የኢጣልያ የፖለቲካ ቀውስ  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 29.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የኢጣልያ የፖለቲካ ቀውስ 

በኢጣልያ ባለፈው ሳምንት የተጀመረው ጥምር መንግሥት ምሥረታ ከተቋረጠ በኋላ ሀገሪቱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ተሰይሞላታል። ስዩሙ ጠቅላይ ሚኒስትር በፍጥነት መንግሥት ያቋቁማሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሀገሪቱ ምርጫ እስከሚካሄድ ይቆያል የተባለው ጊዜያዊ መንግሥት የኢጣልያ ምክር ቤትን ድጋፍ ካላገኘ መፍረሱ አይቀርም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:44

ኢጣሊያ አዲስ መንግስት

በኢጣልያ ህዝበኛ ንቅናቄ እና ቀን ጽንፈኛ ፓርቲ ተጣምረው ባለፈው ሳምንት የጀመሩት መንግሥት ምሥረታ ተቋርጦ ሀገሪቱ ሌላ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተሰየመላት አንድ ቀን ተቆጠረ። ኢጣልያ ባለፈው ረቡዕ  ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሰየምላት የሁሉም ትኩረት ማለት ይቻላል አሁን የቀድሞ የሚባሉት የስዩሙ ጠቅላይ ሚኒስትር የጁሴፔ ኮንቴ መንግሥት በኢጣልያ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ እንዲሁም በአውሮጳ ህብረት እና በዩሮ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ ላይ ነበር።  ትኩረት የሳበውም የ53 ዓመቱ ኮንቴ የአውሮጳ ህብረትን እና ዩሮን በሚቃወሙ እንዲሁም ቅድሚያ ለኢጣልያ በሚሉ ፓርቲዎች ለጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጣቸው ነበር።  ባለፈው እሁድ የሆነውን ግን የዛሬ ሳምንት  የጠበቀ ወይም ይሆናል ብሎ ያሰበ አልነበረም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ኮንቴ በተሰየሙ በ4ተኛው ቀን ባለፈው እሁድ ሳይጠበቅ የኢጣልያ ፕሬዝዳንት ሰርጅዮ ማታሬላ የሰጧቸውን መንግሥት የመመስረት ሥልጣን  አስረከቡ። 
«ሁላችሁም እንደምን አመሻችሁ! እንደተጠበቀው ከሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ማታሬላ የለውጥ መንግሥት ለመመሥረት የተቀበልኩትን ሥልጣን አስረክቤያለሁ። የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ግንቦት 23 ሃላፊነቱን ስለሰጡኝ አመሰግናቸዋለሁ።ለሁለቱ የፖለቲካ መሪዎች ለአምስት ኮከብ ንቅናቄ መሪ ለሉዊጂ ዲ ማዮ እና ለሊግ መሪ ማቴዮ ሳልቫኒም ለዚህ ሃላፊነት ስለጠቆሙኝ አድናቆቴን እገልጻላቸዋለሁ። በበኩሌ ለዚህ ሃላፊነት ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ ጥረት እንዳደረግኩ አረጋግጥላችኋለሁ።ይህ ሊሆን የቻለውም እኔን ከጠቆሙኝ የፖለቲካ ኃይላት በኩል በነበረው ሙሉ የትብብር ድባብ ነው። አመሰግናለሁ።»

ኮንቴ መንግሥት እንዲመሰርቱ የተሰጣቸውን ሥልጣን ያስረከቡት ባዋቀሩት ካቢኔ ውስጥ ለኤኮኖሚ ሚኒስትርነት ያጯቸውን የ81 ዓመቱን የኤኮኖሚ ምሁር ፓውሎ ሳቮናን ፕሬዝዳንቱ ባለመቀበላቸው ነበር። ፕሬዝዳንት ማታሬላ ሳቮናን የተቃወሙበትን ምክንያት አስረድተዋል። 
« ከኤኮኖሚ ሚኒስትሩ በስተቀር በሁሉም ሚኒስትሮች ተስማምቼያለሁ። የኤኮኖሚ ሚኒስትር ምርጫ፣ ለፋይናንሱ ዓለም ፈጣን የመተማመኛ አለያም የማስጠንቀቂያ መልዕክት ያስተላልፋል። ይህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መርሃ ግብሩን በተረዳ አብላጫ ድምጽ ካላቸው የፖለቲካ ኃይል ከበሪታ በሚሰጠው ሰው እንዲያዝ፣ በተጨማሪም በተደጋጋሚ ሲቀርብ እንደነበረው ዩሮን ሊተናኮል የሚችል ወይም ከዩሮ ወደመውጣት የሚወስድንን መስመር የማይደግፍ እንዲሆን ጠይቄያለሁ።» 
ማታሬላ ይሁንታ ያልሰጧቸው ሳቮና፣ የአውሮጳ ህብረት ማሻሻያዎች እንዲያደርግ የሚጠይቁ እና ኢጣልያም ከጋራ መገበያያው ገንዘብ ዩሮ እንድትወጣ የሚፈልጉ የታወቁ የኤኮኖሚ ምሁር ናቸው። ፕሬዝዳንቱ ፣ኮንቴ ሳቮናን በሌላ እንዲተኩ ጠይቀው ነበር። ሆኖም ኮንቴም ሆነ ተጣምረው መንግሥት ምሥረታ ጀምረው የነበሩት ፓርቲዎች አሻፈረን ብለው ሥራቸውን አቋረጡ። የማታሬላ ውሳኔ  ባለአምስት ኮከብ ንቅናቄን እና የሊግ ፓርቲዎችን በእጅጉ አበሳጭቷል። በመጋቢቱ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያሸነፈው ባለ አምስት ኮከብ ንቅናቄ መሪ ሉዊጂ ዲማዮ እንዳሉት አሁን በኢጣልያ ዴሞክራሲ መኖሩ አጠያያቂ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው ።
« በህይወት ዘመናቸው ዩሮን ወይንም አውሮጳን የተቹ ባለሞያዎች ምሁራን በሙሉ ጥሩ ሚኒስትሮች ሊሆኑ አይችሉም? ጉዳዩ ይህ ከሆነ በኢጣልያ ትልቅ ችግር አለ ። ይህ ነፃ ዴሞክራሲ አይደለም።» 
የሊግ ፓርቲ መሪ ማትዮ ሳልቫኒም ኢጣልያ ዴሞክራሲያዊ ሀገር መሆንዋን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑን ተናግረው በኢጣልያ ጉዳይ ላይ የሚወስኑት ኢጣልያውያን ጀርመናውያን ወይስ ፈረንሳዮች? ሲሉ ጠይቀዋል። ከፓርቲዎቹ እምቢታ በኋላም ፕሬዝዳንት ማታሬላ ካርሎ ኮታሬሊን በጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰየሙ። የኤኮኖሚ ምሁሩ ኮታሬሊ ትናንት ሃላፊነቱን ከማታሬላ እንደተረከቡ ከሚያከናውኗቸው ተግባራት አንዱ አዲስ ምርጫ ማቀድ መሆኑን ተናግረዋል። 

 «የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት በጠየቁኝ መሠረት መንግሥት የመመሥረት ሥልጣን ተረክቤያለሁ። እንደ ኢጣልያዊ ይህ ሃላፊነት ሲሰሰጠኝ ከፍተኛ ክብር ይሰማኛል። ለዚህም የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።  ኢጣልያን ወደ አዲስ ምርጫ የሚወስድ መርሃ ግብር ለፓርላማው እንዳቀርብ ፕሬዝዳንቱ ጠይቀውኛል። ይህንንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማቅረብ አቅጃለሁ። በጣም በአጭር ጊዜ የሚኒስትሮችን ዝርዝር ለፕሬዝዳንቱ አቀርባለሁ። ለፓርላማውም መርሃ ግብሬን አቀርባለሁ። ይሁንታ ካገኘሁ መርሃ ግብሩ የ2019 ዓምን በጀት የሚጨምር ይሆናል። ከዚያ በኋላ ፓርላማው ተበትኖ በ2019 መጀመሪያ ምርጫ ይካሄዳል።»
ይሁን እና ጊዜያዊው ጠቅላይ ሚኒስትር ኮታሬሌ ይህን ማድረግ የሚችሉት የምክር ቤቱን ይሁንታ ካገኙ ነው። ሆኖም የአምስት ኮከብ ንቅናቄ እና የሌጋ አባላት በሚያመዝኑበት በአሁኑ የኢጣልያ ምክር ቤት  ኮታሬሊ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ማሳካታቸው አጠራጣሪ ነው። ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፓርላማው ድጋፍ ካልሰጣቸው መንግሥታቸው ወዲያውኑ ሥልጣን እንደሚለቅ እና ከነሐሴ በኋላ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ፣ዋናው ሥራው መደበኛ ተግባራትን ማከናወን ብቻ እንደሚሆን ኮታሬሊ ተናግረዋል።
በመጋቢቱ ምርጫ ውጤት መሠረት መንግሥት መመስረት ባለመቻሉ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑ የኢጣልያ ፖርቲዎች እና ህዝቡን ለሁለት የከፈለ ይመስላል ይላል የሮሙ ወኪላችን ተክለእዝጊ ገብረ እየሱስ።
ተጣምሮ መንግሥት መመሥረቱ ያልተሳካላቸው ባለ አምስት ኮከብ ንቅናቄ እና ሊጋ መንግሥት ከመመስረት አደናቀፉን ያሏቸውን ፕሬዝዳንት ማታሬላ እንዲከሰሱ እየወተወቱ ነው። በቅርቡም በሮማ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ አቅደዋል። ይሁን እና የአውሮጳ ህብረት እና ፈረንሳይ የፕሬዝዳንት ማታሬላን እርምጃ ደግፈዋል። ጀርመን ደግሞ በቅርቡ የተረጋጋ እና ከአውሮጳ ህብረት ጋር የሚቆም መንግሥት ይመሰረታል ብላ ተስፋ እንደምታደርግ አስታውቃለች። ያም ሆኖ  ከአውሮጳ ህብረት መሥራች አገሮች አንዷ በሆነችው በኢጣልያ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ  እና ከሥስት ወር አለያም ከ6 ወራት በኋላ ይካሄዳል የተባለው ምርጫ ምን ይዞ እንደሚመጣ ከወዲሁ ማሳሰቡ አልቀረም ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic