የኢንዱስትሪ ትዕይንት በሃኖቨር | ኤኮኖሚ | DW | 21.04.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኢንዱስትሪ ትዕይንት በሃኖቨር

በዚህ በጀርመን በሃኖቨር ከተማ በያመቱ የተለመደው በዓለም ላይ ታላቁ የኢንዱስትሪ ትዕይንት እየተካሄደ ነው። በፊታችን ሰንበት ደግሞ የዓለም የገንዘብ ተቋማት ስብሰባ በዋሺንግተን ይካሄዳል።

default

በኢንዱስትሪው ትዕይንት ላይ ከ 64 ሃገራት የመጡ 4.800 አምራቾች እየተሳተፉ ሲሆን አዳዲስ የቴክኖሎጂ ግኝቶችንና ኤነርጂን ለቆጠበ የአመራረት ዘይቤ የሚበጁ መፍትሄዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። ኢጣሊያ ዘንድሮ የኤግዚቪሽኑ ተባባሪ አገር ስትሆን የሃኖቨሩ ትዕይንት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ የገበያ ዕድል በመመዘኑ በኩልም ጠቃሚ መለከያ ሆኖ መታየቱም አልቀረም።

የሃኖቨሩን የኢንዱስትሪ ትዕይንት ባለፈው ዕሑድ በይፋ የከፈቱት የጀርመኑ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር ራይነር ብሩደርለና የኢጣሊያ የሥልጣን አቻቸው ክላውዲዮ ስካጆላ ናቸው። ለነገሩ የዚህ ዓመቱ የሃኖቨር ትዕይንት በጀርመኗ ቻንስለር በወሮ/አንጌላ ሜርክልና በዘንድሮዋ ተባባሪ አገር በኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር በሢልቪዮ ቤርሉስኮኒ ነበር ሊከፈት የታቀደው። ግን ሰሞኑን በየዘርፉ እንደሆነው ሁሉ የአውሮፓን አየር አመድ ያለበሰው የተፈጥሮ ሃይል፤ የአይስላንዱ እሣተ-ገሞራ ሳይፈቅድ ቀርቷል። በብዙ የአውሮፓ አገሮች የአየር በረራው ሲታገድ ሁለቱ መሪዎችም በጊዜ ሊደርሱ አልቻሉም።

ይሁን እንጂ ከአሜሪካ ጎዟቸው በኋላ ዘግይተውም ቢሆን ወደ አገር የተመለሱት ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ቢቀር በማግሥቱ ሰኞ ትዕይንቱን ለሁለት ሰዓታት እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል። በቦታው ያሰሙት ንግግርም እንደተለመደው ተሥፋ ሰጭ ነበር።

“የሃኖቨር ትዕይንት ብዙ አምራቾችን ባሰባሰበበት በዚህ ዓመት በኤኮኖሚ ተሃድሶ ረገድ እመርታን የሚያስከትል በመሆኑ ደስተኛ ነኝ”

የሃኖቨር ትዕይንት ተሳታፊዎችም የኤግዚቢሽኑ ሃላፊ ቮልፍራም-ፎን-ፍሪትሽ እንዳስረዱት ካለፈው ዓመት የፊናንስ ቀውስ በኋላ በተሥፋ የተመሉ ናቸው።

“በተለይ በቀውሱ ሰዓት ከኦሪጂናሉ ጋር መቀጠሉን እመርጣለሁ ነበር ያለኝ በቅርቡ አንድ የኢንዱስትሪ ባለቤት። ኢሪጂናሉ ደግሞ የሃኖቨር ኤግዚቢሽን መሆኑ ነው። እና ለዚህም ነው ወደዚህ የሚመጡት”

በዕውነትም የአይስላንድ እሣተ-ገሞራ የተፋው አመድ ደመና የአየር በረራዎችን ማሰናከሉ ሳይበግራቸው በአውቶቡሶች፣ በባቡርና በአውቶሞቢል አጀብ ከቱርክ፣ ከኢጣሊያ፣ ከስፓኝ፣ ከፈረንሣይና ከስካንዲናቪያ ወዘተ. ወደ ሃኖቨር የመጡት ምርት አቅራቢዎች ብዙዎች ናቸው። አዘጋጆቹ የአየር በረራው በሰፊው ቢሰናከልም በተቻለ መጠን በርካታ አቅራቢዎችን ወደ ሃኖቨር ለመሳብ ያደረጉት ሙከራ ሰምሮላቸዋል።

በተለይ ይህ ትዕይንት የሚካሄደው ወሣኝ በሆነ ወቅት ነው። ጊዜው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ካለፈው አሠርተ-ዓመት ቀውሱ ማገገም የጀመረበት ሲሆን በዓለም ላይ ታላቁ የሆነው ትዕይንት ደግሞ ጠቃሚ መመዘኛው ሊሆን ይችላል። ይህ የጀርመን የምርት መኪና አምራች ማሕበር ሃላፊ የማንፍሬድ ቪተንሽታይንም ዕምነት ነው።

“እንደማስበው ቀስ በቀስ ዕድገት እየተደረገ መሆኑን ባለፉት ወራት ለማየት ችለናል። በአንዳንድ ዘርፎች እንዲያውም እንደገና ጠንካራ ዕርምጃ እየተደረገ ነው። እርግጥ ነው በርከት ባሉት በተለያዩ ዘርፎች ያለው የዕድገት ሁኔታ ይለያያል። ነገር ግን በአጠቃላይ ሲታይ ዛሬ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ይልቅ ተሥፋ ሰጭ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው”

የሃኖቨር ኤግዚቢሽን ዘጠኝ የተለያዩ የትዕይንት ዘርፎችን በአንድ ጥላ ስር የጠቀለለ ነው። ዘንድሮ አዲሱ ነገር በተለይ ሞቢሊቴክ በመባል የሚጠራው አማራጭ ሞተሮችንና ከብከላ በአብዛኛው የጸዳ የትራንስፖርት ዘዴን የሚጠቀልለው ዘርፍ ነው። በኤሌክትሪክ ሃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ጉዳይና የኤነርጂ ብቃት ደግሞ ዘንድሮ ዓቢይ የተሃድሶው መስኮችና ማተኮሪያዎች ናቸው። የኤሌክትሮው- ኢንዱስትሪ ማሕበር ሃላፊ ፍሪድሄልም ሎህ እንደሚሉት ይሄው የተፈጥሮ ጥበቃ ቴክኖሎጂ በጀርመን ብቻ ሣይሆን በሌሎች ብዙ አገሮችም የኤኮኖሚ ዕድገት መንኮራኩር የሚሆን ነው።

“ታላቁ ርዕስ ኤሌክትሮው እንቅስቃሴ እንደሆነ ጨርሶ አያጠያይቅም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኤነርጂ ብቃት በትዕይንቱ ዙሪያ ሁሉንም እያነጋገረ ነው። የአካባቢ አየር ጥበቃ በጀርመንና በዓለምአቀፍ ደረጃም የኤኮኖሚ መንኮራኩር ሆኖ ይገኛል። እኛ ጀርመናውያን ገና ከአሁኑ በዚህ ረገድ በዓለም ላይ 16 ከመቶ ድርሻ ሲኖረን ኢንዱስትሪው ይህን ይበልጥ እንደሚያስፋፋም አምናለሁ። እንግዲህ ይህን ታላቅ ሂደት ነው ለማለት እወዳለሁ”

ሜጋ ወይም ታላቅ ሂደት፣ ተሥፋ! የሃኖቨር ትዕይንት መርህ በወቅቱ ይህ ነው። ለነገሩ በትዕይንቱ ላይ ተሥፋን የሚያንጸባርቁ የሚዘረዘሩ ነገሮችም አልታጡም።

“ይህንን በዚህ ትዕይንት ላይ በቀረቡት የተሃድሶ ውጤቶች ብዛት ለመለየት ይቻላል። ከአራት ሺህ የሚበልጡ አዳዲስ ነገሮች ቀርበዋል። ይህም ከዚህ ቀደም በአንድ ኤግዚቪሽን ላይ ካየነው ሁሉ የሚበልጥ ነው። ከተሳታፊዎች ምዝገባም የታዘብነው ነገር አለ። 4.800 አቅራቢዎች ሲመጡ ይህ ደግሞ ከ 2008 ዓ.ም. ግሩም ተሳትፎ ጋር የሚስተካከል ነው። እናም የዘንድሮውን ትዕይንት ተሥፋ ሰጭ ያደርገዋል”

ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋማትና የኤኮኖሚው ቀውስ

Türkei Istanbul Robert Zoellick Jahrestagung IWF und Weltbank

የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ሮበርት ዞሊክ

የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ. በያዝነው ሣምንት መጨረሻ ዋሺንግተን ላይ በዓመቱ የመጀመሪያ ወራት የተለመደ ስብሰባቸውን ያካሂዳሉ። ሁለቱ ተቋማት በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ እንደገና ትርጉም ቢያገኙም ገና ብዙ ሥራ ነው የሚጠብቃቸው። መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል የዓለም ባንክ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የሕልውና ትርጉሙን እስከማጣት ነበር የደረሰው። ድህነትን እንዲታገል የተቋቋመው የዋሺንግተን ተቋም የሚሰራው ነገር አጥቶ ነበር ለማለት ይቻላል።

ቻይና በአፍሪቃ መዋዕለ-ነዋይ ታፈሳለች። በርካታ የእሢያ አገሮች በተፋጠነ ዕርምጃ የአዳጊም አዳጊ ከሆኑት አገሮች ደረጃ ሲደርሱ ላቲን አሜሪካ ደግሞ የራሷን የልማት ባንክ አቋቁማለች። ሆኖም ግን ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ታዳጊዎቹን አገሮች ከበለጸጉት ይልቅ ክፉኛ መምታቱ ከተወቀ በኋላ አሁን ሁኔታው መለሶ ተለውጧል። የዓለም ባንክ ድንገት ተፈላጊ እየሆነ ሲሄድ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የሰጠው ብድር መጠን መቶ ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚጠጋ ነው።

ታዳጊ አገሮች ቀድሞ የ 12 ሚሊያርድ ዶላር ብድር ሲወስዱ በቀውሱ ሂደት ግን ይሄው ወደ 21 ሚሊያርድ ከፍ ብሏል። የዓለም ባንክ ዕሕት ድርጅት ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋምም እንዲሁ በቀውሱ ነው ወደ ሕልውናው የተመለሰው። አንዳንዶች የተባበሩት መንግሥታት የእሣት አደጋ መከላከያ ያሉት አይ-ኤም.ኤፍ የቀውስ ጊዜ የገንዘብ ክምችቱን ዛሬ ከ 50 ወደ 550 ሚሊያርድ ዶላር ከፍ ለማድረግ ችሏል። በዚሁ ቡድን-ሃያ መንግሥታት ባለፈው ዓመት ለንደን ላይ በተስማሙበት የገንዘብ መዋጮ ቻይናን፣ ሕንድን፣ ብራዚልንና ሩሢያን የመሳሰሉ በዕድገት የተራመዱ 13 ሃገራትም ተሳታፊዎች ናቸው።
የምንዛሪው ተቋም በፊናንሱ ቀውስ ሂደት እንደታየው በአውሮፓም መርዳቱ ዛሬ የተለመደ ነገር ሲሆን በእሢያው ቀውስ አመኔታ አጥቶ የነበረው ድርጅት አሁን እንደ ብድር ሰጪና ምክር ለጋሽ እንደገና ተፈላጊ ነው። ግን እስከመቼ? የተቋሙ የመዋዕለ-ነዋይ ገበያ ዘርፍ ሃላፊ ሆሴ ቪኛልስ ባለፈው የበልግ ስብሰባ የሕልውናው አደጋ ገና እንዳልተሰወረ ነበር ያመለከቱት።

“በማገገም ጎዳና ላይ ነው የምንገኘው። ግን ይህ መላው አደጋ እንዳይመለስ ተሰውሯል ማለት አይደለም”

ይልቁንም በአንጻሩ አዳዲስ ፈተናዎች እየተደቀኑ ነው። የምንዛሪውን ተቋም ድጋፍ የሚፈልጉት ሃገራት ቁጥር በጨመረና ቁጥጥሩም ባነሰ ቁጥር ዲሢፕሊን ለጎደለው የበጀት አያያዝ፣ የገንዘብ ብክነትና አዲስ የትርፍ ፍለጋ ቁማሮ የበለጠ አደጋ ነው የሚደቀነው። ለዚህም ነው ለምሳሌ የጀርመን ፌደራል ባንክ አስተዳዳሪ አክስል ቬበር ለምንዛሪው ተቋም የሚቀርበው ገንዘብ ከቀውሱ በኋላ መልሶ እንዲቀንስ የሚያስገነዝቡት።

“አሁን የምናያቸው የአይ.ኤም.ኤፍ ዕርምጃዎች ስለ መውጫ ስትራቴጂ፤ ወይም ስልታዊ መውጫ መርህ በምናወራበት ጊዜ አብረው መጤን አለባቸው። የምናወራው ወደፊት እርጋታን ስለሚያስከትል የፊናንስ ፖሊሲ ከሆነ፣ በእርጋታ አቅጣጫ ስለሚያመራ የገንዘብ ፖሊሲ ከሆነ ተቋሙም ከመጠን በላይ የስፋውን በጀት ሊመረምርና የወጪ ዕቅዱንም ሊያጤን ይገባል። ተቋሙ አሁን በቀውሱ ወቅት የመፍትሄ ፍለጋው አካል ሲሆን ወደፊት ደግሞ የመውጫው ስልት አካል መሆኑም ግድ ነው”

በጥቅሉ ወደፊት የፊናንስ ገበዮች ቁጥጥሩ ምን መልክ እንዲሚይዝም ገና በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም። ለነገሩ የፊናንሱ ዘርፍ የቀውሱን ወጪ በመሽፈኑ ረገድ ስለሚኖረው ድርሻ በፊታችን ሰኔ ወር ካናዳ ውስጥ በሚካሄደው የቡድን-ሃያ መንግሥታት ጉባዔ በጉዳዩ ለመወያየት ነው የሚታሰበው። ሆኖም ግን ባንኮች ቀውሱን እንዳልነበር በማድረግ የሚያሳዩት ዝንባሌ የፊናንሱን ቁጥጥር ጉዳይ አሁንም አጣዳፊ ስለሚያደርገው ጉዳዩ በፊታችን ሰንበት የዋሺንግተን ስብሰባ ላይ መነሳቱ እንደማይቀር የተቋሙ ሃላፊ ዶሚኒክ ሽትራውስ-ካህን ቃል ገብተዋል።

መስፍን መኮንን/DW

አርያም ተክሌ