የኢጣልያ የፖለቲካ ቀውስ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 06.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የኢጣልያ የፖለቲካ ቀውስ

የኢጣልያው ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዮ ሬንሲ ባልተጠበቀው የህዝበ ውሳኔ ውጤት ሰበብ ከሥልጣን ለመውረድ ወስነዋል ። ውጤቱ የሀገሪቱን ጽንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስፈንጥዟል ። ህዝቡ የሰጠው መልስ በአውሮጳ ህብረት በኢጣልያ እና ሀገሪቱ አባል በሆነችበት በዩሮ ቀጣና ሊያስድር የሚችለው ተጽእኖ ማነጋገሩ ቀጥሏል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:41
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:41 ደቂቃ

የኢጣልያ የፖለቲካ ፖለቲካ ቀውስ

 «በኢጣልያ ፖለቲካ ውስጥ በህግ መምሪያ ምክር ቤት እና በክፍላተ ሀገር ያሉትን እጅግ ቡዙ  የሥልጣን መቀመጫዎችን ለመሰረዝ ነበር የምፈልገው ። አልተሳካልኝም ። ስለዚህ ከሥልጣኔ መነሳት አለብኝ ። ነገ ከሰዓት በኋላ ካቤኔውን ሰብስቤ የስራ ባልደረቦቼን ላከናወኑት እጅግ የሰመረ ጠንካራ የቡድን ሥራ ካመሰገንኳቸው በኋላ ለሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት የስንብት ደብዳቤየን አስረክባለሁ ።»የኢጣልያው ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዮ ሬንሲ የህገ-መንግሥት ማሻሻያ ጥያቄአቸው ባለፈው እሁድ በዝህበ ውሳኔ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ከዚህ ቀደም ቃል በገቡት መሠረት ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ያሳወቁበት መግለጫ ነበር ። ሬንሲ ትናንት ማታ ከኢጣልያው ፕሬዝዳንት ሰርጅዮ ማታሬላ ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ከተነጋገሩ በኋላ ከሥልጣን  የመውረድ እቅዳቸውን  የጎርጎሮሳዊው 2017 በጀት እስኪጸድቅ ድረስ እንዲያዘገዩት ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋቸዋል ። ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ትናንት ማታ በወጣው መግለጫ መሠረት በጀቱ እንደጸደቀ ሬንሲ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለኢጣልያው ፕሬዝዳንት ማስረከብ ይችላሉ  ። ሬንሲ እንደፈለጉት አላሠራ ያላቸው የኢጣልያ ህገ መንግሥት እንዲቀየር ጥያቄ ያቀረቡት በጎርጎሮሳዊው የካቲት 2014 ሥልጣን ከያዙ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ነበር ። የሬንሲ እና የመሀል ግራው ፓርቲያቸው «ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ» ፣  በሚያዚያ 2014 ነበር ለኢጣልያ የህግ መወሰኛ እና የህግ መምሪያ ምክርቤቶች ማሻሻያውን የቀረቡት ። ረቂቅ ህጉ ማሻሻያዎች ተደርገውበት ከአንድ አመት ከ6 ወር በኋላ በህግ መወሰኛ ምክር ቤት ተቀባይነት ሲያገኝ  በጥር 2016 ዓም ደግሞ የህግ መምሪያውን ምክር ቤት የመጀመሪያ ድጋፎች አግኝቷል ። በህግ መወሰኛ ምክር ቤት ለመጨረሻ ጊዜ የፀደቀው ጥር 2016 ዓም ሲሆን በሚያዚያ 2016 ዓም ደግሞ የህግ

መምሪያ ምክር ቤቱን የመጨረሻ ይሁንታ አገኘ ። ይሁንና ማሻሻያው በሁለቱም ምክር ቤቶች የፀደቀው ከሁለት ሦስተኛ በላይ በሆነ  የአብላጫ ድምጽ ባለመሆኑ i,ሀገሪቱ ህገ መንግሥት አንቀጽ 138 በሚያዘው መሠረት ነው ያለፈው እሁዱ ህዝበ ውሳኔ የተካሄደው ። ህዳር 25 ፣2009 ዓም የኢጣልያ ህዝቡ ድምጹን የሰጠውም የኢጣልያ ህገ-መንግሥት ይሻሻል ወይስ እንዳለ ይቀጥል በሚለው ጥያቄ ላይ ነበር ። ብዙሀኑ ኢጣልያውያን ህገ መንግሥቱ አይሻሻል ሲሉ ድምጻቸውን ሰጥተዋል ። ሬንሲ እና ፖርቲያቸው ያቀረቡትን ማሻሻያ ውድቅ ያደረገው 59.7 በመቶው መራጭ ነው ። በዚህ ህዝበ ውሳኔ ድምፅ ለመስጠት ከተመዘገበው 47 ሚሊዮን ኢጣልያዊ ከ68 በመቶው በላይ ድምጹን መስጠቱ ተነግሯል ። ከመካከላቸው የሬንሲን ሀሳብ የደገፉት 41 በመቶው ነበሩ ። ማሻሻያ እንዲደረግ የተፈለገውም በኢጣልያ ህገ መንግሥት የኢጣልያ ምክር ቤት ስብጥር እና ሥልጣን ላይ እንዲሁም በመንግሥት በክልሎች እና በሌሎች የአስተዳደር አካላት መካከል ሊኖር የሚገባው የሥልጣን ክፍፍል ላይ ነበር ። ሬንዚ ከተሸነፉበት ህዝበ ውሳኔ በኋላ እንዳሉት አልተሳካላቸውም እንጂ ፣ ዓላማቸው ነገሮችን ማቅለል አሠራርን ማቀላጠፍ ነበር ። 
"አሁን የሚሠራበት የኢጣልያ ዴሞክራሲ የፓርላማ ስርዓትን መሠረት ያደረገ ነው ። የመታመኛ ድምጽ ስንጠይቅ ስርዓቱን ለማቅለል ነበር ። ለሁለቱም ምክር ቤቶች እኩል ሥልጣን የሚሰጠው ባይካሜራሊዝምን ለማስወገድ ፣ፖለቲካ የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመቀነስ እና ፣ ቀጥተኛ ዴሞክራሲን ለማስፋት ነበር ።ይህ ነበር ለህዝበ ውሳኔ ያቀረብነው ማሻሻያ ። ግን አሳማኝ አልነበርንም ፤ አዝናለሁ የምለቀው ያለ ምንም መፀፀት ነው ። ምክንያቱ ዴሞክራሲ እና አይሆንም የሚለው ድምጽ ካሸነፈ እኛም በስሜት እና በቁርጠኝነት መታገላችን ሀቀ ነው ። የኔ መንግሥት ልምድ እዚያህ ላይ ያበቃል »
በጎርጎሮሳዊው በ1948 ቱ ህገ መንግሥት በሚመራው የኢጣልያ የፖለቲካ ስርዓት ሁለት ምክር ቤቶች አሉ ። አንደኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም የህግ መምሪያ ምክር ቤት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ወይም ሴኔት ነው ። የሁለቱም ምክር ቤቶች አባላት ህዝብ በቀጥታ በሚሰጠው ድምጽ ነው የሚመረጡት ። ኢጣልያ ውስጥ አንድ ህግ የሚያልፈው እኩል ሥልጣን ያላቸው ሁለቱም ምክር ቤቶች ሲጸድቁት ብቻ ነው ። የሬንዚ ማሻሻያ «bicameralism» የሚባለውን ይህ ዓይነቱን አሠራር ለማስቀረት ያለመ ነበር  ። ማሻሻያው የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ወይም የሴኔት አባላት ቁጥር ከ315 ወደ 100 ዝቅ እንዲል በተጨማሪም አባላቱ በህዝቡ በቀጥታ ከመመረጥ ይልቅ በክልል ምክር ቤቶች እንዲመረጡ የሚያደርግ ነው ። በማሻሻያው መሠረት አንዳንድ ከንቲባዎችም እንደ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሊያገለግሉ ይችላሉ ። ሬንሲ እንዳሉት ማሻሻያው አንድ ህግ በሁለቱም ምክር ቤቶች እስኪጸድቅ የሚወስደውን ጊዜ ለማሳጠር ታስቦም ነው የተዘጋጀው። ህዝቡ ማሻሻያውን ተቀብሎት ቢሆን ኖሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ይሁንታ ሳያስፈልገው ፣ የኢጣልያን በጀት ጨምሮ በርካታ ህጎች እንዲያሳልፍ ማድረግ ይቻል ነበር ።ሆኖም ሴኔቱ ለምሳሌ ሌሎች ህገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን እና የአውሮፓ ህብረት ውሎችን ማፅደቅን የመሳሰሉ

ከበድ ያሉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን ብቻ እንዲሰጠው ነበር የታሰበው ።ጠቅላይ ሚኒስትር ሬኔ ይህ አልተሳካላቸውም  ። ምንም እንኳን ኢጣልያውያን ባለፈው እሁድ ህዝበ ውሳኔ ያካሄዱት በህገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች ላይ ቢሆንም ውሳኔውን የብሪታንያ ህዝብ ከአውሮጳ ህብረት ለመውጣት ካሳለፈው ውሳኔ ጋር የሚያጠጋጉት አልጠፉም ። የምርጫው ውጤት ህዝቡ ከተለመዱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወዳፈነገጡት ድርጅቶች የማዘንበሉ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል የሚሉም አሉ ። የህዝበ ውሳኔው ውጤት የኢጣልያ ፅንፈኛ ፓርቲዎችን አስፈንድቋል ። «ባለ አምስት ኮከብ ንቅናቄ» (FIVE STAR MOVEMENT )በምህጻሩ M5S ተብሎ የሚጠራው ዋነኛ የኢጣልያ ጽንፈኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ውጤቱን ካወደሰ በኋላ በአስቸኳይ አዲስ ምርጫ እንዲጠራ ለመጠየቅ የቀደመው የለም ። በአሁኑ ጊዜ የአብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ጥያቄ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲቋቋም ነው ። በኢጣልያ ፓርላማዎች መቀመጫዎች ያሉት የ M5S ፓርቲ መሪ  ቤፔ ግሪሎ ግን ከሬንሲ ስንብት በኋላ ኢጣልያውያን በተቻለ ፍጥነት የአዲስ ምርጫ ጥሪ እንዲደረግላቸው አሳስበዋል ። በኢጣልያ ፓርላማ የባለ አምስት ኮከብ ንቅናቄ አንዱ ተወካይ ሉዊጂ ዲ ማዮም ተመሳሳይ ጥያቄ ነው ያቀረቡት ።
«በህዝበ ውሳኔው የተከፋፈለችውን ሀገሪቱን እንደገና አንድ ለማድረግ እና አዲስ ምርጫ ለማካሄድ  ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ። »
ግሪሎ በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓም የመሠረቱት ይህ ባለ አምስት ኮከብ ንቅናቄ ምዕራባውያን በሩስያ ላይ ማዕቀብ መጣላቸውን ይቃወማል ፤ የባንኮችን አሠራር ፣ትላልቅ ኩባንያዎች እና የነፃ ንግድ ውሎችን ይተቻል ። በኢጣልያ የዩሮ ቀጣና አባልነት ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድም ይፈልጋል ።«ኖርዘርን ሊግ» የተባለው የአውሮጳ ህብረት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲም ምርጫ ይጠራ ብሏል ። የቀድሞው የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የመሠረቱት «ፎርሳ ኢጣልያ» የተሰኘው ፓርቲ ደግሞ ከነዚህ በተለየ የሬንዚ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በአዲስ መሪ ሌላ መንግሥት እንዲያቋቁም  ነው የጠየቀው ፤ዋናው ጉዳይ ሬንሲ ወደ መጡበት መመለስ አለባቸው ፤ጨዋታው አብቅቷል ሲል ። ሬንሲ ባጋጠማቸው ሽንፈት የተደሰቱት የአውሮጳ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎችም ናቸው ከመካከላቸው ብሔራዊ ግንባር የተሰኘው የፈረንሳይ ቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ ይገኝበታል ። የፓርቲው መሪ ማሪን ለፔን ውጤቱ እንደታወቀ « ኢጣልያውያን የአውሮጳ ህብረትን እና ሬንሲን አንፈልጋችሁም ብለዋል ፤የህዝቦች የነጻነት እና የዋስትና  ጥማታቸው ጆሮ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ በትዊተር ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል ። የኢጣልያው ህዝበ ውሳኔ ውጤት

የአውሮጳ ህብረትን ማሳሰቡ አልቀረም ።የአውሮፓ ህብረት እና አባል መንግሥታት በውጤቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ውጤቱ ሬንሲ እንዳሰቡት ባለመሆኑ ማዘናቸውን በቃል አቀባያቸው በኩል ገልጸውላቸዋል ።
«መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የጠቅላይ ሚኒስትር ማትዮ ሬንሲን ሥልጣን መልቀቅ በሀዘኔታ ነው የተቀበሉት ። ከማትዮ ሬንሲ ጋር በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ እና በመተማመን ሠርተዋል ።ሆኖም ርግጥ ነው የኢጣልያ ያ ዜጎች የደረሱበት ውሳኔ መከበር ይኖርበታል ።»
በኢጣልያ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ በጋራ መገበያያው ዩሮ ላይ ሊያስከትል ይችላል የተባለው ጫና ከወዲሁ እያነጋገረ ነው ። በህዝበ ውሳኔው ማግሥት ትናንት በገንዘብ ገበያው የዩሮ ምንዛሬ መውረዱ ተዘግቧል  ። ውሳኔው የውጭ ባለሀብቶችን እንዳያሸሽ እያሰጋ ነው ። ይህም ምናልባት እዳቸው ባላያቸው ላይ የሚያናጥረውን የኢጣልያ ባንኮች ከክስረት ለማዳን በሚደረግላቸው ድጋፍ ላይ ተጽእኖ በማሳደር  በዮሮ ተጠቃሚ አባል ሀገራት ማህበር ላይ ሰፊ የገንዘብ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ግምትም አለ ። የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ ግን አሁን ስለ ዩሮ ቀውስ ልናነሳ የምንችልበት ምክንያት የለም ነው ያሉት ሁኔታው የኢጣልያን ወይም የኢጣልያን ባንኮች የኤኮኖሚ ሁኔታ ሊለውጥ አይችልም ሲሉ ስጋቶቹን አጣጥለዋል ። 
ከሁለት ዓመት ከ9 ወር በፊት ሥልጣን የያዙት የ41 ዓመቱ ሬንሲ በ92 ዓመት የሀገሪቱ ታሪክ ለመሪነት የበቁ የመጀመሪያው ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው ። ሬንሲ እሁድ አሸማቃቂ ውጤት ቢገጥማቸውም በኢጣልያ ፖለቲካ ውስጥ አበቃላቸው ማለት አይደለም እየተባለ ነው ። በጎሮጎሮሳዊው 2012 ተነጥቀውት የነበረውን  የዴሞክራሲያዊ ፓርቲያቸውን መሪነት በዓመቱ መልሰው እንደመያዛቸው አሁን የለቀቁትንም ሥልጣን እንደገና የማግኘት እድል ሊገጥማቸው እንደሚችልም የሚናገሩ አሉ ። ለአሁኑ ግን እየተናነቃቸውም ቢሆን ሽንፈታቸውን ተቀብለዋል  

«ተሸንፌያለሁ ፣ ይህንንም ቢተናነቀኝም ጮክ ብዬ እናገራለሁ ። እኛ ሮቦቶች አይደለንም ።»
አሁን ዋነኛው ሃላፊነት በኢጣልያው ፕሬዝዳንት ሰርጅዮ ማታሬላ ላይ ወድቋል ። የኢጣልያ ፓርላማ የመጨውን ዓመት በጀት እስኪያጸድቅ ፋታ የሚያገኙት ፕሬዝዳንቱ ቀጣዩ እርምጃቸው ምን ይሆን ? አብረን የምናየው ይሆናል ።  

ኂሩት መለሰ 

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች