የኢጣልያ አዲስ ጥምር መንግሥት ምሥረታ  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የኢጣልያ አዲስ ጥምር መንግሥት ምሥረታ 

ከአውሮጳ ህብረት እንዲሁም ከዩሮ መሥራች ሀገሮች አንዷ የሆነችው ኢጣልያ፣ ወደፊት የህብረቱን መርሆች በሚጻረሩ ፓርቲዎች መተዳደርዋ የአውሮጳ ህብረትን ስጋት ውስጥ ከቷል። ሰሞኑን ሊመሰረት ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ ጥምር መንግሥት የህብረቱ ትልቅ ፈተና እና ራስ ምታት ይሆናል ተብሎም ነው የሚገመተው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:57

የኢጣልያ አዲስ መንግሥት ምሥረታ

በኢጣልያ የአዲስ መንግሥት ምሥረታ የተቃረበ ይመስላል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጥምር መንግሥት ለመመስረት የተስማማቱት ፀረ አውሮጳ ህብረት አቋም ያላቸው ሁለት ፓርቲዎች እጩ ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ትናንት ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አሳውቀው የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው ። የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን በቅርቡ ይመሠረታል ተብሎ በሚጠበቀው በአዲሱ የኢጣልያ ጥምር መንግሥት እና በአውሮጳ ህብረት ስጋት ላይ ያተኩራል። ዝግጅቱን ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች።
በኢጣልያ ምርጫ ከተካሄደ 2 ወር ከሦስት ሳምንት በላይ ተቆጥሯል። ፀረ-አውሮጳ ህብረት እና ፀረ-የውጭ ዜጋ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ አብላጫ ድምጽ ያገኙበት፣ ነባር ፓርቲዎች ደግሞ ከባድ ሽንፈት የተከናነቡበት የጎርጎሮሳዊው መጋቢት 4፣2018 የኢጣልያ ምርጫ ውጤት በሀገሪቱ የመንግሥት ምሥረታን አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል። በዚህ ምርጫ ሁሉም ፓርቲዎች መንግሥት ለመመስረት የሚያስችላቸውን በቂ ድምጽ አለማግኘታቸው አንዱ ችግር ነበር። ከሁሉም በላይ በምርጫው አብላጫ ድምጽ ካሸነፈው «አምስት ኮከብ ንቅናቄ» በመባል ከሚጠራው ህዝበኛ ፓርቲ አለያም ሶሥተኛ ደረጃን ከያዘው ፀረ የውጭ ዜጋ አቋም ካለው የሌጋ ድጋፍ ውጭ መንግሥት መመስረት አስቸጋሪ መሆኑ መንግሥት ምሥረታውን እንዲዘገይ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳል። ኢጣልያን ሲመራ የቆየው ነባሩ «ዴሞክራቲክ ፓርቲ» አብላጫ ድምጽ ካገኘው ከ«አምስት ኮከቦች ንቅናቄም ሆነ ከቀኝ ፅንፈኞች ጋር ጥምር መንግሥት እንደማይመሰርት ይልቁንም ተቃዋሚ እንደሚሆን ማሳወቁ የተለመደውን የፖለቲካ ስርዓት የሚቃወሙ ፀረ ዩሮእ እና ፀረ ስደተኛ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ተጣምረው መንግሥት የሚመሰርቱበትን እድል ፈጥሮላቸዋል። የሮሙ ወኪላችን ተክለ እዝጊ ገብረየሱስ እንደሚለው አምስት ኮከብ ንቅናቄ እና ሌጋ ለመጣመር ከመስማማታቸው በፊት ሌሎች ሙከራዎችም

ተደርገው ነበር።
በዚሁ መሰረት ከ11 ሳምንታት ውጣ ውረድ በኋላ ባለፈው አርብ FIVE STAR MOVEMENT «አምስት ኮከብ ንቅናቄ» በምህጻሩ M5S እና ፀረ ስደተኞች አቋም ያለው ሊግ የተባለው ፓርቲ ጥምር መንግሥት ለመመስረት ተስማምተዋል። ሁለቱ ፓርቲዎችም የህግ ምሁሩን  ጁሴፔ ኮንቴን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ መምረጣቸውን ትናንት ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አሳውቀው የፕሬዝዳንቱ የመጨረሻ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው። የ54 ዓመቱ ኮንቴ የማናቸውም ፓርቲ አባል ያልሆኑ እና ብዙም የማይታወቁ ነገር ግን የ«አምስት ኮከቦች ንቅናቄ»ደጋፊ ናቸው ተብሏል። ተጣማሪዎቹ ፓርቲዎች እንደሚሉት ፍላጎታቸው መንግሥታቸው ኢጣልያን እና ህዝቧን እንዲያስቀድም ነው። ከአምስት ኮከቦች ጋር የሚጣመረው የሊግ ፓርቲ ሊቀመንበር ማቴዮ ሳልቪኒ ይህንኑ የፓርቲያቸውን አቋም ፓርቲዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ይፋ ባደረጉበት በትናንትናው እለት ተናግረዋል። 
« እኛ በግልጽ የምንፈልገው በምርጫ ዘመቻችን ወቅት እንዳልነው፣የኢጣልያን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል የሚያደርግ መንግሥት ነው፤ እያንዳንዱን እና ሁሉንም የሚያከብር ነገር ግን ኢጣልያን ማዕከል የሚያደርግ ኢጣልያኖችን የሚያስቀድም መንግሥት ።»
ከአውሮጳ ህብረት እንዲሁም ከዩሮ መሥራች ሀገሮች አንዷ የሆነችው ኢጣልያ፣ ወደፊት የህብረቱን መርሆች በሚጻረሩ ፓርቲዎች መተዳደርዋ የአውሮጳ ህብረትን ስጋት ውስጥ ከቷል። ሰሞኑን

ሊመሰረት ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ ጥምር መንግሥት የህብረቱ ትልቅ ፈተና እና ራስ ምታት ይሆናል ተብሎም ነው የሚገመተው። የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ ይህን ሊያስብሉ የቻሉትን ምክንያቶች ይዘርዝራል።
ለመጣመር  የተስማሙት ሁለቱ ፓርቲዎች በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ከገቡት ቃል በመነሳት የሚመሰርቱት መንግሥት ለሀገሪቱ ኤኮኖሚም ሆነ ለአውሮጳ ህብረት የሚበጅ አይደለም የሚሉ ትችቶች እና ስጋቶች ቢሰነዘሩም መንግሥት ፓርቲዎች ግን ማስተባባያዎችን እየሰጡ ነው። የሊጋ መሪ  ሳልቪኒ ስለ አዲሱ የኢጣልያ መንግሥት ከውጭ ዓለም በሚሰነዘረው ስጋት እና ትችት ላይ በሰጡት መልስ «ሀሳብ አይግባችሁ» ብለዋል ፤ 
«ከሌሎች አገራት ሚኒስትሮች እና ከአውሮጳ ህብረት ኮሚሽነሮች የሚሰነዘሩ አንዳንድ ስጋት አዘል መግለጫዎችን በትኩረት እና በአግራሞት እንከታተላለን። ሊያሳስባቸው የሚገባ አንድም ነገር የለም። መንግሥት ኢጣልያን ማሳደግ ነው የሚፈልገው። ለልጆቻንን ብዙ ሥራ ፣አነስተኛ ግብር ፣ዝቅተኛ ቢሮክራሲ እና ተጨማሪ ደህንነት የሰፈነባት የተሻለች ሀገር ትተን ለማለፍ አቅደናል።»
በቅርቡ ይመሰረታል ተብሎ ስለሚጠበቀው የኢጣልያ ጥምር መንግሥት ኢጣልያውያን የሚሰጡት  አስተያየት ደግሞ የተለያየ ነው። እስቲ እንያቸው ሲሉ የደገፏቸው እና ያልተቀበሏቸው ቁጥር  ተቀራራቢ ባይባልም የሰፋ ልዩነት አይታይበትም እንደ ሮሙ ወኪላችን ተክለእዝጊ። ያም ሆኖ  የሁለቱ ፓርቲዎች የፖለቲካ ልምድ አናሳ መሆን ህዝቡ በጥርጣሬ እንዲያያቸው ማድረጉ

አልቀረም።
ከአምስት ኮከቦች ንቅናቄ ቅሬታዎች ውስጥ «ጀርመን እና ፈረንሳይ በበላይነት በሚመሩት በአውሮፓ ህብረት ውስጥ የኢጣልያ ሚና ዝቅተኛ መሆን ነው። በጋራ መገበያያውን ዩሮም ላይ ያነሳቸው ጥያቄዎች አሉ። ፀረ ስደተኞች አቋም የሚያራምደው ተጣማሪው የሌጋ መሪ ሲልቪኒ በአዲሱ ጥምር መንግሥት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ሃላፊነት መያዝ ይፈልጋሉ። የርሳቸው የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርነት ዘመን ግን ለውጭ ዜጎች በተለይም ኢጣልያ ላሉ መንግሥት ህገ ወጥ ለሚላቸው እና ወደ ኢጣልያም ለመግባት ለሚሞክሩ ስደተኞች አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም እንደ ተክሊኖ።
በቅርቡ ይመሰረታል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ የኢጣልያ ተጣማሪ መንግሥት በአውሮጳ ህብረት የጋራ መርሆች ላይ ጥያቄዎችን የሚያነሳ እና ለውጦችንም የሚጠብቅ ከሆነ ምን ያህል አብሮ ሊጓዝ ይችላል የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ገበያው ከወዲሁ የሚያሰጉ ጉዳዮች ቢኖሩም መግባባት ላይ የሚደረስባቸውን መንገዶች ሊገኙም ይችላሉ የሚል ተስፋ አለ ይላል።
የአምስት ኮከቦች ንቅናቄ መሪ ሉዊጂ ዲማዮ ደግሞ ትችቱ ስራ እስክንጀምር ድረስ ይቆይ ሲሉ ተደምጠዋል
" ፖለቲካዊ መንግሥት ነው የሚሆነው የፖለቲካ ጥያቄዎችን ማዕከል የሚያደርግ መንግሥት ነው የሚሆነው ። ምናልባት በዓለም አቀፍ ደረጃ ልል የምፈልገው መጀመሪያ ወደ ሥራ እንግባ እና ከዚያ በኋላ ተቹን ይህን የማድረግ መብት አላችሁ ሆኖም እስቲ እንጀምረው»

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic