የኢጣልያ ምርጫ ውጤት እና መጪው መንግሥት  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 06.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የኢጣልያ ምርጫ ውጤት እና መጪው መንግሥት 

ባለፈው እሁድ በተካሄደው የኢጣልያ ምርጫ ፀረ ስደተኛ እና ፀረ አውሮጳ ህብረት አቅም ያላቸው ፓርቲዎች የላቀ ድምጽ ማግኘታቸው እያነጋገረ ነው። ፓርቲዎቹ ያገኙት ድምጽ ራሳቸውን ችለው መንግሥት ለመመሥረት የሚያበቃቸው ባለመሆኑ ማን ከማን ጋር ተጣምሮ መንግሥት እንደሚያቆም እስካሁን ግልጽ አይደለም። ውጤቱ ለአውሮጳ ህብረት ጥሩ አይደለም ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:48

አነጋጋሪው የኢጣልያ ምርጫ ውጤት

 ከትናንት በስተያ የተካሄደው የኢጣልያ ምርጫ ውጤት ከዚህ ቀደም በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች እንደተገመተው ቢሆንም ማነጋገሩ ግን አልቀረም። በቀደሙት ትንበያዎች ቀኝ ጽንኛ ፣ ፀረ ስደተኛ እና የጋራውን ገንዘብ ዩሮን የሚጠራጠሩ ፓርቲዎች ከፍተኛ ድምጽ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተነግሮ ነበር። ሆኖም ለዓመታት በፖለቲካው መድረክ የቆዩትን ነባር ፓርቲዎች በሰፊ ልዩነት ያሸንፋሉ ተብሎ ግን አልተጠበቀም። ትናንት ይፋ በተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት መሠረት የቀድሞው የኢጣልያ ፕሬዝዳንት ሲልቭዮ ቤርሉስኮኒ የሚመሩት ሦስት ፓርቲዎች የተሰባሰቡበት የመሀል ቀኝ ህብረት 37 በመቶ ድምጽ አሸንፏል። ህብረቱ ያካተታቸው ፓርቲዎች ቀኝ ጽንፈኛው ኖርዘርን ሊግ 18 በመቶ፣ ፎርሳ ኢጣልያ 14 በመቶ  የኢጣልያ ወንድማማቾች የተባለው ፓርቲ ደግሞ 5 በመቶ ድምጽ አሸንፈዋል። በአሁኑ ምርጫ  ቀኝ ጽንፈኛው ኖርዘርን ሊግ ከቤርሉስኮኒ ፓርቲ «ፎርሳ ኢጣልያ» የላቀ ድምጽ ማግኘቱ ፎርሳ ኢጣልያን አስደንግጧል።  ፓርቲዎቹ ባደረጉት ስምምነት መሠረት ሦስት ፓርቲዎች የተሰባሰቡበት ህብረት ወሰ ሥልጣን ከመጣ አብላጫ ድምጽ ያገኘው ፓርቲ ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ይመርጣል። ምንም እንኳን በዚህ ምርጫ የመሀል ቀኙ ህብረት ከፍ ያለ ድምጽ ቢያገኝም አሸናፊ የተባለው ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ 32.6 በመቶ ድምጽ ለማግኘት የበቃው ባለ አምስት ኮከቦች ንቅናቄ ነው። የዚህ ዩሮን የሚጠራጠረው እና ፀረ የተለመዱት ፓርቲዎች አቋም ያለው ፓርቲ ውጤት ኢጣልያውያንን በእጅጉ አስገርሟል። የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አልቤርቶ ካስቴልቬቺ ፓርቲው ለዚህ ድል ሊበቃ የቻለበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

«ለመጀመሪያ ጊዜ ከምንም የተነሳ ማለትም ከዝቅተኛው የኢጣልያ ህብረተሰብ የወጣ አንድ ንቅናቄ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከመራጩ ህዝብ 30 በመቶውን ድምጽ አግኝቷል። ይህ የሆነውም የባለ አምስት ኮከቦች ንቅናቄ በዋነናነት ፀረ-መንግሥት እና ፀረ-የተለመዱት ፓርቲዎች ንቅንቄን በቅጡ ወደ ህዝቡ ማድረስ በመቻሉ ነው። »
የኢጣልያ ህዝብ ድምጹን ለቀኝ ዘመም እና ፀረ ስደተኛ ፓርቲዎች የሰጠው በነባር ፓርቲዎች ላይ ያለው እምነት በመሟጠጡ መሆኑ ይነገራል። ከዚህም በላይ አሸናፊዎቹ ፓርቲዎች ለህዝቡ የነገሩት አማላይ ተስፋም ለድላቸው አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይታመናል። የሮሙ ወኪላችን ተክለ እዝጊ ገብረ እየሱስ እንደሚያስረዳው የተለመዱትን ፓርቲዎች የሰለቸው ህዝብ አዲሶቹን ደግሞ እስቲ እንሞክራቸው እያለ ነው። ያም ሲባል ግን ህዝቡ በአጠቃላይ ውጤቱን ደግፏል ማለት አይደለም ። በዚህ ምርጫ ዋነኛው ተሸናፊ የመሀል ግራው ጥምረት «ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ» ነው።በቀድሞው የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ማትዮ ሬንዚ የሚመራው ይህ ፓርቲ 23 በመቶ ድምጽ ነው ያገኘው። ይህ ውጤትም በፓርቲው ታሪክ እጅግ አነስተኛው ነው። በአሁኑ ምርጫ ፓርቲያቸው እጅግ ዝቅተኛ ድምጽ ያገኘው ሬንዚ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል። ማትዮ ሬንዚ አሁን ያሸነፉት አክራሪ እና ዝግ ያሏቸው ፓርቲዎች ኢጣልያን የመምራት ብቃት የላቸውም ሲሉ አጣጥለዋቸዋል። የሬንዚ ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሸነፍ የተገመተ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ቁልቁል ይወርዳል ተብሎ ግን አልተተነበየም ነበር። ይሁን እና ከኢጣልያ ነባር ፓርቲዎች አንዱ የሆነው «ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ» የገጠመው ከባድ ሽንፈት ካስቴልቬቺ እንዳሉት ሠራተኛውን ማዕከል ለሚያደርጉ ሌሎች ፓርቲዎች ምሥረታ መንገዱን ይጠርጋል።
«የመሀል ግራው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በዚህ ምርጫ ተሸናፊ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሽንፈቱ የመሪው የማትዮ ሬንዚ ነው። ከዓመታት በፊት ሬንዚ ከ38 እስከ 40 በመቶ ወደሚደርስ ድምጽ ነበረ የሚያመሩት አሁን ይህ በግማሽ አንሶ ወደ 20 በመቶ ዝቅ ብሏል። ይህ በእርግጥም ከላፉት 20 ዓመታት ወዲህ ለዴሞክራሲያዊ ፓርት ታላቅ ሽንፈት ነው።ይህ አዳዲስ የሠራተኛ ማህበራት ንቅናቄዎች ቦታውን እንዲወስዱ መነሻ ይሆናል።»  

የኢጣልያ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች እና ባለ አምስት ኮከብ ንቅናቄ ተጣምረው መንግሥት ይመሰርታሉ የሚል ግምት አለ። ይሁን እና የፓርቲዎቹ አቋም መለያየት ግን ተጣምሮ መንግሥት መመሥረት ማስቻሉን አጠያያቂ አድርጎታል። በዚህ የተነሳም ተክለ እዝጊ እንደሚለው በኢጣልያ በአጭር ጊዜ ውስጥ መንግሥት መመሥረቱ ላይሳካ ይችላል። 
በአሁኑ የኢጣልያ ምርጫ የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር። ከ60 ሚሊዮን የኢጣልያ ህዝብ የመምረጥ መብት ያላቸው 43 ሚሊዮን ኢጣልያውያን ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ከቀደመው ከጎርጎሮሳዊው ከ2013ቱ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ በጣም ከፍተኛ ህዝብ ነው የወጣው። ውጤቱ የአውሮጳ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎችን አሰደስቷል። ከህዝቡ አብዛኛው ለቀኝ ጽንፈኞች ድምጹን መስጠቱ የአውሮጳ ህብረትን አስደንግጧል። የህብረቱ አባል ሀገራት ምክንያቱ ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የደረሰባት ከፍተኛ የስደተኞች ጫና መሆኑን የተረዱ ይመስላል። በዚህም ህብረቱ ተወቅሷል። ከወቃሾቹ አንዱ የላክሰምበርጉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የንስ አሰልቦርን ለውጤቱ የአውሮጳ ህብረትን ልቅ የፍልሰት ስርዓት ተጠያቂ አድርገዋል። ፈረንሳይም የውጤቱ መንስኤ ሀገሪቱ የደረሰባት የስደተኞች ጫና መሆኑን ተናግራ ችግሩን ለመከላከል አውሮጳን በማጠናከሩ እንደምትገፋ አስታውቃለች። ጀርመን ደግሞ በኢጣልያ ከአውሮጳ አስተሳሰብ ጋር የሚሄድ መንግሥት ይመሰረታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብላለች። ለማንኛውም በኢጣልያ እንዱት መንግሥት እንደሚመሰርት እና ይህም መቼ ሊሆን እንደሚችል ለአሁኑ ባይታወቅም ርዕሰ ብሄሩ አሸናፊዎቹን ካነጋገሩ በኋላ የሚደርሱበት ውሳኔም ለመንግሥት ምሥረታ ወሳኝ መሆኑን ተክለእግዚ ገልጿል።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ


 

Audios and videos on the topic