፡፡

“ለምሳሌ ካርቦን ዳይኦክሳይዱ ሙቀት ለማመቅ አንድ ብርድ ልብስ ብትጠቀም ሜቴኑ ግን እስከ 25 ብርድ ልብስ ያህል ሊቆጠር ይችላል፡፡ ወይም ሃያ አምስት ጊዜ የማያዝ አቅም አለው ማለት ነው፡፡ የካበቢ አየሩን እንዳያሞቅ ወደ ህዋ ሊሄድ የሚገባው የሙቀት መጠን ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋር ሲነጻጸር ሃያ አምስት ጊዜ የመብለጥ አቅም አለው፡፡ በዚህ የተነሳ ይህን አቅሙን ለማሳጣት ማቃጠልና ወደ ካርቦን ዳይኦክሳይድ መቀየር እንደ አንዱ መንገድ ሆኖ ይታሰባል” ይላሉ አቶ ይስሐቅ፡፡

በዚህ መልኩ የበካይ ጋዞችን ልቀት ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በቆሼ መተግበር ከጀመረ አራት ዓመት ሆኖታል፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት መንገዶቹን ያመላከተው የአቶ ይስሐቅ ጥናት ታዲያ አዲስ አበባ ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በስድስት ከተሞች ያሉ የቆሻሻ መጣያ ቦታዎችንም የዳሰሰ ነበር፡፡ በመቀሌ፣ ባህርዳር፣ አዋሳ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ እና ሀረር ባሉ የቆሻሻ መጣያዎች የተከማቸው ቆሻሻ በአግባቡ እንዲወገድ ከተደረገ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ጥቅም እንደሚያመጣም አመላክቷል፡፡ እንዲህ የካርቦን ልቀትን የሚቀንሱ ፕሮጀክቶች ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጠቀም ያለ ገንዘብ ያስገኛሉ፡፡

ከቆሻሻ የሚመነጨውን በካይ ጋዝ መቆጣጠር እና ወደ ጥቅም የመለወጥ ሂደት በከተሞች ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በገጠር የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባዮ ጋዝ የተሰኘውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የደረቅ እና የፍሳሽ ቆሻሻዎችን ወደ ኃይል ለመለወጥ ስራዎች ከተጀመሩ ቆዩ፡፡ በ1950ዎቹ በአምቦ እርሻ ኮሌጅ አማካኝነት በኢትዮጵያ የተዋወቀው የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ አሁን በኢትዮጵያ ገጠር አካባቢዎች እንደሚታየው በቤት ደረጃ ሳይሆን በሰርቶ ማሳያ የተጀመረ ነበር፡፡

በገጠር የከብቶችን እና የሰው እዳሪን በማጠራቀም ኃይልን ማመንጨቱም ሆነ በከተማ ቆሻሻን ለተመሳሳይ አላማ የመጠቀሙ ተመሳሳይ ሂደት እንደሚመሳሰል አቶ ይስሐቅ ይናገራሉ፡፡

“በየቤቱ የሚሰራውም ሆነ በቆሻሻ መድፊያ ላይ የሚመነጨው የጋዝ አይነት መጠኑ ሊለያይ ይችላል እንጂ ተፈጥሮው አንድ ነው፡፡ ያው ሚቴን የተባለው ጋዝ ነው፡፡ ባዮ ጋዝ ወይም ላንድ ፊል ጋዝ የሚባለው ከፍ ያለው መጠን ሚቴን ሲሆን ዝቅ ያለው ደግሞ ካርቦንዳይኦክሳይድ ነው፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ለምሳሌ ላንድ ፊል የምታገኘው 60 በመቶ ሚቴን ከሆነ 40 በመቶው ካርቦንዳይኦክሳይድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንደዚሁ በየቤቱ የምታገኘው ምናልባትም 50 በመቶ ሚቴን ሆነ 50 በመቶው ካርቦንዳይኦክሳይድ ይሆናል፡፡ ግን እንደአጠቃላይ ላንድፊል ጋዝም ሆነ ባዩ ጋዝ ከ50 እስከ 60 በመቶ ሚቴን ወይም የሚቃጠል ጋዝ ይይዛል ተብሎ ይታሰባል” ይላሉ ባለሙያው ሲያብራሩ፡፡ 

ኢትዮጵያ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ ያወጣችው ሀገር አቀፍ የባዮ ጋዝ እቅድ ቴክኖሎጂውን በቤት ውስጥ የማስፋፋት ዓላማ ነበረው፡፡ ገጠሩን ትኩረት ያደረገው ይህ እቅድ በአራት ክልሎች 14 ሺህ የባዮ ጋዝ ማብሊያዎችን ለመትከል አቅዶ ነበር፡፡ ባለፈው ሐምሌ ለንባብ የበቃ እና የእቅዱን አፈጻጸም የሚገመግም ጥናት እንዳመለከተው ሀገሪቱ ከእቅዱ ማሳካት የቻለችው 60 በመቶውን ብቻ ነው፡፡     

"አረንጓዴ የልማት ስትራቴጂን እከተላለሁ" የምትለው ኢትዮጵያ ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥናቶች አካሄዳለች፡፡ እቅዶችም አውጥታለች፡፡ ተግባር ላይ ግን ወገቤን እንዳለች አለች፡፡ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ የቆሼውን አደጋ ተከትሎ ሲነገር የሰነበተው አካባቢውን ወደ ህዝብ መናፈሻነት የመለወጥ ዕቅድ ነው፡፡ ይህ ዕቅድ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ባለስልጣናት መነገር ከጀመረ በትንሹ አምስት አመታት ተቆጠረ፡፡ እንደዚህ ለሚጓተቱ እቅዶች የቆሼው አደጋ ማንቂያ ደወል ነው፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic