የኢንቴርኔት መመለስ፣ የቁቤ ቁጣና የዘመነ ካሴ ጉዳይ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 09.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢንቴርኔት መመለስ፣ የቁቤ ቁጣና የዘመነ ካሴ ጉዳይ

ከሳምንት በላይ ተቋርጦ የዘለቀዉ የኢንተርኔት አገልግሎት ዳግም መመለስ፤ የቁቤ አፋን ኦሮሞ የፊደል አሰላለፍ፤ የገባበት ሳይታወቅ ለወራት ቆይቶ ከኤርትራ መዉጣቱ የተነገረዉ የቀድሞ የግንቦት ሰባት ታጋይ ስለሆነ አንድ ኢትዮጵያ የሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎችን ትኩረት ስበዉ ሲያወያዩ የሰነበቱ ጉዳዮ ናቸዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:14

ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

ኢንቴርኔት አገልግሎት መመለስ
ባለፈዉ ዓመት አሁን በያዝነዉ ወር፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባዉ ፈተና ሾልኮ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በመበተኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የፌስቡክ፣ የትዊተር፣ ኢንስታግራምና የቫይበር አገልግሎቶችን መዝጋቱ ይታወሳል። ዘንድሮም ከግንቦት 21 ቀን 2009 እስከ ሰኔ 1 ቀን 2009ዓ,ም የኢንቴርኔት አገልግሎት በመላ አገሪቱ መቋረጡ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ከፍተኛ መነጋገርያ ሆኖ ሰንብቷል። መንግሥትም የባለፈዉ ዓመት ድርጊት እንዳይደገም እና ተማሪዎችም ፈተናውን ተረጋግተው እንዲፈተኑ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ይፋ አድርጓል። ባለፈዉ ሳምንት ከሰኞ እስከ ረቡዕ ድረስ የ10ኛ ክፍል የመሰናዶ ትምህርት መግቢያ ፈተና ተሰቶ ተጠናቋል። ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያዉ የ12ኛ ክፍል ፈተናም በዚህ ሳምንት ከሰኞ እስከ ሐሙስ ድረስ ተሰጥቷል።

መንግሥት ፈተና እንዳለቀ የኢንቴርኔት አገልግሎቱን ነፃ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ነበር። ዶይቼ ቬሌ በትናንትናዉ ዕለት ለፌስቡክ ገፁ ተከታታዮች የኢንቴርኔት አገልግሎት በየአካባቢያቸዉ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠይቆ ነበር። አብዛኞቹ አገልግሎቱ ዳግም መጀመሩን ገልጸዉ፣ መንግሥትም የወሰደዉ ርምጃ በተማሪዎቹ የፈተና ሂደት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳለዉ ነዉ የገለጹት። አንዳንዶቹ ደግሞ የችግሩ መፍትሄ የኢንቴርኔት አገልግሎትን መዝጋት እንዳልሆነ አስተያየታቸዉን አጋርተዉናል።

ታምራት አለሙ ሲሳይ፤ በፌስቡክ « መንግሥት አገልግሎቱን ማጥፋቱ ተገቢ ነዉ፣ ከመንግሥት ይልቅ ለዚህ ተጠያቂ የሚሆኑት የፈተና ቦርዶችና መምህራኖች ታማኝ አለመሆናቸዉ ነዉ» ብሏል።

ኢዮብ አሻግሬ ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎቱን አስመልክቶ «ለዛሬ በዋስ ተለቋል» የሚል አስተያየት ጽፏል። አብርሃም ይስሃቅም «ኢንተርኔት ለፈተና ብሎ በመዝጋት ብቸኛዉ አገር እትዮጵያ» ሲል፤  ቪክ ጥላሁን ደግሞ « የመንግሥት አቅምና ብቃት ይሄዉ ነዉ፣ ኢንተርኔትን የሚያዩበት መንገድ "የጠበበና ክፉኛ የተንሸዋረረ" መሆኑን ተገንዝበናል።» የሚል አስተያየታቸዉን ሰንዝረዋል።

ተሾመ የሳዉድ አረቢያ ጅዳ ከተማ ነዋሪ መሆኑን ተናግሮ የኢኒተርኔት መዘጋት ከቤተሰቦቹ ጋር ለመገናኘት እንዳስቸገረዉና መንግሥት የወሰደዉ ርምጃ ዘላቂ መፍትሄ አለመሆኑን በዋትስኣፕ የድምፅ አስተያየት ልኮልናል።

በላይነህ ሙሉነህ በዶይቼ ቬሌ ፌስቡክ ገጽ «መንግሥት ኢንተርኔት ቢለቅም «ሰሞኑንን ያጡትን ገቢ ለማካካስ ነው መሰለኝ ደቂቃ ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ከ10ብር ያላነሰ ይቆርጣሉ» በማለት  ያጋጠማቸዉን አስፍረዋል።

የቁቤ አፋን ኦሮሞ አሰላለፍ የፈጠረዉ ዉዝግብ
ሰሞኑንም ሌላኛዉ የማኅበራዊ መገናኛዎች መነጋገርያ ሆኖ የሰነበተዉ የቁቤ አፋን ኦሮሞ የፊደል አሰላለፍ ዉዝግብ ነዉ። እንደ አዉሮጳዉያኖቹ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ የተማሪዎችን የመጻፍና የማንበብ ክህሎት ለማዳበር «Early Grade Reading Assesment »የተሰኘዉ ፕሮጀክት በአሜሪካዉ የርዳታ ድርጅት «USAID» 90 ሚሊዮን ዶላርስ የገንዘብ ርዳታ ተመድቦለት ሥራ ጀምሯል። ጥናቱም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአፋን ኦሮሞ ቃላቶችን በመዉሰድ የትኛዉ ቁቤ ወይም ፊደል በቃላት ዉስጥ በተደጋጋሚ መምጣቱን ከተመለከተ በኋላ የተለምዶዉ« ABCD»ተብሎ የሚቀጥለዉ ሳይሆን «LAGIM» መሆንኑ የጥናቱ ግኝት እንዳመለከተ ይገለጻል። ከዚህ በመነሳትም የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ቁቤን ሲማሩ እንደተለመደዉ «ABCD» ሳይሆን «LAGIM» ብለዉ እንዲማሩ መጽሐፍት ተዘጋጅተዉ ካለፉት ሦስት ወሰነ ትምህርት ጀምሮ እየተማሩ መሆኑን ከሀገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን የተከታተሉ በአገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ  የሚኖሩ የአሮሞ ተወላጆች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶቻቸዉን ሲያስነብቡ ሰንብተዋል።

ኦፕራይድ ዶት ኮም በፌስቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረዉ ጽሑፍ « የክልሉ ትምህርት ቢሮ ርምጃ እንዴት የመጻፍና የማንበብ ክህሎታቸዉን ያሻሽላል?» ሲል ይጠይቅና፤ « ይልቁንስ የትምህርት ጥራት ላይ ቢያተኩር እንደምሻለዉ፤» ያሳስባል። ባሪ አያኖ ደግሞ «ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ ያልቻሉበት ምክንያት የቁቤ አሰላለፍ ችግር ሳይሆን የሰለጠኑና በቂ ክህሎት ያላቸዉ መምህራን ስለሌሉ ነዉ ።» ይላል።

በዚህ ፕሮጄክት የተሳተፉት እና በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህር የሆኑት ዶክተር ቶለማርያም ፉፋ የሰጡት መልስም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዉ ተሰራጭቷ። ዶክተሩ ስለፕሮጀክቱ አላማ፣ ሲናገሩ፤ «እኛ «ABCD» ብሎ የተቀመጠዉን ለመቀየር አይደለም። ማንም ሊቀይረዉ አይችልም። አሁን እኛ ይዘን የመጣነዉ ፊደል ለአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ብቻ ነዉ። ይህም ተማሪዎች በአጭር ግዜ ዉስጥ መጻፍና ማንበብ የሚያስችል የማስተማርና የመማሪያ ዘዴ ነዉ።»

ኦስሎ ኖርዌይ የሚኖሩት የስነ ቋንቋ ባለሙያ አቶ አማኑኤል ራጋ ይህ የዘዴ አለዉ ያሉት ተጽዕኖ ለዶይቼ ቬሌ እንዲህ ገልጸዋል፣ «አንደኛ ተማሪዎች ይህን የተምታታ ፊደል ተምረዉ ወደ ከፍተኛ ክፍል ሲሻገሩ ተመሳሳይ ፊደሎች የሚጠቀሙት የሌሎች ቋንቋዎች ፊደሎችም እንደዛዉ ሊመስላቸዉ ይችላል። ሁለተኛዉ የዚህ የአዲሱ የቁቤ አፋን ኦሮሞ ታኣማኒነት ጥያቄ ዉስጥ ነዉ ያለዉ። እዉነት ይህ የቁቤ ችግር ነዉ ወይ የሚል ጥያቄ ማንሳት አለብን። ከዛ በተረፈ የቁቤ አፋን ኦሮሞ ከኦሮሞ ቀንቋ ታሪክና ከሕዝቡ ጋር የተገናኘ ነዉ። የአሮሞ ማንነት በዚህ ሰዓት የሚገለጸዉ ወይም ኦሮሞነትን ለመግለጽ የቀረዉ ነገር ካለ ቀንቋዉ ነዉ። ስለዚህ ይህን ከማንነት ጋር የተቆራኘ ነገር መነካካት አስፈላጊ አይደለም።»


ዘመነ ካሴ ከኤርትራ መልስ
በማኅበራዊ መገናኛዉ የሰሞኑ መነጋገሪያ ከሆኑት ጉዳዮች አንደኛዉ ደግሞ የቀድሞ የግንቦት ሰባት ታጋይ ዘመነ ካሴ የተባለ ግለሰብ ለ15 ወራት መጥፋቱ መነጋገርያ ሆኖ መቆየቱን ይጠቁማል። ግለሰቡ አሁን ከኤርትራ ወጥቶ ሌላ አገር ዉስጥ መሆኑን በማኅበራዊ መገናኛዎች በተሰራጨዉ አጭር የቪዲዮ መልዕክት የገለጸ ሲሆን ከአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮችም ሳይፈልግ እንደተለያቸዉ ይናገራል።

ዘመነ ከኤርትራ ለምን ተሰወረ፣ እንዴት አድርጎ ወጣ የሚሉት ጥያቄዎች በማህበራዊ መገኛዎች ሲመላለስ ታይቷል። ከግቦት ሰባት ወጥቶ ወደሌላ ድርጅት ገብቷል የሚሉ አስተያየቶችም እንዲሁ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ የሚመስሉ አስተያየት ሰጪዎች ይህን መሰል ጥያቄዎችን ቢሰነዝሩም፤ የመወያያ ርዕስ የሆነዉ ዘመነ በቪዲዮ መልዕክቱ ወደፊት ምክንያቱን በሰፊዉ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ዮሐንስ አማራ በፉስ ቡክ፤ « ዘመነ በመመለሱ በጣም እንደተደሰተ ገልጾ ላጋጠመዉ የጤና ችግር ቶሎ ርዳታ እንዲያገኝ ተመኝቷል። ህክምና እንዲያገኝ በጎፈንዲ የተጀመረዉ የገንዘብ ማሰባሰብ ለግዜዉ ቢስተጓጎልም አስተባባሪዎቹ ቶሎ መፍትሄ እንደሚያገኙለትም ገልጿል። ሌሎችም ተመሳሳይ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። ለየት ያለችዉ አስናቀች አዳል በሚል ስም የቀረበች አስተያየት ናት።

አስናቀች አዳል፤ «ምናልባት በድጋሚ የተረጋገጠ እውነት ቢኖር የኤርትራም መንግሥትም ሆነ እዚያ ያሉ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ትግል የደበረውን ወይም ያልተመቸውን አፍነው ለማስቀረት የፀና ውሳኔ እንደሌላቸው መታየቱ ነው።» ትላለች በመቀጥልም «ብዙ ጊዜ ትጥቅ ትግል የሚል ስልት የሚከተሉ ድርጅቶች በአባላቶቻቸው ላይ የዲስፕሊን ርምጃ በሚል እስከ ማስወገድ የሚደርስ ደንብ በስምምነት በማፅደቅ ተግባራዊ ሲያደርጉ ይታወቅ ሰለነበርና የኤርትራም መንግሥት በተለያየ ምክንያት አፍኖ የሚያስቀራቸው ኢትዮጵያዊያኖች መኖራቸው በተደጋጋሚ ሲነገር በመስማታችን ነው። ያም ሆነ ይህ የዘመነ ካሴ ዲያስፖራውን መቀላቀል ለአርበኞች ግንቦት ፯ እና ለኤርትራ መንግሥት ትልቅ ድል ለማህበራዊ ሚዲያ አሉባልተኞች ክስረትና ምናልባትም ተአማኒነት የሚያሳጣ ክስተት ነው።» ብላለች።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ  

Audios and videos on the topic