የኤሌክትሪክ ሽያጭ በኢትዮጵያ | ኤኮኖሚ | DW | 20.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኤሌክትሪክ ሽያጭ በኢትዮጵያ

ከኢትዮጵያ ኃይል ማመንጫዎች መካከል 97 ሜጋ ዋት ማመንጨት የነበረበት የአመርቲነሽ የኃይል ማመንጫ በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የግድቡ ዉሐ በመቀነሱ ሐይል ማመንጨት ሙሉ በሙሉ አቁሟል። የኢትዮጵያ መንግስት በአገር ውስጥ በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ እና እጥረት ቢፈጠርም የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት አገራት እየሸጠ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:28
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:28 ደቂቃ

የኤሌክትሪክ ሽያጭ በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግስት በስምንት ወራት ከኤሌክትሪክ ሽያጭ 123 ሚሊዮን ዶላር (2.6 ቢሊዮን ብር) ማግኘቱን አስታውቋል። ገቢዉ አገሪቱ ለጎረቤቶቿ ኬንያ፤ጅቡቲ እና ሱዳን ከሸጠችው የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘችውን ገቢ ይጨምራል። የውሃ፤መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ዘገባ መስሪያ ቤታቸዉ ያስገኘው ገቢ የእቅዱን 82 በመቶ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከውሃ፤እንፋሎት እና ንፋስ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለአካባቢው አገራት ለመሸጥ ካቀደ ሰንብቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ለኬንያ እና ታንዛኒያ ለእያንዳንዳቸው 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ውል ገብቷል። ያገር ውስጥ ፍላጎቱንም ይሁን የኤሌክትሪክ ኃይል የመሸጥ እቅዱን ለማሳካት የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ተጀምረዋል።
በኦሞ ወንዝ ግርጌ በ1.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው እና 1,870 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የነበረው የግልገል ጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ በኢትዮጵያ መንግስት የእድገት እና ለውጥ ዕቅድ ዘመን ታቅደው ከነበሩት መካከል አንዱ ነው። ከግልገል ጊቤ ሶስት የሚገኘው ኃይል ግማሽ ያህሉ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የታቀደ ሲሆን ቀሪው ለጎረቤት አገራት ሊሸጥ የታሰበ ነበር። ከዚህም ውስጥ 500 ሜጋ ዋት ለኬንያ፤200 ሜጋ ዋት ለሱዳን እና 200 ሜጋ ዋት ለጅቡቲ። የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ አገራት በተገኘ ብድር በመጀመሪያው የእድገትና ለውጥ ዕቅዱ እገነባለሁ ካላቸው የኃይል ማመንጫዎች መካከል የተጠናቀቀው ይህ የግልገል ጊቤ ሶስት ብቻ ነው።
አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የዜጎችን የለት ተለት ኑሮ እያስተጓጎለ ነው የሚል ሮሮ ይደመጣል። ሮሮው ግን ከለት ተለት ሲባባስ እንጂ መፍትሔ ሲያገኝ አልታየም። ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ ለተዘረጋው የባቡር አገልግሎት የሚፈለገውን ኃይል ማቅረብ ባለመቻሉ የድንጋይ ከሰል በአማራጭነት ለመጠቀም ተገዷል። የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም ገበያ በቦንድ ሽያጭ እና ከዓለም ባንክ ባገኛቸው ብድሮች አማካኝነት በአዲስ አበባ ፤አዳማ ፤ሐዋሳ እና መቀሌን በመሳሰሉ ከተሞች የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየገነባ መሆኑን አስታውቋል። የማምረቻ ፓርኮቹ የሚፈልጉትን ከፍ ያለ የኃይል መጠን አገሪቱ ማቅረብ ስለመቻሏ ግን አሁንም ጥያቄዎች አሉ።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic