የኢንጋቢሬ ብይን መተላለፍ | አፍሪቃ | DW | 30.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኢንጋቢሬ ብይን መተላለፍ

የርዋንዳ ፍርድ ቤት ክስ በተመሠረተባቸው በወህኒ የሚገኙት የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይላት የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በሆኑት በወይዘሮ ቪክቷር ኢንጋቢሬ ላይ ብይን ይሰጥበታል ተብሎ የተጠበቀውን የትናንቱን ችሎት ለፊታችን መስከረም ወር አስተላለፈ።

In this May 16, 2010 photo, Victoire Ingabire, a presidential hopeful and an ethnic Hutu, is seen at her home in Kigali, Rwanda. Ingabire was arrested and charged with genocide ideology after giving a speech at Rwanda's genocide memorial in January 2010. Authorities say statements like Ingabire's could incite violence and lead the country back toward genocidal killings. (AP Photo/Jason Straziuso)

በኢንጋቢሬ ላይ የተመሠረተው ክስ ፖለቲካዊ ምክንያት አለው የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡ ክሱ ርዋንዳ ውስጥ ዘሬም በመንግሥት አንፃር ሂስ ማቅረብ እንደማይቻልና የሀሳብ ነፃነት እንደሌለ ያሳየ ነው ብለውታል።
እአአ ከ ጥቅምት 2010 ዓም ወዲህ ወህኒ የሚገኙት ኢንጋቢሬ በርዋንዳ የተፈፀመውን የጎሣ ጭፍጨፋ ክደዋል ለአንድ አሸባሪ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ ሰጥተዋል፡ ብሔራዊውን የፀጥታ ሁኔታ ስጋት ላይ ጥለዋል፡ ሕዝብ በመንግሥቱ አንፃር እንዲነሳ ቀስቅሰዋል በሚል ክስ የመሠረተባቸው የርዋንዳ ዋና ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ኢንጋቢሬ በዕድሜ ልክ እሥራት እንዲበየንባቸው መጠየቁን የጽሕፈት ቤቱ ቃል አቀባይ አላ ሙኩራሊንዳ አስታውቀዋል።
« ኢንጋቢሬ ላይ ዕድሜ ልክ እሥራት እንዲበየን ጠይቀናል።፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ሕጉይህን ዓይነቱን ቅጣት ይፈቅዳል፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ወይዘሮ ኢንጋቢሬ በፍርድ ቤት በአንፃራቸው ያቀረብነውን ማስረጃ ማስተባበል አልቻሉም። »
ጠበቆቻቸው ግን ኢንጋቢሬ በነፃ እንዲለቀቁ ነው የጠየቁት። የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይላት ተጠባባቂ መሪ ኧዤን ንዳሃዮ ይህንን የጠበቆቹን ጥያቄ ደግፈውታል።
« ክሶቹን የፈጠረው መንግሥት ነው። ኢንጋቢሬን ወህኒ ለማውረድ የሚያስችለው ምክንያት ማቅረብ በመፈለጉ ብቻ ነው ይህን ክስ የመሠረተባቸው። »

Ruandas Präsident Paul Kagame

የርዋንዳ ፕሬዚዳንት ፓውል ካጋሜ


የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ዋነኛ ሂሰኛ የሆኑት ኢንጋቢሬ በርዋንዳ የፍትሕ አውታር ላይ እምነት እንደሌላቸው በመግለጽ ካለፈው ሚያዝያ ወዲህ ከችሎቱ ርቀዋል።ምሥክሮች በኢንጋቢሬ አንፃር ቃላቸውን እንዲሰጡ መገደዳቸውንና የመገናኛ ብዙኃንም በአንጻፃራቸው እንዲነሱ መደረጋቸውን የገለጹት ኢንጋቢሬ መንግሥት በፍትሑ አውታር ላይ ጣልቃ እንደሚገባ አስታውቀዋል። በዚህም የተነሳ ዳኞች በነፃ ፍርድ ሊሰጡ መቻላቸውን አብዝተው እንደሚጠራጠሩት አመልክተዋል። የሂውማን ራይትስ ዎች ባልደረባ ካትሪን ቴርሳኪያን የኢንጋቢሬ አስተያየት ይጋራሉ።
« ርዋንዳ መንግሥትና ገዢው የአር ፒ ኤፍ ፓርቲ የሀገሪቱን ተቋማት በጠቅላላ፡ የፍትሑንም አውታር ጭምር ሙሉ ለሙሉ የተቆጣጠሩባት ሀገር ናት። እርግጥ፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ የፖለቲካ ክሶችን በተመለከተ ችሎቱ በትክክል ይካሄዳል። ግን፡ በብዙዎቹ ላይ የመንግሥት እጅ እንዳለበት በግልጽ ነው የሚታየው። »
ኢንጋቢሬ እአአ በ 2010 ዓም በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ በፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ አንፃር ለመፎካከር ነበር ከአሥራ ስድስት ዓመት በኋላ በስደት ይኖሩባት ከነበረችው ኔዘርላንድስ ወደ ትውልድ ሀገራቸው የተመለሱት። ይሁንና፡ ፓርቲያቸው በምርጫው እንዲይሳተፍ ሳይፈቀድለት ቀረ። እሳቸውም የመታሰር ዕጣ ገጠማቸው።
የርዋንዳ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ሰለባ የሆነው የኢንጋቢሬን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም በፕሬዚደንታዊው ምርጫ እንዳይሳተፉ ተከልክለዋል።ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ መመዝገብ ያልቻለው የአረንጓዴዎቹ ዴሞክራሲያዊው ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ምርጫው ሊደረግ ጥቂት ወራት ሲቀረው መገደላቸውና ሊቀ መንበሩም ሸሽተው በውጭ ሀገር መሰደዳቸው ይታወሳል። የሌላው ትልቁ የተቃዋሚ የርዋንዳ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪ ቤርናር ንታንጋንዳም ከ2010 ዓም ወዲህ ወህኒ ይገኛሉ።
ርዋንዳ አበረታቺ የኤኮኖሚ ዕድገት ማስገኘቷንና የጎሳ ጭፍጨፋ የተወውን ጠባሳ ያለፈ ታሪክ ለማድረግና በሁቱና በቱትሲ ጎሳዎች መካከል ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ጋቻቻ በተባሉት ባህላዊ ፍርድ ቤቶችዋ አማካኝነት ያደረገችውን ጥረት በምሳሌነት ብትጠቅስም፡ የኢንጋቢሬ ጉዳይ በግልጽ እንዳሳየው፡ በምሥራቅ አፍሪቃዊቱ ሀገር ውስጥ የሀሳብ እና የአስተያያት ነፃነት አሁንም እንግዳ ናቸው።
ሂልክ ፊሸር
አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 30.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15OhB
 • ቀን 30.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15OhB